በሴት ልጆች ጥቃት ዙሪያ የሚታዩ ፈተናዎች

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ጊዜያት ሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ይሰማሉ። ይህ ጥቃት መልኩን እየቀያየረ ይሂድ እንጂ፤ ማኅበረሰቡ የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ሊያስቆመው አልቻለም። ለዛሬ የሴቶች ዓምድ በቅርቡ በማኅበራዊ ሚዲያ የሰማነውን ወጣት ቃልኪዳን ባህሩ ታሪክ ይዘንላችሁ ቀርበናል። ይህች ታዳጊ በርካታ ሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ማሳያ ናት። በዚህ ፅሁፍ ውስጥ ከታዳጊዋ ጥቃት ባሻገር የሕግ ባለሞያ ሴቶች ማኅበር ከጎኗ መሆኑንና አጋርነቱን ያሳየበትን መግለጫም አካተናል።

ቃልኪዳን የ17 ዓመት ወጣት ናት። ታዳጊዋ ጥቅምት 1 ቀን 2014 ዓ/ም ከቤተሰቦቿ ጋር በምትኖርበት ቤት፣ በድጋሚ ደግሞ በመጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም በማታውቃቸው ሰዎች ከምትኖርበት አካባቢ ወዳልታወቀ ቦታ ተወስዳ የአስገድዶ መድፈር ተፈፅሞባታል:: በተጨማሪ በባዕድ ነገር በማደንዘዝ እራሷን እንድትስት በማድረግ ጥቃት እንዳደረሱባትና ጥቃት ካደረሱባት በኋላ፤ እንጦጦ ኪዳነምህረት አካባቢ ከመኪና ውረጂ በማለት ጥለዋት ሄደዋል:: በተጨማሪ ለቤተሰቦቿም ሆነ ለራሷ በተደጋጋሚ ዛቻና ማስፈራሪያ በቴሌግራም ፅሁፍ ስለደረሰባቸው ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደሆነች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ሲሰራጭ ተመልክተናል። ይህች ታዳጊ ከደረሰባት ጉዳት በላይ ዛቻና ማስፈራራያው የስነ ልቦና ጫና አያደረሰባት መሆኑንም ተናግራለች።

ይህን በማኅበራዊ ሚዲያ ሲሰራጭ የነበረን መረጃ ከሕዝቡ እኩል የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር (ኢ.ሕ.ባ.ሴ.ማ) በማኅበራዊ ሚዲያ ሲሠራጭ ለማግኘት ችሏል:: ይህ መረጃ እንደደረሰው ስለጉዳዩ ለማወቅ መንቀሳቀስ እንደ ጀመረ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ጉዳዩን አስመልክቶ በቅድሚያ መግለጫ የሰጠ ሲሆን፤ በስልክ ቤተሰቦቿን እንዳነጋገረ ገልፀዋል:: በተጨማሪ ማኅበሩ ቃልኪዳንን ከቤተሰቦቿ ማለትም ከእናትና አባቷ ጋር ጠርቶ በሚያዚያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም. እና በግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም. በቢሯቸው ተገኝተው ከመጀመሪያ ጥቃት ከተፈፀመበት ቀን ጀምሮ ሁለተኛ ጥቃት እስከ ተፈፀመበት ጊዜ ድረስ የነበረውን ሁኔታ አስረድተዋል::

ቤተሰቦቿ ስለጉዳዩ እንደተናገሩት፤ በደምብ በመተንተን ውይይት ከማድረግ ባሻገር፤ በፖሊስ እና በጤና ባለሞያዎችም ምርመራ ተደርጎላታል:: ምርመራውን ተከትሎ ማኅበሩ የሕግ ድጋፍ እንዲያደርግ ቢጠየቅም፤ ማኅበሩ ግን በወቅቱ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ብሎ ያሰበውንና ጥቃቱ በታናሽ እህቷ ላይም ተከትሎ ሊደርስ እንደሚችል በመስጋት ካሉበት የሸራ ቤት መውጣት እንዲችሉ ለሚኖሩበት አራዳ ክፍለ ከተማ ቤት እንዲሰጣቸው የሚጠይቅ የትብብር ደብዳቤ ፅፎላቸዋል::

