እንዴት ናችