በምስክር ጌታነው ሚዲያና ፕሮሞሽን የተዘጋጀው የግንቦት ወር መድረክ መሪ ሃሳቡ ‹‹መፍትሔው ኢትዮጵያዊነት ነው›› የሚል ነበር። ተናጋሪዎቹም መፍትሔው ኢትዮጵያዊነት እንደሆነ ተናግረዋል። በመድረኩ ላይ የቀረቡ ዲስኩሮችን እያስነበብናችሁ ቆይተናል፡ በወቅቱ ከነበረው መድረክ የመጨረሻ የሆነውን የመጋቢ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁን እናስነብባችሁ።
እኔ ኳስ ብዙ አልወድም። የማል ወደው ኃጢያት ስለሆነ ሳይሆን ዓይነሥውር ስለሆንኩ ነው። ኳስ ለማየት ዓይን ይጠይቃል። ኤፍሬም የማነ እና ፍቅር ይልቃል የሚባሉ የስፖርት ጋዜጠኞች የሚያቀርቡት አንድ የኳስ መርሐግብር አለ። ስሰማው የኪነ ጥበብ ፕሮግራም ነው የሚመስለኝ። ከቤታቸው አቁላልተው ጨርሰው ነው የሚያመጡት። ብዙ ጋዜጠኞች ግን አየር ላይ ከወጡ በኋላ ነው የሚያቁላሉት። ነገሮችን እንዲህ አቁላልተን እና ራሳችን ጨርሰን ብናወራ የተሻለ ነው ብዬ አምናለሁ።
አንድ የንስሃ አባት ጀማሪ ክርስቲያን የንስሃ ልጅ ነበረቻቸው። ጀማሪ በየቦታው አስቸጋሪ ነው። ጀማሪ ባለሥልጣን ስብሰባ ያበዛል። እና ያች! ልጅ ዘወትር እየመጣች ህልም አየሁ ትላቸዋለች። ሰውየው ስልችት ብሏቸው ‹‹የኔ ልጅ እባክሽ መጀመሪያ ተኚ›› አሏት። አልተኛችም፤ ብትተኛ ህልም አታይም ነበር።
አላርም (ማንቂያ) ሁላችሁም ታውቃላችሁ። አንዳንድ ሰዎች ሌሊት መንቃት ይፈልጉና ‹‹አላርም›› ይሞላሉ። አላርሙ እንግዲህ ሰውየው ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ላይ ነውና ልተወው አይልም፤ ሰዓቱን ጠብቆ ይጮሃል። ሰውየውም የሞላው እንዲያነቃው ነው። እንቅልፍ ሲያሸንፈው ግን ራሱ የሞላውን አላርም ‹‹አፈር ያስበላህ›› ይልና አጥፍቶት ይተኛል።
አገር በየጊዜው አላርሞች ይኖ ሯታል። አጼ ኃይለሥላሴ በ1953 ዓ.ም መንግስቱ ንዋይ እና ግርማሜ ንዋይ የሚባሉ አላርሞች ተነስተውላቸው ነበር። ግን ከእንቅልፋቸው ከመንቃት ይልቅ አላርሞችን አጠፏቸው፤ ትልቅ ስህተት ሰሩ። ደርግም በየጊዜው አላርሞች ተነሱበት፤ በእነዚያ አላርሞች ከመንቃት ይልቅ አጠፋቸው። እነ ጄኔራል መርዕድ ንጉሤ ከአላርም በላይ ሲጮሁ ሊቀመንበር መንግስቱ ኃይለማርያም ጠራርገው አጠፏቸው፤ በኋላ ግን ራሳቸውም ጠፉ!