በተመሳሳይ ለጊዜው የምታርፍበት ጊዜያዊ መጠለያዎችን የማፈላለግና የማነጋገር እንዲሁም የስነ ልቦና ድጋፍ ማግኘት እንድትችል ማመቻቸት የመሳሰሉ እገዛዎችና ስራዎችን ሲሠሩ መቆየታቸውን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል:: የሕግ ድጋፉን በተመለከተ መግለጫ ሰጪዎቹ ጥቆማው ከደረሰበት ቀን አንስቶ ተጠቂ ሁለቱን ጥቃቶች ባመለከተችበት በአራዳ እና ጉለሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ በመመላለስ ጉዳዩን ሲከታተል ቆይቷል::

የአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያም በጉዳዩ ላይ ስልጣን ስላለው ሁለቱን መዝገቦች አጣምሮ እንደሚከታተልና የደረሰበትንም እንደሚያሳውቀን እንደነገራቸው ገልፀዋል:: በተጨማሪም በወቅቱ የሰጡት ምላሽ የተጠቂ የሕክምና ማስረጃ መደፈሯን የማያሳይና በዚህም መነሻ ማድረግ የሚችሉት ነገር እንደሌለ፣ ሆኖም ግን ተጨማሪ ጥቆማዎች ካሉ ተከታትለው ጉዳዩን እንደሚመረምሩ አሳውቀው በነበረበት ሁኔታ የጉለሌ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ መዝገቡን ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እንዳስተላለፈና ኮሚሽኑ እየመረመረ እንደሆነ የበለጠ መረጃ ከኮሚሽኑ ማግኘት እንደሚችሉ ተነግሯቸዋል:: በዚህም መነሻ ከኮሚሽን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመነጋገር ያደረጉት ጥረት በስብሰባ ምክንያት ሊሳካ አልቻለም ሲሉ በመግለጫው ተናግረዋል::

ግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ/ም፤ በወጣት ቃልኪዳን ባሕሩ ላይ በተፈጸመው አስገድዶ መድፈር፣ ዕገታና ፆታዊ ጥቃት ዙሪያ የወጡ የፖሊስ፣ የሕክምና እና የማኅበራዊ ሚዲያ መረጃዎች እንደገና እንዲጣሩና ትክክለኛው መረጃ ለሕዝብ እንዲደርስ፤ ተጠቂዋም ትክክለኛ ፍትህ እንድታገኝ በኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበርና አጋር ድርጅቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ የተለያዩ ማሳሰቢያዎች እነ ጥሪዎችን አካቶ ቀርቧል::

ማኅበራዊ ሚዲያዎች የተበደለን ሰው በደል ከማውጣት እና አስፈላጊውን ምላሽ እንዲያገኝ ከማድረግ አኳያና ድምፁ ያልተሰማ ሰው አገልግሎት ለማግኘት ፈልጎ መረጃው ከሌለው አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያገኝበትን የጥቆማ አገልግሎት የመስጠት ሚና መጫወቱ እንዳለ ሆኖ፤ ባልተጨበጠ መረጃ ላይ በመመስረትና ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሲባል የሚናፈሱ አሉባልታዎችን በመፍጠርና ተጠቂ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ሳያገናዝቡ የተዛቡ መረጃዎችን ማስተላለፍ አንዲት ጥቃት የደረሰባት ሴት መፍትሄ ወይም ፍትህ እንዳታገኝ እንቅፋት ከመሆኑም በላይ በተጠቂ የወደፊት ሕይወት ላይም ከፍተኛ ስነልቦናዊ ጉዳት የሚያስከትል ችግር ሊፈጥሩ ስለሚችል በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ መደረግ ይኖርባቸዋል ብለዋል::

