አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ እና አዲስ የማድረጉ የልማት ጉዞ

ከ135 ዓመታት በላይ ያስቆጠረችው አዲስ አበባ እንደስሟ አዲስ እና ውብ ሳትሆን ዘመናትን ተሻግራለች። እንዴውም ከስሟ በተጻራሪ የቆሻሻ እና የብክለት ተምሳሌት ሆና ያለፉትን ዘመናት አስቆጥራለች። በውልደትና በስደት በየጊዜው የሚያሻቅበውን የሕዝብ ቁጥር የሚመጥን የመኖሪያ ቤትና ሌሎች ተያያዥ መሠረተ ልማቶችን ማሟላት ባለመቻሏም ከፍተኛ ሆነ ጉስቁልና የሚታይባት ከተማ እንድትሆን አድርጓታል፡፡

በተለይም መሐለኛው የአዲስ አበባ ክፍል ችምችም ብለው በተሠሩ ቤቶች የታጨቀ፤ ከዘመኑ ጋር ያልዘመነ፤ ከ135 ዓመታት በፊት በነበረው የቀጠለ እና በአሁኑ ወቅት ያለውን የአኗኗር ሁኔታ የማይመጥን ነው። አብዛኞቹ ቤቶች አንድ መፀዳጃ ቤትን ለሠላሳ፤ ለአርባ የሚጠቀሙ ብዙዎችም መፀዳጃ ቤት የሌላቸውና በየጥጋጥጉ ለመጠቀም የተገደዱ ዜጎች ያሉባቸው አካባቢዎች ናቸው።

ልብ ብሎ ላየው ይህ አኗኗር ልብን የሚሰብር ነው። በዚህ ዘመን ሰዎች አንድ መፀዳጃ ቤትን ለሠላሳ እና ለአርባ ሲጠቀሙ፤ ከዝናብም ሆነ ከፀሐይ በማያድኑ በተጎሳቀሉ ቤቶች ውስጥ ዜጎች ተደራርበው ሲኖሩ ሲታይ መንፈስን ያውካል። በእነዚህ ጎስቋላ ሰፈሮች ሴተኛ አዳሪነት፤ ጎዳና ተዳዳሪነት፤ ዝርፊያና ግድያ ተንሰራፍቶ ከመገኘቱም በላይ የዜጎች በሠላም ወጥቶ የመግባቱ ጉዳይ በእጅጉ አሳሳቢ ሆኖ መገኘቱ ጉዳዩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ያደርገዋል።

ፒያሳን የመሳሰሉ አካባቢዎች ስማቸው ገናና ቢሆንም በገቢር ግን ስማቸውን የሚመጥን ገጽታ የላቸውም። ምንም አይነት ዘመናዊነት የማይታይባቸው ኋላቀር አካባቢዎች ከመሆናቸውም በላይ በስመ አራዳ ለዘመናት ድህነት ተጭኗቸው የቆዩ ናቸው።ስምና ግብር በተራራቀበት በእነዚህ ሰዎች በአንዲት ክፍል ውስጥ ቆጥና ምድር ሠርተው፤ መፀዳጃ ቤት ተጋርተው፤ በአንዲት ክፍል አስር፤ አስራ አምስት ሆነው ተደራርበውና ተነባብረው የሚኖሩባቸው የድህነት ጥግ የሚታይባቸው የከተማችን አካል ናቸው ፡፡

የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፤ የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ እና የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ ክብሯንና ከፍታዋን የሚመጥን ገጽታና መሠረተ ልማት ሳይሟላላት ዛሬ ላይ ደርሳለች። ከዚህ በላይ መቀጠል የከተማዋን የአፍሪካ መዲናነትና የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡

እነዚህንና ሌሎች ማኅበራዊና ኢኪኖሚያዊ ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ በማስገባት መንግሥት ከተማዋን እንደስሟ ውብና አዲስ ለማድረግ ቀርቶ ከተነሳ ወራቶች ተቆጥረዋል። ከተማዋ ካለባት የመሠረተ ልማት እጥረት እና የሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ እንዲሁም ዘመናት ያስቆጠሩ መሠረተ ልማቶችን ለማዘመን፣ ለማደስ እና የነዋሪዎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የኮሪደር ልማት ማከናወን መጀመሩ ይታወቃል፡፡

