ሕይወት ተደጋጋሚ ናት:: አንዳንድ ጊዜም አሰልቺ ናት:: የእኛ ስሜት ደግሞ ከፍም ዝቅም ይላል:: ስሜት ደግሞ ወሳኝ ነው:: አይተህ ከሆነ በጣም ደስ ያለህ ቀን ደስ የሚል ቀን ታሳልፋለህ:: ደስ ብሎሃላ! ከሰዎች ጋር ትግባባለህ፣ ስራው ይሰራል፣ የሚገርም ቀን ታሳልፋለህ:: የደበረህ እለት ግን ቀኑ አይገፋም:: ምን አይነት አስቀያሚ ቀን ነው ትላለህ:: የምትሰራው አይጥምህ፣ የምትበላው አይጥምህ፣ በቃ! ቀኑ አስጠሊታ ሆኖ ይውላል:: ሕይወት በእንደዚህ አይነት ቀኖች የተሞላች ናት:: ታዲያ ‹‹እንዴት አድርጌ ነው ጥሩ ስሜት ውስጥ የምገባው? መጥፎ ስሜቴን የማሸንፈው?›› የሚለው የብዙ ሰዎች ጥያቄ ነው:: እንሆ መልሱ….
‹ሙድህ› እስኪመጣ አትጠብቅ:: አንዳንዴ ስራውን ቀጥታ መጀመር ራሱ ‹ሙድህ› ውስጥ ሊያስገባህ ይችላል:: ዝምብለህ ስራውን ጀምር:: ስፖርት ለመስራት የሚያነቃቃህን አትፈልግ:: የስፖርቱን ልብስ መልበስ ስትጀምር፣ ከአልጋህ ስትወርድ ሳታውቀው ልዩ ስሜት ይቆጣጠርሃል:: አነቃቂ ነገር አትጠብቅ:: ስራው ራሱ ያነቃቃህ:: አለበለዚያም ጥሩ ሙድ ላይ ስሆን እኮ ነው የምሰራው ካልክ ሁሉም እንደዛ ይሰራል:: አንተ እየደበረህ ስራውን ጀምረው:: ስሜትህ ይቀየራል::
በቀዝቃዛ ሻወር ለመታጠብ ፈልገህ ፈርተህ ታውቃለህ መቼም:: ‹‹ኸረ በጣም ብርዱ ያስፈራል›› ልትል ትችላለህ:: የግድህን ከሆነ ግን እየተጠጋህ ትገባለህ:: ቀስ ብለህ እየፈራህ ውሃውን ትከፍተዋለህ:: ጠብ ብሎ ገላህ ላይ መውረድ ይጀምራል:: የመጀመሪያዎቹ ያስፈሩሃል:: ሰውነትህን ሊበርደውና ሊያንቀጠቅጠው ይችላል:: ከዛ በኋላ ግን ትለምደዋለህ:: በደምብ አድርገህ ትታጠባለህ:: እንደውም መውጣት ሁሉ አትፈልግም::
አንዳንድ ነገሮች ደፈር ብለህ ስታደርጋቸው ነው ስሜት የሚሰጡህ:: መጥፎ ስሜት እንዲሰማህ ያደረገህ በተመሳሳይ ችግር መጨነቅህ ሊሆን ይችላል:: አዕምሯችን በቀን ውስጥ ከሚያስባቸው ሰማኒያ ሺ ሀሳቦች መካከል አብዛኞቹ ተመሳሳይ ናቸው:: ግማሾቹ ስለነገ ፍራቻ ናቸው:: ግማሾቹ ስለትናንት ስተቶቻችን ወቀሳና ቁጭቶች ናቸው::
