በሀገራችን ተቀባይነትን እያገኘ የመጣው የእደ ጥበብ ውጤት

ክርን በመጠቀም ከሚሰሩ የእጅ ሥራ ውጤቶች ውስጥ የተለያየ ዓይነት ልብሶች፣ ጌጣጌጦች፣ የቤት ውስጥ ማስዋቢያዎች ይጠቀሳሉ። እነዚህ በኪሮሽና በመሳሰሉት የሚሰሩ አልባሳት ቀደም ሲል በእጅጉ ይፈለጉ የነበረ ቢሆንም፣ የሆነ ወቅት ላይ ግን ተፈላጊነታቸው እየቀነሰ መምጣቱ ይታወቃል።

እነዚህ የእጅ ሥራ ውጤቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተፈላጊነታቸው እየጨመረ መጥቷል። የእጇ ውጤት የሆኑ ሥራዎችን በመሥራት ለገበያ በማቅረብ ላይ የምትገኘው ዲዛይነር እና የእደ ጥበብ ባለሙያዋ ሶፊያ ጀማልም ይህንን ታረጋግጣለች።

ሶፊያ ከክር የሚሰሩ ሹራቦች፣ የሕፃናት ልብሶች፣ በተለያዩ ክሮች የሚሰሩ የሴት ቦርሳዎች፣ አበባ እንዲሁም ቤትን ለማስዋቢያነት የሚውሉ ጌጣጌጦች በአጠቃላይ በእጅ የሚሰሩ ሥራዎች እንደምትሰራ ትናገራለች። ‹‹ልጅ ሆኜ ጀምሮ ስዕል መሳል እወዳለሁ፤ እናቴም በክር የሚሰሩ የቤት ውስጥ ማስዋቢያዎችን ስትሰራ አያት ነበር፤ በዚህ ሁሉ ምክንያት ወደ እጅ ሥራው የተሳብኩት ከልጅነቴ ጀምሮ ነው›› የምትለው ሶፊያ፣ እናቷ ስትሰራ ብታያትም የተቀሩት ወላጆቿ ግን በቀለም ትምህርቷ ላይ እንድታተኩር ነበር ፍላጎታቸው።

ሶፊያ ካደገች እና የራሷን ኑሮ መስርታ የልጅ እናት ከሆነች በኋላ ግን በልጅነት አዕምሮዋ የቀረጸችውን ሙያ የቤት ማስዋቢያ ጌጣጌጦችን፣ ከኪሮሽ የሚሰሩ ልብሶችን በተለይም የሕፃናት ልብሶችን እየሰራች በልጇ ላይ መሞከር ትጀምራለች።

‹‹ ሥራዎቼን የምታስተዋውቅልኝ ልጄ ናት ማለት እችላለሁ፤ ለእሷ የሰራሁትን ልብስም ሆነ ጌጥ ልጄ አድርጋው ስትወጣ ሌሎች ሰዎች አይተው እንደሰራላቸው ያዙኛል›› ስትል ገልጻ፣ በቤት ውስጥ በትርፍ ሰዓት እና እንዲሁም በመውደድ ደረጃ የተጀመረው የሶፊያ የእጅ ሥራ በቤተሰቦቿ ፣ በሥራ ቦታዋ እና በዙሪያዋ ባሉ ሰዎች ዘንድ ተቀባይነትን እያገኘ መጥቷል።

ይህ ብቻም አይደለም ለሌሎች ሰዎች መሥራቷን ቀጠለችበት። ከዚያም ሥራው ወደ ንግድ ሥራ መዋል /ቢዝነስ መቀየር/ እንደሚችል በማመን በባለቤቷ አበረታችነት የሙሉ ጊዜ ሥራዋ አድርጋ አጠናክራ ቀጠለችበት።

የእደ ጥበብ ውጤቶች በሀገራችን ያላቸው ተቀባይነት እምብዛም አበረታች ሳይሆን ቆይቷል የምትለው ሶፊያ፣ የሙሉ ጊዜ ሥራዋ ካደረገችው በኋላ ግን ሰዎች ሊወዱት በሚችሉት መልኩ ተጠንቅቃና የራሷን ፈጠራ በማከል ሥራዎቹን መሥራቱን ተያይዛዋለች። በተለያዩ ስጦታ እቃ መሸጫ ሱቆች፣ ልብስ ቤቶች፣ እንደማሳያ የሚሆኑ ሥራዎቿን በማስቀመጥ ሥራዎቿን ለሚወዱ እና ለሚፈልጉ ሰዎች በትእዛዝ መሥራቷን ቀጥላለች።

‹‹ ከአንድ እና ከሁለት ዓመት በፊት ብዙ ሰዎች በእጅ መሰራቱን ፣ የሀገር ውስጥ መሆኑን በማየት ሥራዎቹን ሊያጣጥሉት ይፈልጉ ነበር ›› የምትለው ሶፊያ፣ በአንጻሩ አሁን ደግሞ ለእጅ ሥራ ውጤት ልዩ ዋጋ ሰጥተው የሚያዙ ደንበኞች እንዳሏትም ተናግራለች።

በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሙያዋን የሚያሳድጉላትን ተንቀሳቃሽ ምስሎች የምትመለከት ሲሆን፣ በሌሎች ሀገራት ለኪሮሽ ሥራ ልብሶችም ሆኑ በክር ለተሰሩ ቦርሳዎች ያለው ተቀባይነት በሀገር ውስጥም ቢኖር ትመኛለች። ለዚህም እንደ ምስክርነት የምታነሳው በሀገር ውስጥ ደንበኞቿ አማካኝነት ሥራዎቿን በውጭ ሀገር ለሚገኙ ዜጎች ጭምር ሰርታ መላኳን ነው።