በመጀመሪያ ዙርም በዓድዋ ድል መታሰቢያ ፒያሳ-አራት ኪሎ-ቀበና-መገናኛ፤ አራት ኪሎ-ቦሌ አየር ማረፊያ-ቦሌ ድልድይ-መገናኛ፤ ከመገናኛ-አዲስ አፍሪካ ኮንቬንሽን ማዕከል ሲኤምሲ እንዲሁም ከሜክሲኮ-አፍሪካ ኅብረት-ሣር ቤት ወሎ ሰፈር 40 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኮሪደር ልማት ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡

ከፒያሳ እስከ አራት ኪሎ፣ ከአራት ኪሎ እስከ ቦሌ ድልድይ፣ ከቦሌ ድልድይ በመገናኛ ወደ ሲኤምሲ፣ ከቦሌ ተርሚናል ወደ ጎሮ፣ ከሜክሲኮ ወደ ወሎ ሠፈር፣ እንዲሁም ከእንግሊዝ ኤምባሲ ወደ አራት ኪሎ የሚወስዱ ኮሪደሮች ወደ ግንባታ ገብተው አብዛኞቹ መንገድ፤ የኤሌክትሪክ፤ የውሃና የቴሌ መሠረተ ልማቶች ወደ መገባደዱ ደርሰዋል። በተለይም ከፒያሳ እስከአራት ኪሎ ያለው መንገድ አብዛኞቹ መሠረተ ልማቶች ተሟልተውለት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡

የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ብስክሌትና ሌሎች የመዝናኛና የእግር ጉዞ እንዲሁም ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ማዘውተሪያ ስፍራዎችን የሚይዝ በመሆኑ አዲስ አበባ ያላትን አሕጉራዊና ዓለም አቀፍ ደረጃዋን ከፍ የሚያደርግ ነው። በኮሪደር ልማት ሥራው ቀደም ሲል የነበሩ ሕንጻዎች በመታደሳቸውና አንዳንዶቹም የቅርጽ ለውጥ በማድረግ ጭምር ውብና ማራኪ እንዲሆኑ በመደረጋቸው ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት መፍጠር ችለዋል። የሕንጻዎቹ የቀለም ቅብና ፅዳት ዓይን በሚማርክ መልኩ ተውቧል። በቀጣይም የሚሠሩት ሕንጻዎች ዓለም አቀፍ ደረጃ ወጥቶላቸው በዘመናዊ መልኩ ስለሚገነቡ አዲስ አበባ እንደስሟ አዲስ የምትሆንበት ቀን ሩቅ አይሆንም።

በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን ያየ ከሚደመምባቸው ተግባራት አንዱ የእግረኛ መንገዶች ስፋትና የአረንጓዴ ልማት ተጠቃሾች ናቸው። አንድ ከተማ ለነዋሪዎች ምቹ እና ዘመናዊ ነው የሚባለው የተስተካከለ የመንቀሳቀሻ መንገዶች ሲሟሉ ጭምር በመሆኑ የእግረኛ መንገዶቹ ስፋት ፈረስ የሚያስጋልብ የሚባል አይነት እየሆነ ነው።

ከእግረኛ መንገዶቹ ጎን ለጎን ክፍት ቦታዎች በአበቦችና በዘንባባ ዛፎች አምረውና ተውበው ሲታዩ መንፈስን ያረካሉ፤ ልብን ይሞላሉ። ለወትሮው በዘንባቦች ውበትና በአበቦች ድምቀት የማትታወቀው አዲስ ዛሬ አይን ማራኪ በሆኑ አፀዶች ደምቃ ለሥራም ሆነ ለኑሮ ምቹ ሆናለች፡፡

