የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ የኃይል መሙያ ሥርዓት ወደ ሥራ ሊገባ ነው

አዲስ አበባ ፡- የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ የኃይል መሙያ (EV-CHARGE) ሥርዓት እየተዘጋጀ ሲሆን በቅርቡ ወደ ሥራ ለማስገባት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቶችና የመመሪያ ሥርዓቶች እየተዘጋጁ መሆኑን የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለሥልጣን አስታወቀ::

የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አህመድ ሰይድ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ የኃይል መሙያ (EV- CHARGE) ሥርዓት መመሪያን በተመለከተ በኃይሌ ግራንድ ሆቴል ከትናንት በስቲያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገ ውይይት ላይ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ከነዳጅ ኃይል ከሚሰሩ ተሽከርካሪዎች በታዳሽ ኃይል ወደሚሰሩ ተሽከርካሪዎች እየተሸጋገረች ሲሆን ለዚህም የሚረዱ ዘርፈ ብዙ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው::

ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን መመሪያ ወጥቷል ያሉት አቶ አህመድ፤ በአሁኑም ወቅት የመጨረሻው ረቂቅ ላይ ውይይት ተደርጓል:: በመቀጠል ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መመሪያውን ካፀደቀው በኋላ ወደ ፍትህ ሚኒስቴር በመላክ ወደ ሥራ የሚገባ ይሆናል፤ ለዚህም እየተነጋርን ነው ፤ ስታንዳርድና ሕጎችን እንደ ባለሥልጣን የምናወጣ ሲሆን የሚመለከታቸው አካላት ደግሞ የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ የሚጠበቅብንን እየሠራን ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በየዓመቱ ነዳጅ ለማስገባት ከ 6 ነጥብ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ እያወጣች መሆኑን የተናገሩት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህ በሀገሪቱ ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያሳድር በመሆኑ ወደ ታዳሽ ኃይል መግባት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህ ጉዞ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ብክለትን ለመከላከል የምታደርገው ጥረት አካል ሲሆን በወጪ ደረጃም በጣም አዋጭ መሆኑን ገልፀዋል:: ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ በርካታ የታዳሽ ኃይል አማራጭ ያላት ሀገር በመሆኗ ይህን ለመቀጠቀም መወሰኗ በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል::

በነዳጅ እና ኢነርጂ ባለሥልጣን የብቃት ማረጋገጥና ቴክኒካል ሬጉሌሽን ቡድን መሪ ኢንጂነር ዳንኤል ስጦታው በበኩላቸው፤ መመሪያው ሀገሪቱ በየጊዜው እያሳየች ያለውን ዕድገት ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ እንደአስፈላጊነቱ የታዳሽ ኃይል ሥራ ላይ ሲውል በሕግ እንዲመራ ሀገሪቱ ብሎም ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማሰብ ነው ሲሉም አስረድተዋል::

መመሪያው በኢትዮጵያ ውስጥ ለኤሌክትክ ተሽከርካሪ ኃይል ሙሌት አገልግሎት በሚሰጥ ወይም በሚጠቀም ማንኛውም ሰው አሊያም ድርጅት ላይ ተፈጻሚ የሚሆን ሲሆን፤ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች ያሉት መሆኑንም አመልክተዋል::

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎችን ለመጠቀም መወሰኗ እና ወደ ተግባር መግባቷ አስደሳች መሆኑን ገልፀዋል:: ይሁንና ይህ ኢንቨስትመንት በዓይነቱ አዲስ በመሆኑ ማበረታቻዎች፣ አስቻይ መመሪያዎችና የሀገሪቱን መፃዒ ዕድሎችን ብሎም ቀጣይነት ያለው ኢንቨስትመንትን ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን በጥልቀት ሊመከርበት እንደሚገባ ጠይቀዋል::

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You