ፖሊስ በመጀመሪያ ተማሪ ቃልኪዳን ጥቃት ደረሰብኝ ብላ ባመለከተችበት ወቅት በቀጥታ ወደ ሆስፒታል ወስዶ እርዳታ እንድታገኝ ማድረጉ መልካም ሆኖ ሳለ፤ የሕክምናው ሂደት ትክክል መሆኑን ማጣራት፤ ማረጋገጥና ተከታታይ የጤና ክትትል እንድታደርግና የተገኘውን ውጤት ከቤተሰብና ከተጠቂዋ ጋር በግልጽ ከመነጋገር ይልቅ በደፈናው ክትትል እየተደረገበት እንደሆነ ነግሮ የፖሊስ ምርመራው የደረሰበትን ደረጃ በግልፅ ለተጠቂ ማሳወቅና የፖሊስ ምርመራ መዝገቡ የተዘጋም ከሆነ ፋይሉ የተዘጋበትን ምክንያት፣ መዝገቡ የተዘጋው ለጊዜው ቢሆን እንኳን በቂ ማስረጃ ከተገኘ ሊከፈትና ምርመራው ሊካሄድ እንደሚችል ማስረዳት ሲገባ ይህንን ሳያደርግ በመቅረቱ በተጠቂዋ ላይ ተጨማሪ ጥቃት ሊፈጸም ችሏል ብሏል::

ሁለተኛው ጥቃት ሲፈፀም ለሕክምና ጴጥሮስ ሆስፒታል ሄዳ የተደረገላት ሕክምና እና የተመረዘችበትን ሁኔታ ካለ ሳይረጋገጥ፤ መደፈሯንና አለመደፈሯን ብቻ ቅድመ ሁኔታ በማድረግ አስፈላጊው ምርመራ እና ክትትል ሳይደረግ፤ እንደ መጀመሪያው ጥቃት ግልጽነት በጎደለው መልኩ ለተጠቂ በቂ መረጃ ሳይሰጣት በድጋሚ ጉዳዩ ተይዞ የነበረው ሚኒሊክ ሆስፒታል ስለሆነ ወደዛ እንድትሄድና ምርመራ እንዲካሄድ መደረጉ፣ ብትሄድም ፋይሉን ከማገናኘት ውጪ ተገቢው የጤና ምርመራ አለመደረጉ ተጠቂዋ ተስፋ እንድትቆርጥ አድርጓታል::

ፖሊስም መነሻውን የሕክምና ሰነድ ብቻ በማድረግ በጉዳዩ ላይ በቂ ማስረጃ የለም ማለቱ፣ አጥቂዎችን ለመያዝ በቂ ክትትል አለማድረጉ፣ በቴሌግራም፣ በስልክ እንዲሁም በፅሁፍ ለተጠቂ እና ለእናቷ በደረሳቸው መልዕክቶችና ዛቻ ዙሪያ ተጠቂን ፅሁፍ እንድትጽፍ በማድረግና ፅሁፉን በማመሳሰል ብቻ በተለየ የፎረንሲክ ምርመራ ሳይደረግ እንደውም ተጠቂን ተጠርጣሪ የማድረግ በሚመስል ሁኔታ ምርመራውን ማካሄዱ፤ ሌሎች ተጨማሪ የፖሊስ ምርመራ ሂደቶች ተደርገው ቢሆን እንኳን ውጤቱን በግልፅ ለተጠቂም ሆነ ለቤተሰቦቿ ሳያሳውቁ፣ ከወንጀሉ ውስብስብነት እና ተጠቂ በባዕድ ነገር ከመመረዟ በመነሳት የተፈጠረውን ሁኔታ ፖሊስ በረቂቅ ምርመራ ሂደት ከመመርመር አኳያና አስፈላጊውን የፎረንሲክ ምርመራና በመረጃና ደህንነት ተቋም በኩል በወጣት ቃልኪዳን ባህሩ ላይ በተፈጸመው አስገድዶ መድፈር፣ ዕገታና ፆታዊ ጥቃት ዙሪያ የወጡ የፖሊስ፣ የሕክምና እና የማኅበራዊ ሚድያ መረጃዎች እንደገና እንዲጣሩና ትክክለኛው መረጃ ለሕዝብ እንዲደርስ፤ ተጠቂዋም ትክክለኛ ፍትህ እንድታገኝ በኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበርና አጋር ድርጅቶች የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የቴክኖሎጂ ምርመራ ሳያደርግ ተደርጎም ከሆነ በግልፅ ሳያሳውቅ ተጠቂዋን ሀሰተኛ መረጃ አሰራጭታለች ብሎ መወንጀሉ የምርመራ ሂደት ስነስርዓቱን ተዓማኒነት ከማሳጣት እና አንዲት ጥቃት ለደረሰባት ሴት ፍትህ የመጠየቅና የማግኘት መብቷን ከመንፈግ ባሻገር በሚደረገው ምላሽ አሰጣጥ አገልግሎት ላይ ዝቅ ያለ ግምት እንዲኖራትና አጥቂዎችን የበለጠ ረቂቅ የጥቃት መንገድ እንዲጠቀሙ የሚያበረታታ ከመሆኑም በላይ ጥቃት የሚደርስባቸው ሴቶች ሰሚ አካል እንደሌላቸው እንዲያስቡ የሚያደርግ እርምጃ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል ብለዋል::

የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር እና ከታች የተዘረዘሩ አጋር ድርጅቶች የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በጉዳዩ ላይ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል:: ለአዲስ አበባ ፖሊስ፡ በቴሌግራም መልዕክቶችን እንዲሁም ለተጠቂ እናት በስልክ ሲደርሳቸው የነበረው ዛቻና ማስፈራሪያና የመደራደር ሀሳብን አስመልክቶ ፖሊስ በምን መንገድ አስፈላጊውን ምርመራ እንዳደረገ ከምርመራው ያገኘውን ውጤት በግልፅ እንዲያሳውቀን ይህ አይነት የተወሳሰበ ወንጀል በቴክኖሎጂ፣ በፎረንሲክ እንዲሁም በልዩ ልዩ የፕሮፌሽናል ማስረጃ በማረጋገጥ የሚፈታ ወንጀል በመሆኑ የአዲስ አበባ ፖሊስ ይህን አድርጎ ከሆነም ውጤቱን በግልፅ እንዲያሳውቀን ሲሉ ገልፀዋል:: ይህ ሳይሆን ቀርቶ ከሆነ ሌሎች ሴቶች ልጆች እንዲሁም ሕፃናት ላይ ከፍተኛ የደህንነት ስጋት የሚያደርስ ከመሆኑ አንፃር አሁንም በድጋሚ ጥልቅ ምርመራ እንዲያደርግ፣ የፖሊስ የምርመራ ሂደት መዝገብ ከወንጀሉ ውስብስብነት አኳያ ለተጠቂ የተደረገ ጥንቃቄም ግልፅነትን መሠረት ያደረገ ስራ ተሰርቶ ከሆነ ሂደቱን እንዲያረጋግጥላቸው አሳስበዋል::

ለሚኒሊክና ለጴጥሮስ ሆስፒታሎች፡ የህክምና ማስረጃውን በሚመለከት ተጠቂ የህክምና እገዛ ይደረገልኝ ብላ እንዳመለከተች ምንም አይነት የዘረመል ምርመራ አለመደረጉ እና በወቅቱ በነበረው የህክምና ባለሙያ በአይን ከመመልከት የዘለለ ህክምና እንዳልተደረገ እና ምርመራው ምን ያህል ደረጃውን የጠበቀ እና የተጠቂን የጉዳት መጠን ያማከለ መሆኑን ለተጠቂ እና ለቤተሰቦቿ በግልፅ ማስረዳትና ተከታታይ ህክምና የሚያስፈልጋት ቢሆን እንኳን እርዳታና የተጠቂን ጤና፣ ጥቅምና ሞራል ያላማከለ የህክምና እገዛ ተደርጎላት ሊሆን እንደሚችል ያሳያል ብለዋል::