እነዚህ ሁሉ ልማቶች ሲከናወኑ ታዲያ ነዋሪውን ታሳቢ በማድረግ ነው። ልማቱ ከመጀመሩ በፊት በአግባቡ በማወያየትና ከተጀመረ በኋላ እንደነዋሪው ፍላጎት የኮንዶሚኒየም ቤትና የቀበሌ ቤት በመስጠት ጭምር ልማቱን ያለምንም ቅሬታ ሕዝቡ እንዲቀበለው ለማድረግ ተሞክሯል። ለግል ቤት ነዋሪዎችም ካሳና ምትክ ቦታ በመስጠት ልማቱ ሁሉንም የሚጠቅም መሆኑን በገሐድ ታይቷል፡፡

የነዋሪዎችን ማኅበራዊ ትስስር ለማስቀጠልም በድጎማ የሚቀርቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በማቅረብ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ዕድል መኖሩም አብሮነታቸውን ለማስቀጠል ምቹ አጋጣሚ ነው። ይህም ልማቱ የማኅበረሰቡ ማኅበራዊ መስተጋብር እንዲቀጥልና በልማቱ ላይ የባለቤትነት ስሜት እንዲፈጥርባቸው የሚያደርግ ነው፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎንም የኮሪደር ልማቱ ታሪካዊ ቦታዎች እንዲሁም ቅርሶችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መከናወኑ አድናቆት የሚገባው ነው። በተቻለ መጠን ነባር የከተማዋ አካባቢዎች ሲፈርሱ ቅርሶች እንዳይፈርሱ ጥንቃቄ በማድረግ መሠራቱ አዲስ አበባ የጥንት ገጽታዋን ሳትለቅ ከዘመናዊው ጋር እንደትዋሓድ አስችሏታል፡፡

በቅርስነት የተለዩ እንደሲኒማ ኢትዮጵያ፣ ሀገር ፍቅር፣ ሸዋ ሆቴል፣ ሲቲ ኮንቬንሽን፣ የሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ ቤት፣ የቀድሞዎቹ ማዘጋጃና ፖስታ ቤት ታድሰው ባሉበት ይቀጥላሉ ተብሏል። ይህም አልፎ አልፎ በአንዳንድ ‹‹አክቲቪስቶች›› ዘንድ የሚነዛውን የሐሰተኛ መረጃ ያከሸፈ ነው፡፡

የኮሪደር ልማቱ እስካሁን ከተሠሩት የልማት ሥራዎች መካከል ማዘጋጃ ቤት፣ መስቀል አደባባይ፣ ወንድማማችነትና አንድነት ፓርክ፣ ሳይንስ ሙዚየም አብርኆት ቤተ መጽሐፍት፣ ጎተራ አቃቂ ቦሌ መንገድ ግንባታ በመሳሰሉ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ላይ ተጨማሪ ውበትን የሚፈጠር ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና ድንገተኛ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን መረጃ እንደሚያመላክተው፤ የመዲናዋ የኮሪደር ልማት ከከተማ ልማትም ባለፈ ለእሳትና ድንገተኛ አደጋ ተጋላጭ የነበሩ ዜጎችን ሊታደግ የሚችል ነው። በተለይም ነባር በሆኑት የከተማዋ ክፍሎች የኤሌክትሪክ ዝርጋታው እጅግ ኋላቀር ከመሆኑ በላይ እጅግ የተወሳሰበና ለአደጋም የተጋለጠ ነው፡፡

በዚህ ላይ ዝናብና የንፋስ ሽውታ ሲያገኘው በቀላሉ የሚበጠስና መብራትም በየአጋጣሚው የሚጠፋበት አካባቢ ነው። ንፋስና ዝናብ ሲመጣ በቀላሉ በኤሌክትሪክ ዝርጋታው ላይ አደጋ ስለሚደርስ እሳት ቃጠሎን የመሳሰሉ በሰዎች ሕይወትና በንብረት ላይ የከፋ አደጋ ሲደርስ ቆይቷል፡፡

በኮሪደር ልማቱ የኤሌክትሪክ መስመሮች ከምድር ውስጥ ስለሚቀበሩ ለዘመናት ሲደርስ ነበረውን አደጋ ሙሉ ለሙሉ የሚያስቀር ነው። ከዚሁ ጎን ለጎንም በየኪሎ ሜትሩ የእሳት አደጋ ማጥፊያ ውሃ ስለተቀበረ በቀላሉ አደጋ ሲደርስ ቀድቶ አደጋውን በቀላሉ መታደግ የሚያስችል ዕድል ፈጥሯል፡፡