አንዲት ልጅ ደመወዟ 30 ሺ ብር ነው:: የሚገርመው ግን ሁልግዜ የምትንገበገብበት ነገር አላት:: ከጥቂት ዓመት በፊት አንድ ጓደኛዋ የተበደራትን 3 ሺ ብር አልሰጣትም:: የእርሷ ገንዘብ 30 ሺ፤ እርሷ ሁሌ የሚያንገበግባት 3 ሺ ብር ነው:: በሕይወታችን ውስጥ በጣም ትናንሽ የሚባሉ ነገሮች ናቸው ስሜታችንን የሚያበላሹት፤ የሚበክሉት:: ግን እኮ አስቡት እንዴት ነው ውቅያኖሱን ጠብታ ደም የሚያቀላው? በፍፁም አያቀላውም:: የእኛም ስሜት ጠንካራ መሆን አለበት:: ተራ ነገር የሚያሸብረን፣ ተራ ነገር ስሜታችንን የሚቀይረው መሆን የለበትም::
በሕይወት ውስጥ ከባዱ ነገር የሚፈልጉትን ማጣት ነው:: ከሁሉም ነገር በላይ ግን እጅግ ከባዱ ነገር የሚፈልጉትን አግኝቶ ማጣት ነው:: እጃችን ላይ የሌሉን ነገሮች ወይም የጎደሉንን ጉድለቶች በማሰብ ግዜ የምናጠፋ ከሆነ ያገኘናቸውንም ልናጣ እንችላለን:: ‹‹የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች›› ይባል የለ፤ በዚህ ዓለም በነፃ ያገኘናቸው ነገሮች ብዙ ናቸው:: ለምን ይከፋሃል ታዲያ?፣ ለምን መጥፎ ስሜት ውስጥ ትገባለህ? ራስህን መቀየር የምትፈልግ ከሆነ፣ ስሜትህን መቀየር የምትፈልግ ከሆነ ያደረካቸውን መልካም ነገሮች አስብ:: ትላንትን አስብ:: ያሳለፍከውን አስብ::
አንተ እኮ በቀላሉ እዚህ አልደረስክም:: ብዙ ዋጋ ከፍለሃል:: ብዙ የፍቅር ግዜ፣ ብዙ የስራ ግዜ፣ ብዙ የትምህርት ግዜ አሳልፈሃል:: ውጣውረዱስ ቀላል ነበር እንዴ ? እንተን መሆን ይጠይቃል እኮ:: ለቤተሰቦችህ ደርሰሃል:: ለምትወዳቸው ሰዎች ብዙ ዋጋ ከፍለሃል:: ዝም ብለህ እኮ አልኖርክም:: እግረ መንገድህን እዚ ጋር አልደረስክም:: ብዙ ነገር አሳልፈሃል:: ብዙ ከባድ ግዚያትን አንተ ስለሆንክ ችለሃቸው ተወጥተሃቸዋል:: ወኔህንና ስሜትህን ሁሉ ተቆጣጥረህ ለዛሬ ቀን ደርሰሃል:: ዛሬ ለምን ይከፋሃል:: ለምን መጥፎ ስሜት ውስጥ ትገባለህ:: ለማን ብለህ ትጨነቃለህ::
ስሜትህን ቀይረው:: ራስህን ለውጠው:: ስሜትህ ሲቀየር ድርጊትህም አብሮ ይቀየራል:: ተግባርህ ይቀየራል:: ወዳጄ! ስሜት በጣም ወሳኝ ነው:: መልካሙን አስብ:: ትላንትን አስብ:: እንዴትም አድርገህ ግን ስሜትህን ቀይረው:: በዚህ ስሜት ውስጥ እንዳትቀጥል:: የዛሬው ቀን አዲስ ነው:: የዛሬውን ቀን ከዚህ በፊት አላየኸውም:: አንተ ግን ትላንት ላይ ተቸንክረሃል:: ትላንትን እየኖርክ ነው:: ደስታህን ማንም አይሰጥህም:: ምንጩ አንተ ጋር ነው:: ያንተ ስሜት እንዲቀየር ምንም ነገር መቀየር የለበትም:: አንተ ተቀየር!
