ለጥሩ ውጤት – ጠንክሮ ማጥናት

ልጆችዬ እንዴት ናችሁ? ሰላም ናችሁ? ሳምንታችሁ እንዴት አለፈ? ደስ በሚል ሁኔታ እንዳሳለፋችሁ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ልጆችዬ ትምህርት ለሁሉም ነገር መሠረት እንደሆነ ትገነዘባላችሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ወላጆቻችሁ እና አሳዳጊዎቻችሁም፤ ወደ ፊት ትምህርታችሁን ጨርሳችሁ ውጤታማ ዜጋ እንድትሆኑ ወደ ትምህርት ቤት የሚልኳችሁም ይህንን በማሰብ ነው፡፡ ታዲያ እናንተስ ውጤታማ እና ጎበዝ ተማሪ ለመሆን ታነባላችሁ? በርትታችሁ እና ጠንክራችሁ ታጠናላችሁ? ያልገባችሁን ለመምህራን ትጠይቃላችሁ? መልሳችሁ ‹‹እንዴ በሚገባ!›› የሚል እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለንም፡፡

ልጆችዬ የዓመቱ መደበኛ የትምህርት መርሀ ግብር ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት ብቻ ናቸው አይደል የቀሩት? የሰኔ ወር ደግሞ የዓመቱ የመጨረሻ ፈተና እና ውጤት የሚገለጽበት ነው፡፡ እናንተም ዓመቱን በሙሉ ፕሮግራም በማውጣት ስታጠኑ፣ ያልገባችሁን ስትጠይቁ፣ መምህሮቻችሁን በንቃት ስትከታተሉ እንደነበር ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በተለይም የዓመቱ የትምህርት አጋማሽ ላይ ያገኛችሁት ውጤት በትምህርታችሁ የበለጠ እንድትጠነክሩም ሆነ ማሻሻል ያለባችሁን ነገር እንድታሻሽሉ በሚገባ ያግዛችኋል፡፡

ልጆችዬ የትምህርት ዓመቱን በጥሩ ውጤት ለማጠናቀቅ ያላችሁ ጥቂት ቀናት ብቻ ናቸው፡፡ እናንተም በርትታችሁ በጥናት እያሳለፋችሁ እንደሆነ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እናም እናንተ እንዳታጠኑ የሚያዘናጓችሁን ነገር ማድረግ የለባችሁም። ለምሳሌ ቴሌቪዥን ማየት፣ ጌም መጫወት፣በጥናት ሰዓት መጫወት እና መረበሽ በፍጹም የለባችሁም፡፡ ልጆችዬ ማወቅ ያለባችሁ ነገር ምን መሰላችሁ? አሁን መደበኛው ትምህርት ሊዘጋ ጥቂት ቀናት ብቻ ስለቀሩ ጨዋታውም ይሁን ሌሎች ነገሮችን በእረፍት ጊዜያችሁ መከወን እንደምትችሉ እና አሁን ከሁሉም ነገር ቅድሚያ መስጠት ያለባችሁ ለትምህርታችሁ ብቻ መሆኑን ነው፡፡ እናም ልጆችዬ ጥናት የሚጀመረው ፈተና ሲደርስ ብቻ አይደለም፡፡

ልጆችዬ እስቲ ገምቱ? ዓመቱ መጨረሻ ላይ ማን ጥሩ ውጤት በማምጣት የሚያጠናቅቅ ይመስላችኋል? ይህንን መገመት ይከብዳል አይደል? መገመት አይከብድም፡፡ እንደውም በጣም ቀላል ነው፡፡ ‹‹እንዴት ?›› ካላችሁም፤ ሁልጊዜ የሚያጠና፣ መምህራን ሲያስተምሩ በሚገባ የሚከታተል፣ በክፍል ውስጥ የማይረብሽ፣ በክፍል ውስጥ መምህራን ሲያስተምሩ በንቃት የሚሳተፍ ጥያቄዎችን የሚመልስ፣ ያልገባውን የሚጠይቅ፣የፈተና መመሪያዎችን በሚገባ አንብቦና ተረድቶ ትክክለኛውን የሚመልስ እና ሌሎችንም ተግባራዊ የሚያደርግ ተማሪ ዓመቱ መጨረሻ ላይ ጥሩ ውጤት ለማምጣት ምንም የሚከለክለው ነገር የለም፡፡ ስለዚህም ልጆች ይህንን የሚያደርግ ተማሪ ዓመቱ መጨረሻ ላይ ጥሩ ውጤት አስመዝግቦ በትምህርት ቤቱ እና በወላጆቹ እስከመሸለም ይደርሳል፡፡