በዚህ ረገድ ከቤቶች ግንባታ ጥግግት፣ ከመንገዶች ጥበት፣ ከኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ገመዶች መደራረብ እና ከፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች መደፈን ጋር የሚከሰቱ አደጋዎችንም ለመከላከል እየተከናወነ ያለው የመንገድ ኮሪደር ልማት የሚኖረው አስተዋፅዖ ከፍ ያለ ነው። የኮሪደር ልማቱ ቤቶች በፕላን እንዲገነቡ፣ መንገዶች እንዲሰፉ፣ ዘመናዊ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታና የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች በጥራት እንዲሠሩ የሚያደርግ ነው።

በርካታ አካባቢዎችን ከእሳት ቃጠሎ፣ ከጎርፍ መጥለቅለቅ፣ ከትራፊክ መጨናነቅና ሌሎችም አደጋዎች የታደገ ሁነኛ መፍትሔ ይሆናል ተብሎም ይታመናል። በየዓመቱም በትራፊክ አደጋ የሚቀጠፈውንም ሕይወት ለመታደግ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ይኖረዋል። በጤና ረገድም የሚጫወተው ሚና ቀላል የሚባል አይደለም የውሃ ማስተላለፊያ መስመሮችና የቆሻሻ ማስወገጃ ቱቦዎች የተቀበሩበት ሁኔታ ኋላ ቀርና የጤና ችግርም የሚያስከትል ነው። አብዛኞቹ ውሃ መስመሮች ከቱቦዎች ጋር መሳለመሳ የተቀበሩ በመሆናቸው ከመፀዳጃ ቤት የሚወጣው ፍሳሽ ከሚጠጣው ውሃ ጋር እየተደባለቀ ለከፋ የጤና ችግር ሲዳርግ የቆየ ነው፡፡

አብዛኞቹ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች የተቀበሩት ከከተማዋ ምሥረታ ጋር በተያያዘ በመሆኑ ከማርጀታቸውም ባሻገር አሁን ያለውን የሰው ቁጥር የማስተናገድ አቅም የላቸውም። በዚህም ላይ በየጊዜው በሚሠሩ ግንባታዎች አማካኝነት ፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎቹ ለብልሽት ስለተዳረጉ በአግባቡ ፍሳሽን የማስወገድ አቅም ተስኗቸዋል። በዚህም ምክንያት አካባቢዎቹ በየጊዜው በሚፈነዱ መፀዳጃ ቤቶች የሚጥለቀለቁና አፍንጫ በሚሰነፍጥ ጠረናቸውም የሚታወቁ ናቸው። ይህ ደግሞ ለአስምና ለተለያዩ ተላላፊ በሸታዎች መንስኤ ሲሆን መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡

የኮሪደር ልማቱ ከተሞች በቴክኖሎጂ የዘመኑ እንዲሆኑ እና ተመራጭ የቱሪዝም እና የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንዲሆኑም ያስችላል። ንግድና እና የትራንስፖርት ቀልጣፋ ያደርጋል:: ይህም የዜጎች ሕይወት እንዲሻሻል፣ ከተሞች ለነዋሪዎች ምቹ እንዲሆኑ እና ሀገር እንድትበለጽግ በር ይከፍታል፡፡

በአጠቃላይ በአምስት አቅጣጫዎች እየተከናወነ ያከለው ኮሪደር ልማት ከተማዋን ከመሠረቱ የሚቀይር ነው። ከሁሉም የሚያስደስተው ደግሞ ሥራውን በታያዘለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ለማጠናቀቅ የሚደረገው ርብርብ አግራሞትን የሚፈጥር ነው። አጠቃላይ ያለውን እንቅስቃሴ ለተመለከተ የኮሪደር ልማቱ በታሰበለት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ መገመት አያዳግትም።

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You