የሆነ ነገር ጀምረህ ልታቆም ወይም ተስፋ ልትቆርጥ ስትል ለምን እንደጀመርክ አስታውስ:: አየህ አንዳንዴ ከጥሩ ስሜት ውስጥ የሚያወጡህን ነገሮች የምታሸንፈው ስለትልቁ መድረሻህ ስታስብ ነው:: ሁላችንም ለፍተን፣ ተምረን፣ ወይ ሰርተንበት፣ ንብረትና ጎረቤት ገንብተን መጨረሻ ላይ የምንፈልገው ትልቁ ነገር የአዕምሮ ሰላምና ጠንካራ መንፈሳዊ ሕይወት ነው:: በመጨረሻ የምንወርሰው ርስታችን ፍቅርና ደስታ ነው:: ስለዚህ የጀመርነውን መቼም አናቆምም:: ስሜትህን ግን ሁሌም ትቆጣጠረዋለህ:: ሁሌም ደስተኛ ትሆናለህ:: ወደ ጥሩ ሙድ ስለሚያስገቡ ነገሮች ታስባለህ:: መልካሙን ሁሉ ታስባለህ::
ሕይወት አጭር ናት ለምን ትቆጫለህ? ለምን ያለፈው መጥፎ ነገር ያሳስብሃል? መልካሙን አስብ:: ስሜትህን ቀይረው:: ወደ ድርጊት ግባ:: ተግባር ሕይወትህን ይቀይረዋል:: ከተግባር በፊት ግን ስሜትን መቀየር ወሳኝ ነው:: አንድ ሰውዬ ‹‹በጣም የሚያስቅ ቀልድ አለኝ›› ብሎ ለሶስት ጓደኞቹ ቀልዱን አወራላቸው:: ጓደኞቹም በሳቅ ወደቁ:: በጣም ተመቻቸው ቀልዱ:: ከዛ ሰውዬው ‹‹አንድ ሌላ ቀልድ ልጨምርላችሁ›› አለና የመጀመሪያውን ቀልድ ደገመው:: ጓደኞቹ ፈገግ አሉና ዝም አሉ:: ‹‹ቆይ! አንድ ደግሞ አለችኝ›› አለና ሌላ ቀልድ ብሎ ራሱኑ ደገመላቸው:: አሁን ኮስተር አሉ:: ‹‹ምነው! በዛ›› አሉ:: በሶስተኛውም አንድ የመጨረሻ ብሎ ለሶስተኛ ግዜ ራሱኑ ቀልዱን ደገመው:: ይህን ግዜ ጓደኞቹ መሳደብ ጀመሩ:: ‹‹ምነው አንተ ዝም አሉኝ ብለህ ነው እንዲህ የምትጫወትብን›› ብለው ተበሳጩበት::
ምን አላችሁ መሰላችሁ ‹‹አያችሁ አይደል አንዱ ቀልድ አንዴ ነው የሚያስቃችሁ:: ደጋግማችሁ አትስቁበትም:: ታዲያ አንድ ችግር ለምን ሶስት ግዜ ያናድዳችኋል፣ ለምን ብዙ ግዜ ያቃጥላችኋል፣ ለምን ትናደዳላችሁ?›› አላቸው:: በሕይወት ውስጥም እንደዛ ነው:: የሚያናድዱ፣ የሚያበሳጩ ነገሮች አንድ ናቸው:: ተመሳሳይ ናቸው ግን ሁሌ ያንገበግቡናል::
ለመጀመሪያ ግዜ ፍቅር ሲይዝህ የተሰማህ ልዩ ስሜት፣ የመኖር ጉጉትና እርሷን የራስህ ለማድረግ የነበረህን ጥልቅ ፍላጎት አስበው እስኪ:: እርግጠኛ ነኝ የሆነ ውርር የሚያደርግ ደስታ ነበረው:: አየህ! አሁንም እየኖርከው ያለውን ሕይወት፣ እየኖርከው ያለውን ኑሮ የምታፈቅራትን ሴት አግኝተህ እንደመኖር ብታጣጥመው በዚህ ምድር እንዳንተ ደስተኛ የሆነ ሰው አይኖርም:: ወዳጄ! አሁን የደረስክበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ ዋጋ ከፍለሃል::
