በተለምዶ ‹‹ሱፍ›› የምንለው የወንዶች ሙሉ ልብስ አይነት በወንዶች በስፋት እንደ ፕሮቶኮል ልብስ ተደርጎ ይወሰዳል፤ ለየት ላለ ፕሮግራምም ይመረጣል። ተማሪዎች በምረቃ ፕሮግራማቸው፣ በሠርግ ቀናቸው፣ በተለያየ የሥራ ኃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎችም እንዲሁ ይህን የልብስ አይነት ምርጫቸው ያደርጉታል። ‹‹ሱፍ›› ወይም ሙሉ ልብስ የለበሰ ሰው በተለምዶ ‹‹ሙሽራ›› መስለሃል ተብሎ ሲገለጽም ይሰማል።
የኔነህ ጥላሁን ይባላል። በሽያጭ ሥራ ባለሙያነት የረጅም ዓመት ልምድ ያለው ሲሆን፣ በወንዶች ሙሉ ልብስ /የሱፍ ልብስ/ ሽያጭ ሥራ ውስጥ ስምንት ዓመታትን አስቆጥሯል። የሱፍ ልብስ በቀደመው ጊዜ ውስን የሆኑ ተጠቃሚዎች ነበሩት ሲል ገልጾ፣ ገበያው ላይ የነበረው የዲዛይን አማራጭም ጥቂት እንደነበር ይናገራል። አሁን ላይ ሱፍ ልብስን ምርጫቸው የሚያደርጉ ወንዶች ቁጥር በርከት እያለ መምጣቱንም ይጠቅሳል።
‹‹የበፊቱ የሱፍ አይነት ኮቱ ረጅም፣ ሰፊ እና ለመልበስም ከበድ የሚል ነበር፤ የሚለበሰውም ወቅት እየተጠበቀ ብቻ ነው›› የሚለው የኔነህ፣ አሁን ላይ ብዙ አማራጮች እንዳሉ ተናግሯል ።
እሱ እንዳለው፤ በገበያው ላይ በርከት ያለ የሱፍ ልብስ አይነት ይገኛል፤ ልብሱ በአብዛኛው ‹‹ቱ ፒስ እና ስሪ ፒስ›› ተብሎ ይለያል። ኮት ሰደርያ እና ሱሪ የያዘው ስሪ ፒስ ሲባል፤ ብዙዎች የሚመርጡት ደግሞ ኮት እና ሱሪ ብቻውን የያዘው ቱ ፒስ የሚባለውን ነው ።
በአሁኑ ወቅት እንደ ፋሽን ተደርጎ ብዙዎች ምርጫቸው የሚያደርጉት ከሰዎች የሰውነት ቅርጽ ጋር ተስማምቶ የተሠራ የሱፍ ልብስ ‹‹ስሊም ፊት›› የሚባለው መሆኑን ይገልጻል። ይህም የተስተካከለና ጠበብ ያለ ትከሻ እና እግሩም ጠባብ የሱፍ ስፌት አይነት ያለው ነው ይላል። የበፊቱ የሱፍ ስፌት ወጥ መሆኑን አስታውሶ፣ እግሩም ሆነ ትከሻው አካባቢ ያልተመጠነ ስፌት እንደነበረው ተናግሯል።
የኔነህ እንዳብራራው፤ የሱፍ ልብስ በተለያዩ የቀለም አማራጮች በገበያው ላይ ይገኛል። ጠቆር ያለ ሰማያዊ፣ ጥቁር ቀለም በብዛት የሚመረጡ የቀለም አይነቶች ናቸው።
‹‹አሁን ላይ ብዙ የቀለም ምርጫዎች አሉ፤ ሰዎችም የተለያዩ የቀለም አይነቶችን ይመርጣሉ›› ሲል የኔነህ ይገልጻል። ‹‹ኮሌክሽን›› የተሰኘ የሱፍ አይነትም እንዳለ ይገልጻል። እሱም የሱፉ ኮት እና የሱሪው ቀለም የተለያየ አይነት ሲሆን፣ ይህም የሱፍ ልብስን አዘውትረው ለሚለብሱ ሰዎች አልያም ሙሉ ሱፍ መልበስ ምርጫቸው ላልሆነ ሰዎች ከሚኖራቸው ሌላ ሱፍ ጋር አጣምረው እንዲለብሱ ያስችላቸዋል ።
በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው የሱፍ ልብስን ምርጫቸው የሚያደርጉ እና ከሱፍ ልብስ ውጪ የማይለብሱ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ ሱፍ መልበስ ከዚያም ክራቫት ጨምሮ ማድረግ ጭንቀት የሚያሳድርባቸውም አይጠፉም። ለመጀመሪያ ጊዜ የሱፍ ልብስ ለመግዛት ወደ መሸጫ ቦታዎች የሚያመሩት ወጣቶች ከሆኑ ለምርቃ ሥነ-ሥርዓታቸው፣ ሲያገቡ አልያም የወዳጆቻቸው ሠርግ ላይ ሚዜ ሲሆኑ ነው።
