በትምህርት ቤቶች አካባቢ የተከፈቱ ሰባት ሺህ ጫትና ሺሻ ቤቶች ተዘግተዋል

አዲስ አበባ፡- በበጀት ዓመቱ በትምህርት ቤቶችና ህፃናት በሚኖሩበት አካባቢ የተከፈቱ ሰባት ሺህ ጫትና ሺሻ ቤቶች እንዲዘጉ ማድረጉን የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

ባለሥልጣኑ በ2016 በጀት ዓመት ከቁጥጥር ጋር ተያይዞ የሠራቸውን ሥራዎች ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ትናንት ገምግሟል፡፡

የባለስልጣኑ ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ በወቅቱ እንዳሉት፤ በትምህርት ቤቶች እና ህፃናት በሚኖሩበት አካባቢ የተከፈቱ ሰባት ሺህ ጫት ቤቶች እና ሺሻ ቤቶች እንዲዘጉ ተደርጓል፡፡

በአጠቃላይ የተሠራው ሥራ ሲታይ ውጤታማ ነው ያሉት ሻለቃ ዘሪሁን፤ ይህ ውጤት የተገኘው ከህብረተሰቡ ተሳትፎ እና ከባለ ድርሻ አካላት ቅንጅት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የንግድ ቢሮ፣ የግንባታ ፈቃድ፣ የከተማዋ ፅዳት ኤጀንሲ እንዲሁም ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት በቅንጅት በመሆን ያደረጉት አስተዋፅኦ እና አብሮነት የሚደነቅ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

የባለሥልጣኑ አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ቀፀላ ባቀረቡት ሪፖርት እንደተናገሩት፤ ሕገወጥ ንግዶችን ከማገድ ባለፈ ከዘጠኝ ሺህ በላይ ሕገ ወጥ ግንባታዎች እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡

በተጨማሪም ሰማንያ ዘጠኝ የሚጠጉ ሕገ ወጥ ስጋ ቤቶች ማዘጋት እንደተቻለ ጠቁመው፤ ባለሥልጣኑ ማሳካት ለሚፈልገው ዕቅድ በተለይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መሥራቱ ውጤታማ እንዳደረገው አስረድተዋል።

የቅድመ መከላከል ሥራዎች ከአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ክበባት ጋር በመሆን መሠራቱን አስታውሰው፤ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለሚሆን የትምህርት ማህበረሰብ አባላት ግንዛቤ ፈጥረናል ብለዋል።

ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ ከግል ኮሌጆች እና ከማርኬቲንግ ተቋማት ጋር ውጤታማ ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በተለይ ከሚዲያዎች ጋር የተሠራው የግንዛቤ መስጫ ዝግጅቶች ተጠቃሽ እና የሚበረታታ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ከፅዳት ጋር ተያይዞ ከከተማዋ ፅዳት ኤጀንሲ ጋር በመሆን የጋራ ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቅሰው፤ ከህብረተሰቡ ጤና እና ከሀገር ኢኮኖሚ አንፃር ችግሮች እንዳይከሰቱ በቅንጅት ሲሠራ ቆይቷል ብለዋል፡፡

በከተማዋ የሚገኙ ክፍት መሬቶች ወደ መሬት ባንክ እንዲመለሱም ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል፡፡

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You