መቼም ልጆችዬ ስለ ጥናት እና ንባብ ሲነሳ የወላጆች ድጋፍ እና ኃላፊነት አብሮ ይነሳል፡፡ ለምን መሰላችሁ ልጆች? እናንተ እንድታጠኑ፣ ክትትል እና ድጋፍ ማድረግ እንዲሁም አመቺ ሁኔታዎችን መፍጠር ከወላጆች የሚጠበቅ ተግባር በመሆኑ ነው፡፡ እነርሱ ይህንን ማድረጋቸው ጥቅሙ ለእናንተ ብቻ ሳይሆን ለወላጆችም ጭምር ነው፡፡ እንዴት? ካላችሁ፤ ምላሹም የትኛውም ወላጅ ልጆቹ ውጤታማ ሆኖ ማየት ስለሚፈልግ ነው፡፡ ልጆችዬ ታዲያ እናንተም ቤተሰቦቻችሁ በተለያየ ምክንያት ድጋፍ እያደረጉላችሁ ካልሆነ ድጋፋቸው እንደሚያስፈልጋችሁ በግልጽ መናገርም ይኖርባችኋል፡፡

ልጆችዬ ከዚህ ቀደም ፈተና ስትቀበሉ የመጀመሪያ ሥራችሁ መሆን አለበት ያልናችሁ ምን ነበር? ‹‹ራሳችሁን መመዘን፡፡›› ብላችሁ መለሳችሁ? በጣም ጎበዞች፡፡ አሁንም ቢሆን የዓመቱን ማጠናቀቂያ ውጤታችሁን ከተቀበላችሁ በኋላ ምን ትምህርት ላይ ደካማ እና ጠንካራ እንደነበራችሁ፣ የአጠናን ስልታችሁ ምን ይመስል እንደነበር መፈተሽ ፣ በክፍል ውስጥ ያላችሁ ተሳትፎ እስከምን እንደነበር ፣ ለፈተና የምታደርጉት ዝግጅት እና ሌሎች ነገሮች በማጤን ጥሩ ውጤት ያመጣችሁ በዛው መቀጠል ይኖርባችኋል፡፡ ጥሩ ውጤት ላላመጣችሁ ተማሪዎች ደግሞ ውጤታችሁን እንድታሻሽሉ በሚገባ ያግዛችኋልና እነዚህን ተግባራዊ ማድረግ ይኖርባችኋል፡፡

ልጆችዬ በቀጣይ ሳምንታት የስድስተኛ ክፍል እና የስምንተኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና እንደሚሰጥ ሰምታችኋል አይደል? ተፈታኝ የሆናችሁ በፈተና ወቅት መያዝ ያለባችሁን እና መያዝ የሌለባችሁን ነገር በየትምህርት ቤቶቻችሁ መመሪያ እንደተሰጣችሁ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ የዘንድሮ ተፈታኝ የሆናችሁም ተማሪዎች ያለምንም ጭንቀት እና ፍርሀት ፈተናውን መውሰዳችሁ፤ ጥሩ ውጤት እንድታመጡ በሚገባ የሚያግዛችሁ መሆኑን በመረዳት በጥንቃቄ ፈተናችሁን መሥራት ይኖርባችኋል፡ ፡ በእኛ በኩል ከወዲሁ መልካም ፈተና እንዲሆንላችሁ ተመኝተናል፡፡ ልጆችዬ የትምህርት ዓመቱን ጥሩ ውጤት እንደምታመጡ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ለዛሬ በዚሁ አበቃን፡

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You