እመነኝ! በየደቂቃው እጅህ ላይ ባለው ነገር ጥግ ድረስ መደሰት አለብህ:: አስተማሪዋ ተማሪዎቿን በምሳሌ እያስተማረች ነው:: አንዱን ተማሪ መረጠችና ‹‹እስኪ ይህን ጥያቄ መልስልኝ፤ መደመር ነው የዛሬ ትምህርታችን ስለዚህ እኔ አሁን ሁለት ማንጎ አውጥቼ ብሰጥህ፤ እንደገና ደግሞ ሁለት ማንጎ ብጨምርልህ ስንት ይሆናል ?›› አለችው:: ልጁ አሰበና ‹‹አምስት ማንጎ›› አላት:: መምህሯ አልገባውም ብላ አሰበችና ‹‹እየውልህ! ሁለት ማንጎ እኮ ሰጠውህ፤ ከዛ ደግሞ ሌላ ሁለት ማንጎ ጨመርኩልህ እስኪ ደምራቸው›› አለችው:: ‹‹እኮ! አምስት ማንጎ ይሆናል›› አላት ተማሪው::
መምህሯ በስጨት አለች:: ‹‹እሺ በብርቱካን ላስረዳህ›› አለችና ‹‹ሁለት ብርቱካን ሰጠውህ፤ ሌላ ሁለት ብርቱካን ጨመርኩልህ ስንት ብርቱካን ይሆናል አለችው:: ተማሪው አሰበና ‹‹አራት ብርቱካን›› አላት:: ደስ አላት መምህሯ:: ገባው አለች:: ‹‹ስለዚህ አሁን በማንጎ ውሰደውና ሁለት ማንጎ ብሰጥህና ሁለት ማንጎ ድጋሚ ብጨምርልህ ስንት ይሆናል›› አለችው:: ተማሪው አሰበና አሁንም ‹‹አምስት›› አላት:: መምህሯ ተበሳጨች:: ‹‹ምን ሆኖ ነው ይሄ ልጅ አልገባውም እንዴ? ቅድም ለብርቱካኑ አራት አልከኝ ለማንጎ ሲሆን ለምን አምስት ትለኛለህ›› አለችው:: ልጁ መለሰ ‹‹ቦርሳዬ ውስጥ አንድ ማንጎ ስለያዝኩ ነው አላት::
በሕይወት ውስጥ እነዚህ ሰዎች ሁለቱም ትክክል ናቸው:: ልጁም ልክ ነው:: ቦርሳው ውስጥ ማንጎ ነበር:: መመህሯም ልክ ነበረች:: የምታውቀው አራት ማንጎ እንዳለ ነው:: በሕይወትም እንደዛ ነው:: አንዳችን በአንዳችን ጫማ ውስጥ ካልገባን በስተቀር የማይገቡንና የማንረዳቸው ስሜቶች አሉ:: ስለዚህ ሰዎች ሲያናድዱን፤ ከሰዎች ጋር ስንጋጭ እርሱ ልክ ቢሆንስ ብለን በእርሱ ቦታ ሆነን ማሰብ አለብን:: ስሜት ቀላል ነገር አይደለም:: ስሜታችንን በአንዴ ልንጎዳው አይገባም:: ‹‹አልተረዱኝም እኮ!፣ ማንም አይሰማኝም!›› ማለት የለብንም::
ያለህበትን ሁኔታ ቀላልም፤ ከባድም የሚያደርገው ስሜት ነው:: አስበው እስኪ በጣም የሚያስደስት ሁኔታ ውስጥ ሆነህ የምታደርጋቸው ነገሮች እኮ ሁሌም ትርጉም ይሰጡሃል:: ከባድ የሚባለውን ስራ ሳይደክምህ በሚገርም ሞራል ትሰራዋለህ:: አየህ! ብዙ ነገር ያሳኩ ሰዎች ደስተኛ ናቸው:: እንደሚችሉ ያምናሉ:: ሁሌም የሚያበረታ ኃይል ከውስጥ ይገፋቸዋል:: ማንም አይደለም ደስታን የሚሰጣቸው:: ማንም አይደለም ጥንካሬ የሚሰጣቸው:: ውስጣዊ ስሜት ነው የሚያበረታቸው:: የሚያነቃቸው:: አንተም ውስጥ ያ ኃይል አለ::
