ፕሪሚየርሊጉ አዲስ ቻምፒዮን ያገኝ ይሆን?

በ1990ዓ.ም በአዲስ መልክ መካሄድ በጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪምየርሊግ ስምንት ክለቦች ዋንጫውን አንስተዋል። ባለፉት 26 ዓመታት ቻምፒዮን በመሆን የአዲስ አበባ ክለቦች ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙ ሲሆን፤ ሁለት ክለቦች ወደ ሊጉ ባደጉበት ዓመት ዋንጫውን መውሰድ ችለዋል። በዘንድሮ የውድድር ዓመትም ይኸው ታሪክ ሊደገም እንደሚችል ፍንጭ እየታየ ነው። የዚህ ታሪክ አካል እንደሚሆን የሚጠበቀው ክለብም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው።

የ2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቻምፒዮኑን ለመለየት የጥቂት ጨዋታዎች እድሜ ብቻ ቀርተውታል። ይሄንን ታሪክ ለመጻፍ እየተንደረደረ የሚገኘው ደግሞ አዲስ አዳጊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እግር ኳስ ክለብ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። ክለቡ ከፈረሰ በኋላ በአዲስ መልክ ተቋቁሞ ወደ ፕሪምየርሊጉ በማደግ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ቻምፒዮን ለመሆን እየገሰገሰ ነው። የዘንድሮውን ፕሪምየርሊግ የሚያሸንፍ ከሆነም ባደገበት ዓመት የሊጉን ዋንጫ በማንሳት ታሪክ ሶስተኛው ክለብ ይሆናል። ከዚህ ቀደም ይሄን ታሪክ ከሰሩት ክለቦች መካከል ቅዱስ ጊዮርጊስ በ1990 ዓ.ም እና ጅማ አባጅፋር በ2010 ዓ.ም ይጠቀሳሉ።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋንጫውን ካነሳ ዘጠነኛው የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ ቻምፒዮን ክለብ ይሆናል። ባለፉት ዓመታት ሊጉን እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የነገሰበት ክለብ የለም። ፈረሰኞቹ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ዋንጫውን 16 ጊዜ በማንሳት ሲመሩ፤ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሶስት ጊዜ እና ሃዋሳ ከተማ ሁለት ጊዜ ዋንጫውን በማሳካት በቅደም ተከተል የተቀመጡ ክለቦች ናቸው። ኢትዮጵያ ቡና፣ ደደቢት፣ ጅማ አባጅፋር፣ መቐለ 70 እንደርታ እና ፋሲል ከነማ ደግሞ ዋንጫውን አንድ ጊዜ ማሳካት ችለዋል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለራሱ አዲስ ለሊጉ ደግሞ ተጨማሪ ታሪክ ለመጻፍ ከምን ጊዜውም በላይ የተቃረበ ይመስላል። ዓመቱን ሙሉ ድንቅ ብቃትን በማስመልከት ሊጉን እየመራ የሚገኘው ክለቡ 27ኛ ሳምንት ጨዋታዎች እየተካሄዱ በሚገኙበት በዚህ ወቅት ሁለት ነጥብ ቢጥልም ዋንጫውን ለማሸነፍ ግን የተሻለ እድል አለው። የሊጉ ጠንካራ ክለብና የዋንጫ ተፎካካሪ ከነበረው ባህርዳር ከነማ ጋር ያደረገውን ጨዋታ ከመመራት ተነስቶ ነጥብ መጋራቱ ለዋንጫው ይበልጥ እንዲገመት አድርጎታል። በአስገራሚ ሁኔታ እስከ 86ኛው ደቂቃ ድረስ 2 ለ 0 እየተመራ ቢቆይም በአዲስ ግደይ ሁለት ግቦች ታግዞ ነጥብ መጋራት ችሏል።

የዋንጫ ተፎካካሪ የነበሩት ክለቦች ባህርዳር ከነማ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ከውጤቱ በኋላ ከፉክክሩ መራቀቸው እርግጥ ሆኗል። አሁን የቀረው ብቸኛ የዋንጫ ተፎካካሪም መቻል ብቻ ነው። ንግድ ባንክ የተሻለ የማሸነፍ እድልን ይዞ ቀሪዎቹን መረሃ ግብሮች ያከናውናል። በርካታ የግብ ክፍያዎች ያሉት በመሆኑ ከተከታዩ ክለብ በነጥብ እንኳን እኩል ቢሆን ዋንጫውን ማሳካት ይችላል። ክለቡ ከሚቀሩት ሶስት ጨዋታዎች ሁለቱን ካሸነፈ በነጥብ እኩል ስለሚሆኑ በግብ ክፍያ ታግዞ ቻምፒዮን የሚሆንበት እድል ይኖራል ማለት ነው።

ንግድ ባንክ በ27 ሳምንታት የሊጉ ጉዞ 17 ጨዋታዎችን በማሸነፍ፣ 6 ጨዋታዎችን በአቻ በመለያየትና 4 ጨዋታዎችን ብቻ በመሸነፍ 57 ነጥቦችን ሰብስቦ ወደ ዋንጫ የሚደረገውን ፉክክር በቀዳሚነት እየመራ ይገኛል። የአጥቂ ክፍሉ የሚያገኘውን እድል የማይምር ቢሆንም የተከላካይ ክፍሉ ግን በተወሰነ መልኩ ጥንካሬውን ያጣ ይመስላል። ያም ቢሆን የአጥቂ ክፍሉ ጥንካሬ ክለቡን ለዋንጫ እንዲጠበቅና ቅድመ ግምት እንዲሰጠው ማድረግ ችሏል። በዚህም መሰረት 52 ግቦችን በተጋጣሚ መረብ ላይ ሲያዘንብ 26 ግቦች ደግሞ ተቆጥረውበታል።

ቀጣይ 28ኛ ሳምንት የሊጉ መረሃ ግብር ከኃያሉ ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት ጨዋታ ከባድ ከመሆኑ ባለፈ ዋንጫ የማንሳት እድላቸውን የሚያሰፉበት አሊያም አጣብቂኝ ውስጥ ሊከታቸው የሚችልም ይሆናል። በእርግጥ ፈረሰኞቹ ምንም እንኳን መጥፎ የውድድር ዓመትን እያሳለፉ ቢሆንም በቀላሉ እጅ ይሰጣሉ ተብሎ አይጠበቅም። ከጨዋታው ነጥብ ይዞ መውጣት ደግሞ ለንግድ ባንክ ቻምፒዮን ለመሆን የሚጓዘውን መንገድ ሊያቀልለት እንደሚችል ይጠበቃል።

የ29ኛ እና 30ኛው ሳምንት መረሃግብር ከዚህ ጨዋታ አንጻር ቀለል ያሉ በመሆኑ ለቻምፒዮንነት የሚያስፈልጉትን ነጥቦች ያሳካል ተብሎም ይጠበቃል። በመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች መውረዱ የሚቀር ከማይመስለው ሻሸመኔ ከተማ እና የበፊት አቋሙን መድገም ከተሳነው ኢትዮጵያ መድን ወሳኝ ፍልሚያ ያደርጋል። ከእነዚህ የጨዋታ ትዕይንቶች በኋላም የ2016 ዓ.ም የሊጉ አሸናፊ ብቻም ሳይሆን 9ኛው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቻምፒዮን ክለብ ማነው የሚለው ምላሽ የሚያገኝ ይሆናል።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ሰኔ 8/2016 ዓ.ም

Recommended For You