ይህ የወንዶች የፕሮቶኮል ልብስ ተደርጎ የሚወሰደው ሱፍ በመላው ዓለም የሚታወቅ እና ተቀባይነትን ያገኘም ነው። ፈረንሳይ እና ጣሊያን በስፋት ይታወቁበታል። ወደ ሀገራችን የሚገቡ የሱፍ ልብሶችም ቱርክን ጨምሮ ሦስቱ ሀገራት በስፋት የሚታወቁባቸው ናቸው። ‹‹በሱፍ ልብስ ጣሊያንና ፈረንሳይ በጣም ስለሚታወቁ ዋጋቸውም ውድ የሚባል ነው። ከቱርክ የሚመጣው ግን ዲዛይኑም ጥሩ ነው ዋጋው ተመጣጣኝ ነው፡፡›› የሚለው የኔነህ፣ በሀገራችን አሁን ላይ የቱርክ የሱፍ ልብሶች በገበያው ላይ በስፋት እንደሚገኙ ይገልጻል ።
የሱፍ ልብስም እንዲሁ በእይታ በመውደድ ብቻ የሚለበስ አለመሆኑን የሚያነሳው የኔነህ፣ የትኛው የሱፍ ቀለም ከምን አይነት የቆዳ ቀለም ጋር፣ የትኛው ሱፍ ከየትኛው ሸሚዝ እና ከረቫት ጋር እንደሚሄድ ማወቅን ይጠይቃል ሲል ያብራራል።
ታዲያ ሱፍ ለመግዛት ያሰቡ ሰዎች እውቀት ኖሯቸው ይመጡ ይሆን ወይ ብለን ላቀረብንለት ጥያቄ ሲመለስም፤ ያለፉትን ሦስት ዓመታት ወንዶች በደንብ ስለ ሱፍ አጥንተውና የሚወዱትን አይነት መርጠው ሲመጡ ማስተዋሉን ተናግሯል። የሱፍ ልብስ ተስተካክሎ እና ተሰፍቶ ተዘጋጅቶ እንደሚሸጥ ጠቅሶ፣ የራሱ መጠን እንዳለውም ይገልጻል። ሰዎችም ሱፉን ሲገዙ ባላቸው የትከሻ ልክ የሚመጠን ፈልገው መሆኑን አመልከቶ፣ ከ44 ቁጥር ጀምሮ ግዙፍ እስከሚባለው እስከ 60 ቁጥር ድረስ ልብሱ ገበያ ላይ እንደሚገኝ፣ ልኬቱም ሙሉ ቁጥር ብቻ መሆኑን አስታውቋል።
እሱ እንዳብራራው፤ የሱፍ ልብስ ስፌት ችሎታ እና ጥንቃቄ ይፈልጋል፤ ወንዶች ምርጫቸው የሆነው ሱፍ ባይበቃቸው በጥንቃቄ የሚስተካከልበት ሁኔታ ይኖራል።
ቆንጆ ሱፍ የሚባል ቢኖርም፣ በሥራው የረጅም ዓመት ልምድን የያዘው የሽያጭ ባለሙያ ግን ሱፍ የማያምርበት ሰው እንዳለም ተናግሯል። እሱም ከትከሻ እስከ ወገብ እና ከወገብ በታች የሚኖረው የሰውነት ቅርጽ ያልተመጠነ ሲሆን ሱፉ የሚኖረውን ውበት እንደሚደብቀው አስተውሏል ።
የሱፍ ልብስ ስፌት አይነት ‹‹ሬጉላር ድሮፕ 7 ለቀቅ ያለ የስፌት አይነት እና ድሮፕ 6 የሰውነት ቅርጽን ተከትሎ የሚሄድ የስፌት አይነት ያለው ነው።›› ሲል አብራርቶ፣ የሱፍ ልብስ ብቻውን ውበት ያለው ቢሆንም ሸሚዝ፣ ከረባት እና ለየት ያሉ የጫማ አይነቶች ከሱፍ አለባበስ ጋር አብረው እንደሚሄዱ ገልጸል። ይህም ምርጫ ጥንቃቄ እንደሚሻ የኔነህ ያነሳል ፡፡
እሱ እንዳስታወቀው፤ ሱፍ አሁን ላይ ቀለል ባለ መንገድ ሊዘጋጅም ይችላል፤ ለየት ላለ ፕሮግራም የሚለበሱ የሱፍ አይነቶችም አሉ። ልክ እንደ እንስቶች ቬሎ ለሠርግ ብቻ ተብሎ የተመረጠ የሱፍ አይነትም አለ። በመሆኑም ሱፍ ለመግዛት የወሰኑ ወንዶች የሱፉን ጥራት፣ ከእነርሱ ቀለም፣ ተክለ ሰውነት ጋር አብሮ የሚሄደውን ማየት ይገባቸዋል። አንድ ሱፍ የሚሸጥበት ዋጋ እንደሚመጣበት ሀገር፣ የጨርቅ አይነት ይለያያል።
የሕግ ባለሙያዎች፣ የባንክ ሠራተኞች፣ አብዛኛውን ጊዜያቸውን በቢሮ ውስጥ የሚያሳልፉ የቢዝነስ ሰዎች ሱፍን ያዘወትራሉ።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም