
በአፈጣጠሩ የሙዝ ተክል የሚመስለው “እንሰት” በኢትዮጵያ ብቻ ለምግብነት የሚውል ሰብል ነው። ከእንሰት ስር የሚወጣው ቆጮ በዳቦ መልክ ሲዘጋጅ፣ ቡላው በገንፎ መልክ ለምግብነት ይውላል። የእንሰት ተረፈ ምርት የሆነው ቃጫም ለግንባታና ለኢንዱስትሪዎች ግብዓትነት የሚውል ነው። እንሰት በንጥረ ነገር ይዘቱ የበለጸገ መሆኑንም በሰብሉ ላይ ምርምር ያካሄዱ ምሁራን ይናገራሉ።
የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም ዓመቱን ሙሉ አረንጓዴ ሆኖ በመቆየት አቅሙም ከሌሎች ሰብሎች የተለየ ባህሪው መሆኑ ይነገርለታል። በአመዛኙ በሀገራችን ደቡባዊ አካባቢዎችና በኦሮሚያ የተወሰኑ አካባቢዎች የሚዘወተረው እንሰት በርካታ የጤና ጥቅም ያለው፣ ብዙ ቁጥር ባለው ማኅበረሰብ ዘንድም የሚዘወተር ሰብል ትልቅ ሥፍራ ያለው ተክል ቢሆንም፣ የሚገባውን ያህል ትኩረት አለማግኘቱን በዘርፉ ምሁራን ዘንድ ሲነገር ይሰማል።
የአዘገጃጀቱ ሂደት የእናቶችና ሴቶች አቅም የሚፈትን መሆኑም ሰብሉ በስፋት እንዳይመረት ተግዳሮት መሆኑም ይነሳል። ወይዘሮ ታሪኳ ተገኝ፣ ከጉራጌ ዞን የመጣች እናት ስትሆን እንሰት በተለይም በደቡብ የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተወዳጅ የሰብል አይነት መሆኑን ትናገራለች።
የእንሰት ውጤቶችን ተመጋቢ የሆኑ ሰዎች በአካላዊ በጥንካሬያቸው ይለያሉም ትላለች። ወይዘሮ ታሪኳ እንደምትለው ቆጮና ቡላ በብዙ ማኅበረሰብ ዘንድ ተወዳጅና ተፈላጊ የምግብ አይነቶች ቢሆኑም የአዘገጃጀት ሂደታቸው ግን እጅግ አድካሚ ነው ትላለች።
ዛሬም የእኔ እናት እንሰትን በጣም አስቸጋሪና አድካሚ በሆነ ሂደት እያዘጋጀት ኑሮዋን ትገፋለች ያለችው ወይዘሮ ታሪኳ፤ እንሰት የእናቶችና ሴቶችን ሳያደክም በቀላሉ መዘጋጀት የሚቻልበት ሁኔታ ቢመቻች፣ ቆጮና ቡላ በከተማና በሌሎችም አካባቢዎች የተለመደ ምግብ እንዲሆን ምኞት እንዳላት ገልጻለች።
በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ የሰብል ምርምር ዳይሬክተር ፍቃዱ ጉርሙ (ዶ/ር) እንሰት በሀገራችን ትልቅ ስፍራ ያለው ሰብል መሆኑን ይናገራሉ።
እንደ እርሳቸው ገለጻ እንሰት ከምግብ ይዘቱ አንጻር፣ በጣም በርካታ ጥቅም ያለው፣ ብዙ ሕዝብም የሚጠቀምበት የሰብል አይነት ነው። የእንሰት ተክል በተለያዩ ሀገራት ያለ ቢሆንም ለምግብነት የሚውለው ግን በሀገራችን ኢትዮጵያ ብቻ ነው። ይህ በምግብ ይዘቱ የበለጸገ ሰብል በሀገራችን የክፉ ቀን ደራሽ ተብሎም ይጠራል።
የታሪክ መጻፍት እንደሚጠቁሙት፣ ሀገራችን ድርቅና ረሀብ በገጠሟት ጊዜያቶች በተለይ በደቡብና በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች እንሰትን በመመገብ እነዚያን ጊዜያቶች አሳልፈዋል።
ከዓመታት በፊት እንሰት 25 ሚሊዮን ሕዝብ እየመገበ እንደሚገኝ የሚገልፁ መረጃዎች መኖራቸውን ያነሱት ፍቃዱ (ዶ/ር)፣ አሁን ላይ ግን ይህ ቁጥር ወደ 40 ሚሊዮን ያድጋል የሚል እሳቤ መኖሩን ይጠቅሳሉ።
እንሰትን “ከምግብነትም በላይ ነው” በማለት የገለጹት ዶ/ሩ፣ ሰብሉ ማኅበረሰብን በማስተሳሰርም ጭምር ትልቅ የማኅበረሰብ ዋልታ ነው ብለዋል። በአንዳንድ አርብቶ አደር አካባቢዎች የከብት ብዛት የኑሮ ደረጃ መለኪያ እንደሆነው ሁሉ ወደ ደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብና ኦሮሚያ የተወሰኑ አካባቢዎች “ስንት እንሰት አለው?” የሚለው ነው ትልቅ ዋጋ ስለሚሰጠው የኑሮ ደረጃ መለኪያ መሆኑን አንስተዋል።
ፍቃዱ (ዶ/ር) እንዳብራሩት፣ ሰብሉ ይህን ያህል ቦታ ያለው ሆኖ እያለ፣ እስካሁን ድረስ ግን የሚገባውን ያህል ትኩረት ያገኘ አልነበረም። እንሰትን ስትራቴጂክ ሰብል የማድረግ እንቅስቃሴ የተጀመረው በቅርብ ጊዜ ነው። በዚህ ሂደት እንሰትን በስፋትና በተሻለ የአዘገጃጀት ሂደት ለማምረት ተግዳሮት የሆኑ ጉዳዮች ተለይተዋል ።
ከእነዚህ ተግዳሮቶች መካከል የእንሰት አጠውልግ በሽታ አንዱና ለረጅም ጊዜ የቆየው ችግር ነው። ለዚህም መፍትሔ ይሆን ዘንድ በሽታን መቋቋም የሚችሉ ዝርያዎችን የማውጣት ጥረት እየተደረገ ነው። በተጨማሪም አርሶ አደሩ ራሱ በለመደው መንገድ በሽታው ከአንዱ ወደ ሌላ እንዳይተላለፍ ጥንቃቄን እንዲያደርግ በተሻለ ሁኔታ የማስተማር እንዲሁም አርሶ አደሩ በበሽታው የተጠቁ እንሰቶችን በመቅበር ወይም በማቃጠል እንዲያስወግድ ትልቅ የህብረተሰብ ንቅናቄዎች ተካሂደዋል ይላሉ።
ዳይሬክተሩ ከጠቀሷቸው ችግሮች መካከል የእንሰት አዘገጃጀት አስቸጋሪ መሆኑ አንዱ ነው። እናቶችና ሴቶችን ለወገብ ህመም የሚዳርገውን የእንሰት አዘገጃጀት በማሽን በመተካት የእናቶችን ድካም ለማስቀረትም እንዲሁ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው።
ከአዘገጃጀቱ ጋር በተያያዘ ያለውን አስቸጋሪ ሂደት ለመቀየር፣ አዘገጃጀቱን ዘመናዊ ማድረግ፣ የተሻለ አይነት የእንሰት አፋፋቅ ልምድ ካላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር እርስ በእርስ ልምድ እንዲካፈሉ ማድረግ ከመፍትሔዎቹ መካከል ይጠቀሳሉ።
ዘመናዊ ማሽነሪዎችን ከማምረት አንጻር፣ በሀገራችን በሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ተቋማትና ምርምር ማዕከላት የሚገኙ ተማሪዎች ቆጮ መፋቅ፣ ቡላ መጭመቅና ቃጫ ማውጣት የሚችሉ ማሽኖችን እየሠሩ መሆናቸውን አንስተዋል። በዚህ መስክ እየተሠሩ ያሉ የምርምር ሥራዎች ጥሩ ውጤት እያሳዩ ናቸው ያሉት ፍቃዱ (ዶ/ር ) የተሻለውን መርጦ ወደ ማስፋፋት ለመግባት ከማዕከላቱ ጋር እየሠራን ነው ብለዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ያነጋገርነው ወጣት ዲንቃ ተሾመ በየካ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን የእንሰት መፋቂያ ወይም እንሰት ፕሮሰሲንግ ማሽን ሠርተዋል። ማሽኑ ሙሉ በሙሉ በመንግሥት በቀረቡ መሣሪያዎች የተዘጋጀ መሆኑን ገልጾ፣ እናቶች ከእንሠት የሚዘጋጁ ምግቦችን ለማዘጋጀት የሚያወጡትን ድካም የሚያቃልል እንደሆነ ተናግሯል። ማሽኑ ቆጮ፣ ቡላ እና ቃጫን ለየብቻ ለይቶ ማውጣት የሚያስችል መሆኑን የተናገረው ወጣቱ፤ ከ75 ሺ ብር እስከ 90 ሺህ ብር የዋጋ ተመን እንደወጣለትና ክፍያውን በሶስት ጊዜ ከፍሎ መጨረስ የሚያስችል እንደሆነ አስታውቋል።
ፍቃዱ (ዶ/ር)፣ ምንም የሚጣል ነገር የሌለው እንሰትን ስትራቴጂክ ሰብል ለማድረግ ምን እናድርግ? በሚል ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር፣ አንድ ዓመት ተኩል የሆነው ሰነድ ብሔራዊ የእንሰት ፈላግሺፕ ፕሮግራም እያዘጋጁ በመሆናቸው የሚገባውን ትኩረት እንዲያገኝ እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
ዮርዳኖስ ፍቅሩ
አዲስ ዘመን ሰኔ 1/2016 ዓ.ም