በመሆኑም በዚህ ረገድ ለፖሊስ ከተሰጠው የህክምና ማስረጃ ሰርተፍኬት በዘለለ የተደረገላት ህክምና እና የምርመራውን ሂደት በግልፅ የሚያሳይ ውጤት እንዲገለፅላቸው፤ የተጠቂዋን ደህንነት እና የደረሰባት ጉዳት ካለም በግልፅ እንዲያሳውቃቸው ጠይቀዋል::

ለማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች፡ በማህበራዊ ሚዲያ በተደጋጋሚ እየተሰራጨ ያለው ሀሰተኛ መረጃ ተጠቂዋን ከደረሰባት ጥቃት በተጨማሪ ፍትህ የማግኘት መብቷን እየነፈጋትና በጤንነቷም ሆነ በስነልቦናዋ ላይ በድጋሚ ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚፈጥርባት በመሆኑና ድጋሚ ሌላ ተጨማሪ ጥቃት ከማድረስ የማይተናነስ በመሆኑ በወጣት ቃልኪዳን ባህሩ ላይ በተፈጸመው አስገድዶ መድፈር፣ ዕገታና ፆታዊ ጥቃት ዙሪያ የወጡ የፖሊስ፣ የህክምና እና የማህበራዊ ሚድያ መረጃዎች እንደገና እንዲጣሩና ትክክለኛው መረጃ ለህዝብ እንዲደርስ፤ ተጠቂዋም ትክክለኛ ፍትህ እንድታገኝ በኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበርና አጋር ድርጅቶች የሚጠይቁ መሆኑ በመግለጫው ተጠይቋል።

ለሚዲያ አካላት፡ ሚዲያዎች መረጃዎችን ለኅብረተሰቡ በማሰራጨትና ተደራሽ በማድረግ የአንበሳውን ድርሻ ስለሚወጡ ይህ መረጃ ሃሰተኛ ይሁን አይሁን ለማጣራት በሚደረገው ሂደትና ተጠቂዋ ትክክለኛ ፍትህ እንድታገኝ በሚያደርጉት ጥረት ከጎናቸው በመቆም ትክክለኛውን መረጃ ለኅብረተሰቡ እንዲያደርሱ ጥሪያቸውን አቅርበዋል::

በሴቶች መብቶች ዙሪያ ለሚሰሩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በየጊዜው በሴት እህቶች ላይ የተለያዩ ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እየደረሱ ይገኛሉ:: በመሆኑም ስለተጠቂ ቃልኪዳን ባህሩ እየተሰራጨ ያለውን መረጃ ትክክለኛነት በማጣራትና በነበሩ ሂደቶች ዙሪያ የተደረገላት የሕክምና ሂደቶች ትክክለኛነት ተጣርቶ ፍትህ እስክታገኝ ድረስ ከተቋማቸው ጋር ተባብረው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል::

ለመላው የኅብረተሰብ ክፍል፡ የሴትን ልጅ ጥቃት ፍጹም የማይታገስ ህብረተሰብ እንዲፈጠር ለማህበረሰቡ ግንዛቤ በመስጠት በሚያደርጉት ጥረት ከጎናቸው እንዲቆሙና በማህበራዊ ሚዲያም ሆነ በማንኛውም መንገድ የሚሰራጩ መረጃዎችን ትክክለኛነት ሳያረጋግጡ እንዳይወናበዱና በሀሰተኛ መረጃ ላይ ተመርኩዘው ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች ስም በጥፋት ከመፈረጅ እንዲቆጠቡ አሳስበዋል::

ይህንን መግለጫ ያስተላለፉ ተቋማት ዝርዝር የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር የኢትዮጵያ ሴቶች መብት ተሟጋች፤ የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት፤ ሴቶች ይችላሉ፤ ሲሃ ኔትወርክ ናቸው።

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2016 ዓ.ም

Recommended For You