በአላርም አለመንቃት አደጋው ይሄ ነው። በትዳራችን አላርም አለ። በንግዳችን አላርም አለ። በየቦታው አላርም አለ፤ አላርሞችን እያጠፋን ለጥ ብሎ መተኛት ግን እስከወዲያኛው መተኛትን ያመጣል። በአሁኑ ሰዓት ለኢትዮጵያ አላርሞቿ እነ ሶሪያ፣ ሊቢያ፣ የመን፣ ጎረቤት አገር ሰማሊያ…ናቸው። እነዚህ ዓይነት አገራት አንድ ሃይማኖት እየተከተሉ፣ አንድ ቋንቋ እየተናገሩ፤ ይሄው እንደምንሰማው ነው።
‹‹ለውጥ ምንጊዜም ነውጥ አለው።›› መጽሐፍ ቅዱስም እንደሚለው አንዲት ሴት ስትወልድ ብዙ ስቃይ ታያለች። ወልዳ ልጁን ስትስም ግን ‹‹ምጡን እርሽው ልጁን አንሽው›› ይባላል። ምጥ ሊነጋ ሲል ይጨልማል እንደሚባለው ነው።
አገሪቱ ውስጥ ሁለት አይነት መፈናቀል ነው ያለው። አፈናቃዮች ከአዕምሯቸው ተፈናቅለዋል፤ ተፈናቃ ዮች ግን ከቦታቸው ነው የተፈናቀሉት። ሁለቱም ተፈናቃዮች እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ለአፈናቃዮቹ ፍቅርና ጥበብ፤ ለተፈናቃዮቹ ደግሞ ልብስና ምግብ።
በየመድረኩ እንናገራለን፤ የምንናገ ረው ስለሚያንገበግበን ነው። እኔ የምናገረው የሦስት ሺህ ዓመት ታሪክ እንዳይጠፋ አይደለም፤ እኔ መኖር ስላለብኝ ነው። አንድ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረ ባለቅኔ እንዳለው ሰው ክፋት ሲያስብ በሃይማኖት ያሽገዋል። በሃይማኖት ያሽገውና ሲከፈት ግን ክፋት ነው። የምናገረው ልጆቼ ውለው እንዲገቡ ነው። ከሙስሊሞች ጋር የምግባባው ለእነርሱ ብዬ ሳይሆን ለራሴው ብዬ ነው። ራጉኤል እሳት ከተነሳ አንዋርም ስለሚቃጠል ነው ውሃ ይዘን የምንሄደው። ብቻውን ተቃጥሎ አይቀርም።
እየመረረን የምንውጠው ሀቅ ማንም ያልወከላቸው በየብሄሩ የተደራጁብን ሰዎች ናቸው። እቅጩን እንነጋገር ከተባለ አማራን እንወክላለን ብለው የተነሱ ሰዎች፤ ደብረብርሃን፣ ጎንደር፣ ደሴ እና ባህርዳር ይሂዱና ህዝቡ ለሕወሓት፣ ለአረና፣ ለትግራይ ህዝብም ያለውን ጥላቻ ቀይሮ ልቡን ለፍቅር እንዲከፍት ይንገሩት፤ ከዚያ በኋላ ነው መወያየት የሚቻለው። ይሄ እየጎመዘዘን የምንውጠው ሀቅ ነው። ሰው ‹‹ኦፕሬሽን›› የሚደረገው ጠባሳ ፈልጎ አይደለም። ጠባሳው ግዴታ ነው፤ በሽታው ግን መውጣት አለበት።
መቀሌ ያሉት ወገኖቻችን ለትግራይ ህዝብ ሊነግሩት የሚገባው ስለአማራው፣ ስለኦሮሞው፣ ስለሶማሌው ሳይሆን ለእነ ቶሎሳ፣ ለእነ ዘበርጋ እና ለእነ ጂግጂጋ ልብህን ክፈት ብለው ይንገሩት፤ ያኔ የምንፈልጋት ኢትዮጵያ ትቀጥላለች።
በኦሮሚያ ክልል ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለህዝባቸው የሚቆረቆሩ ከሆነ የኦሮሞ ህዝብ ሌላውን እንዲያቅፍ በጆሮው በኦሮምኛ ይንገሩት። ከዚህ ውጪ ጥላቻን እየሰበኩ መፍትሔ ሊመጣ አይችልም። አንድ ሰው ኖረ የሚባለው መኖር ሲፈልግ ነው። መኖር አልፈልግም የሚል ሰው ነው አደጋ የሚሆነው።
አንድ ሰው ልረብሽ ካለ እኮ መረበሽ ቀላል ነው። ሦስት ቁንጫዎች ቢመዘኑ አንድ ኪሎ እንኳን አይሆኑም፤ ግን 50 ኪሎ ሰው ቁጭ አድርገው ያሳድራሉ። እንኑር ከተባለ ነው በሠላም የሚኖረው እንጂ አልኖርም ከተባለ ማንም ለማንም ቁንጫ ነው።
‹‹መብትና ግዴታውን የማያውቅ ሕፃን እና የአዕምሮ ህመምተኛ ነው።›› የአዕምሮ ህመምተኛን አስቦ ሰርግ የሚጠራው የለም፤ ለቅሶ ቀረህ ብሎ የሚወቅሰውም የለም፤ ምክንያቱም ከማህበረሰቡ ሀዲድ ውጪ ነው ያለው። እኛ ግን ሕጻንም ሳንሆን የአዕምሮ ህመምተኛም ሳንባል መብትና ግዴታችንን መለየት እያቃተን ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ፓስተርና የኔ አይነት ሰባኪ የበዛው የኢትዮጵያ ህዝብ ዝም ብሎ ስለሚያጨበጭብ ነው፤ ካጨበጨብን በኋላ ነው ‹‹ምንድን ነው?›› ብለን የምንጠይቅ። ጠይቆ የሚያጨበጭብ ቢሆን ኖሮ አርፈን ነበር የምንቀመጥ። ሕዝብ እልም አድርጎ ይሳሳታል። በኖህ ጊዜ የጥፋት ውሃ ያጥለቀለቀው መንግስት ተሳስቶ ሳይሆን ህዝብ ተሳስቶ ነው።