እሷ እንደምትለው፤ የእጅ ሥራ ውጤት ቦርሳዎችን ለመሥራት በገበያው ላይ የተለያዩ ግብዓቶች የሚገኙ ሲሆን፣ በብዛት ጥቅም ላይ የሚውለው ክር ነው። ግብዓቱ በከተማችን አዲስ አበባ ውስጥ በመርካቶ ድር ተራ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ላይ በብዛት ይገኛል።

ቦርሳ ለመሥራት የምትጠቀመው የክር ዓይነት እንደየደረጃው ይለያያል፤ ክር፣ መረብ፣ ኪሮሽ፣ ተስተካክሎ የተዘጋጀ ቆዳ ፣ የቦርሳ ቁልፍ ፣ ማጣበቂያዎች እንደ ግብዓት የምትጠቀማቸው ናቸው።

‹‹ ከዚህ በፊት በብዙ ሰው ዘንድ ተቀባይነት ስላልነበረው ገበያው ላይ የነበረው አቅርቦትም ያን ያህል አልነበረም፤ ያኔ ገበያው ላይ ያለው ጥሩ ክር ወይም እቃ ሌላ ጊዜ ላይኖር ይችላል፤ አሁን ግን ምርቱን ሰዎች እየተቀበሉት ስለመጡ ሥራውን የሚሰሩ ባለሙያዎችም ስለተበራከቱ ይመስለኛል ግብዓቱም ከሌላው ጊዜ በተሻሻለ በገበያው ላይ ይገኛል። ›› ስትል አብራርታለች።

ሶፊያ የልጅ እናትም እንደ መሆኗ እነዚህን ሥራዎች የምትሰራው በቤት ውስጥ ሆና ነው፤ የእርሷ ሙያና ከቤታቸው ርቀው መሥራት ለሚከብዳቸው ሰዎች እንደ አንድ አማራጭ ሊጠቅም ይችላል። ሥራዎቿን ለተለያዩ ሱቆች ከማስረከብ ባለፈ በግል ለሚያዟት ደንበኞች ባሉበት ቦታ በመሄድ ታስረክባለች።

ቦርሳዎቿን በአብዛኛው የምትሰራቸው ለሴቶችና ለሕፃናት እንዲሆኑ እርጋ ነው፤ እንደየቦርሳው መጠን ሰርቶ ለማጠናቀቅ ከአንድ ቀን እስከ ሁለት ቀን ያህል ጊዜን ይወስድባታል። ለመዘነጫነት የሚሆኑ የእጅ ቦርሳዎችን በማይነጫጩ እና ወፍራም በሆኑ ክሮች፣ መረብ እና የተለያዩ ማስዋቢያዎችን ተጠቅማ እንደምትሰራ ትናገራለች።

ብዙ እቃ መያዝ የሚችሉ ትልቅ እና ለእለት ተዕለት መገልገያ የሚሆኑ ቦርሳዎችን ደግሞ ቆዳ፣ ወፍራም እና ጠንካራ ክርን በመጠቀም ትሰራለች።

ከክር የተሰሩ ቦርሳዎች ተመራጭ የሚያደርጋቸው ምን ይሆን ብለን ላቀረብንላት ጥየቄም ‹‹የክር ቦርሳዎች ይለያሉ ነው ያለችው፤ በዲዛይንም ተመሳሳይ አይሆኑም፤ ውበት አላቸው፤ በዛ ላይ በሚቆሽሹበት ጊዜ አጥቦ መጠቀምም ይቻላል። ›› በማለት ትገልጻቸዋለች።

ሶፊያ ሙያውን ለማሳደግ በየቀኑ ከምትሞክራቸው አዳዲስ ዲዛይኖች ባሻገር የዲዛይን ትምህርት በመውሰዷ ማንኛውንም ቦርሳ ከመሥራቷ በፊት በአዕምሮዋ የምታስበውን ዲዛይን አስቀድማ በወረቀት ላይ በስዕል መልክ ታሰፍረዋለች።

ጥቁር ቀለም ያላቸው ከክር የተሰሩ ቦርሳዎች በብዙ ሴቶች ዘንድ ተመራጭ እንደሆኑም ጠቅሳ፣ ሰዎች ከራሳቸው ባለፈ ለሌሎች ሰዎች ስጦታ ለመስጠት እሷ ዘንድ እንደሚሄዱም ነው የተናገረችው። ከትንንሽ የሕፃናት ቦርሳዎች፣ ለሴቶች እቃ መያዝ የሚችሉ ቦርሳዎችን ከ500 ብር ጀምሮ ትልቅ እስከሚባለው እስከ ሁለት ሺህ ብር ድረስ እየሰራች ለገበያ ታቀርባለች። ለደንበኞቿ በምትሰጥበት ወቅትም ከተጠቀሙ በኋላ በፕላስቲክ ውስጥ ለይተው እንዲያስቀምጡት ትመክራለች።

ሶፊያ ሙሉ ለሙሉ በእጅ የተሰሩ ውጤቶች ወርክሾፕ ወይንም የእደ ጥበብ ውጤት መሸጫ ሱቅ ባለቤት መሆን ህልሟ መሆኑን ትገልጻለች። ያ ሲሆን ሀገራችን ስለ እደ ጥበብ ውጤቶች ያለው አመለካከት ይቀየራል ብላም ታምናለች።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You