አሁን ራሱ ምንም አይነት ስሜት ውስጥ ብትሆን እስኪ ወደምትፈልገው ኑሮ፣ ሀብት፣ ደስታ፣ የአእምሮ ሰላም እየተጓዝክ እንደሆነ አስብ እስኪ:: ስሜትህ እንደሚቀየር እርግጠኛ ነኝ:: ወዳጄ! እንደ ንፋስ ሽው ብሎ ለሚያልፈው እድሜህ ስትል ለምንድን ነው መጥፎ መጥፎውን የምታስበው? ለምንድን ነው ከመጥፎ ስሜት የማትወጣው? ስሜትህን መቀየር አለብህ:: እሱ ነው ወደ ድርጊት የሚያስገባህ:: እሱ ነው ሙሉ ጉልበት የሚሰጥህ:: ከሰው በላይ የሚያደርግህ፣ አቅምህን እንድትጠቀም የሚያስችልህ ስሜትህ ነው፤ ሙድህ ነው:: ዋናው መውደቅህ አይደለም:: ወድቀህ መነሳትህ ነው:: ማጎንበስህ አይደለም:: መልሰህ ቀና ማለትህ ነው:: ማዘንህ አይደለም እንደገና መሳቅህ ነው::
ወዳጄ! አትርሳ የዋንጫ ቡድንም እኮ አንዳንዴ ይሸነፋል:: ለግዜው ነው እንጂ ያንተ ቦታ ከፍታ ነው፣ ያንተ ርስት ደስታ ነው:: ያንተ ርስት ፍቅር ነው:: አንዳንዴ ዋጋ ቢስ እንደሆንክ፣ የትም እንደማትደርስ፣ መቼም ደስተኛ ለመሆን እንዳልታደልክና እንደማትረባ ሊሰማህ ይችላል:: ሁሉም ሰው እንደዛ ይሰማዋል:: የሆነ ቀን አለ የሚደብርህ፤ የሚከፋህ:: ምንም ነገር ከመሬት ተነስቶ የማይጥምህ ቀን አለ:: ግን አንድ ነገር አድርግ:: በየቀኑ ትናንሽ መስጠቶችን ተለማመድ:: መስጠት! ግዜህን ይሆናል፤ አልያ ገንዘብህን ወይ ጉልበትህን፣ ሃሳብህንም ሊሖን ይችላል:: ብቻ ስጥ! ያረጋጋሃል::
ለተቸገረ ገንዘብ መርዳት ብቻ አይደለም መስጠት:: የከፋው ሰው ካለ የሆዱን ሲነግርህ ግዜ ሰጥተህ ማድመጥ ብቻ ለዛ ሰው ሰላም ሲሰጠው ታይና ልዩ ስሜት ይሰማሃል:: ጉልበት የከዳው፣ አቅም ያነሰው የምታውቀው ሰው ካለ ጉልበትህን ለደቂቃዎች አውሰው:: ታላቅ ስጦታ እንደሰጠኸው አስቦ ሲያመሰግንህ ይውላል:: ይህን ስታደርግ ‹‹እኔ እኮ የማልረባ ነኝ›› የሚለው ስሜትህ ጠፍቶ ማንነትህ በራስ አይምሮ ገዝፎ ይታይሃልና ለዚህ ክብር ያሰብክ ያሰብከኝ አምላኬ ተመስገን ትላለህ:: ወዳጄ! እንዳትጠራጠር ለክብር ነው የተፈጠርከው፤ ስሜትህን አክብረው:: ለሰዎች ስጥ ለማንም አታንስም::
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 1/2016 ዓ.ም