ልዩነቱ ግን ህዝብ የሚሳሳተው በጥቂት አሳሳቾች ነው። አይገመግምም፤ አይለካም። መንግስት ደግሞ የሚንቀውም ሆነ የሚያደንቀው ጠላት ሊኖረው አይገባም። ጠላቱን ካደነቀ ፍርሃት አድሮበታል ማለት ነው፤ ከናቀ ደግሞ ትዕቢት አድሮበታል ማለት ነው።
ኢህአዴግ የሚሳሳተው ነገር፤ 100 ሚሊዮን ህዝብ እየመራ ከአንድ ዘፋኝ ጋር ተጣልቶ ዜና ይሰራል። ይሄ ነውር ነው። እኔ ከተማሪዎች ጋር ስጣላ እዚያው ነው የምገለው፤ ያ! የተጣላሁት ተማሪ ግን ውጪ እንዲወራ ይፈልጋል። ውጪ ቢያወራ ለእሱ ዜና ሊሆን ይችላል፤ ለእኔ ግን ከተማሪው ጋር ተጣላ ተብሎ ውርደት ነው። በዚህ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተዋጣላቸው ይመስለኛል፤ ጠላት መምረጥም መቀነስም ያውቃሉ።
አንድ የፕሮቴስታንት እና አንድ የኦርቶዶክስ ወጣቶች ሲያወሩ እየሰማሁ ነበር። ‹‹ፓስተራችን ኦርቶዶክስ ሊሆን ሳያስብ አይቀርም›› አለቻት፤
‹‹ለምን?›› ስትላት ያችኛዋ፤ ‹‹ባለፈው የጌታን ቃል ሲያካፍለን መድኃኒአለም ሲል ሰምቼዋለሁ›› አለች። እንዲያው እኔ የምመክራችሁ ነገር ፕሮቴስታንቶች ስለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ወይም ስለ እስልምና ማወቅ ከፈለጋችሁ ምኑንም ከማያውቅ ሰው አትጠይቁ። ከእኛ ጠይቁ፤ ቅድስና ባይኖረንም እውቀቱ ግን አለን። እኔ ፊዚክስ አላውቅም፤ ኬሚስትሪ አላውቅም፤ ቤተ ክርስቲያንን ግን አውቃታለሁ።
ኦርቶዶክሶች ስለፕሮቴስታንት ማወቅ ከፈለጋችሁ በሳምንት አንድ ቀን ሄዶ ‹‹ኢየሱስ ጌታ ነው›› ከሚለው አይደለም፤ ከእንደነ ፓስተር ዮናታን አይነቶቹ ጠይቁና ጭብጡን አግኙ። ስለእስልምናም ማወቅ ስትፈልጉ የሚያውቁትን ጠይቁ። እኔ አንድ ጊዜ አንድ የእስልምና ምሁር ስለጫት ጠየቅኳቸው።
ጫት ከእስልምና ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ ነው እቅጩን የነገሩኝ። አንድ ዓርብ ብቻ መስጂድ የሄደ ሙስሊም ጫት ከእስልምና ጋር ይገናኛል ቢለኝ አላምነውም፤ ምክንያቱም እውነቱን ከዑስታዝ ነው ያገኘሁት።
የየትኛውም እምነት ተከታዮች እስኪ ላሊበላን ጎብኙ፤ ለእናንተ ቅርሳችሁ ነው፤ ለእኛ መቀደሻችን ነው፤ ለእናንተ ንብረታችሁ ነው፤ ለእኛ መጽደቂያችን ነው። እኔ ወደፊት ሰው አስተባብሬ ባሌ ውስጥ ኑራ ሁሴን የሚባል መስጂድ ለመሄድ አስቤያለሁ። ሰብስቤ አንዋር መስጊድን ማስጎብኘት እፈልጋለሁ።
እየጎመዘዘን ሀቅን መዋጥ አለብን። አጼ ቴዎድሮስ፣ በላይ ዘለቀ እያሉ በማላዘን አገር ልትቀጥል አትችልም።
ዛሬ ስራ መሥራት አለብን፤ ከሞተው በላይ ዘለቀ ይልቅ ካለው ጎጃሜ ጋር ተግባባ። ከሞቱት አጼ ምኒልክ ይልቅ ካለው የሸዋ ህዝብ ጋር ተቀራረብ። ከሞቱት ይልቅ ካሉት ጋር እንኑር። ኢትዮጵያውያን የሞተ ማድነቅ እንወዳለን፤ የሞተ የምናደንቀው ስለምንወደው ሳይሆን፤ የቆመውን ለማበሳጨት ነው።
እኔ በዚህ ዓመት ውስጥ ያየሁት ቴአትር ዶክተር አብይን ለማድነቅ አቶ መለስን ለመሳደብ ነው፤ አቶ መለስን ለማክበር ዶክተር አብይን ማቅለል ነው የሚታየው። አቶ መለስን የሚያመሰግኑት የቆመውን ላለመቀበል፤ ዶክተር አብይንም የሚያመሰግኑት የሞተውን መርገም ልማድ ስለሆነባቸው ነው!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 15/2011