
– ሰሜን ሸዋና ደቡብ ወሎ ዞኖች ሩዝ ማልማት ይጀምራሉ
አዲስ አበባ፡-በአማራ ክልል በዘንድሮ የምርት ዘመን 188 ሺህ 631 ሔክታር መሬት በሩዝ ሰብል ለመሸፈን ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። ዘንድሮ ሰሜን ሸዋና በደቡብ ወሎ ቃሉ አካባቢ የሚገኙ አርሶ አደሮች ወደ ሩዝ ምርት እንዲገቡ የመሬት ልየታና የዘር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተጠቁሟል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ቃልኪዳን ሽፈራው ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በዘንድሮ የምርት ዘመን የክልሉን የሩዝ ማሳ ሽፋን ወደ 188 ሺህ 631 ሄክታር መሬት ለማድረስ ታቅዷል።
የሩዝ ምርት እንደ ክልል የተሻለ ልምድ አለ ያሉት ያሉት ምክትል ኃላፊው፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሩዝ ምርትን ለማሳደግ የተጀመረውን ንቅናቄ በመጠቀም ምርቱን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
አቶ ቃልኪዳን እንዳስታወቁት፤ በክልሉ ባለፈው የምርት ዘመን 82 ሺህ 279 ሔክታር መሬት በሩዝ ምርት መሸፈን ተችሏል። ዘንድሮ ወደ 188 ሺህ 631 ሄክታር ለማሳደግና በአንድ ሄክታር 53 ኩንታል የሩዝ ምርት ለማግኘት ታቅዷል።
በክልሉ በሚገኙ አምስት ዞኖች በተለይም በደቡብ፣ ሰሜን፣ ማዕከላዊ እና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች በሩዝ ምርት የተሻለ ውጤታማነት ያላቸው አካባቢዎች መሆናቸውን ጠቁመው፤ አርሶ አደሩ አዳዲስ አሠራሮችን እንዲላመድ በማድረግ የተሻለ ምርት ለማግኘት መታቀዱን አስረድተዋል።
የማሳ ሽፋኑን በማሳደግ ሂደት ከዚህ በፊት ሲሰራባቸው በነበሩ አካባቢዎች አዳዲስ መሬት ለማልማትና ከዚህ በፊት የሩዝ ምርት ወደሌለባቸው አካባቢዎች ልማቱን ለማስፋፋት እየተሠራ ነው ብለዋል።
ከዚህ በፊት በምስራቅ አማራ አንዳንድ አካባቢዎች የነበረው የአየር ሁኔታው ለሩዝ ምርት ምቹ መሆኑን ተከትሎ ሙከራ ሲደረግበት መቆየቱን ገልጸዋል።
ዘንድሮ በሰሜን ሸዋ አካባቢ እንዲሁም በደቡብ ወሎ ቃሉ አካባቢ የሚገኙ አርሶ አደሮች ወደ ሩዝ ምርት እንዲገቡ የመሬት ልየታና የዘር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውሰዋል።
በክልሉ የሩዝ ሰብል በሁለት ዓይነት መልኩ እንደሚዘራ የተናገሩት አቶ ቃልኪዳን፤ አንደኛው በመደበኛ አሠራር በውሃማ አካባቢዎች የሚለማ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ በክልሉ 86 በመቶ የማሳ ሽፋን ካላቸው 10 አይነት የእህል አይነቶች ጋር በማካተት የሚለማበት ሁኔታ እንዳለ አስረድተዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች የሩዝ መፈልፈያ ማሽን እጥረት፤ ሩዝ ሰፊ ውሃ ባለበት አካባቢ የሚዘራ ሰብል እንደመሆኑ የባለሙያ ክህሎች ችግርና በተለይም የመጀመሪያ ትውልድ የሚባለው የሩዝ ምርጥ ዘር እጥረት ምርታማነቱን እየፈተኑ ያሉ ችገሮች መሆናቸውን አንስተዋል።
በክልሉ ከሩዝ ምርት ጋር ተያይዞ ሰፊ ምርምር መደረጉ፣ አዳዲስ ማሽኖችን በማስገባት የምርት ሂደቱን ለማዘመን የተሠራው ሥራና ሰፊ ውሃ ያለባቸውን አካባቢዎች ለምርቱ መጠቀም መቻሉ እንደተሞክሮ የሚወሰዱ ውጤታማ ልምዶች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በመጨረሻም በሜቲዎሮሎጂ ጥቆማ መሠረት በክልሉ በቀጣይ የተሻለ ዝናብ ይኖራል ተብሎ ስለሚታሰብ በግብርና ዘርፍ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚሳተፉ አካላት ምርታማነትን ለማሳደግ የጀመሩትን ጥረት እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።
አመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኔ 1 ቀን 2016 ዓ.ም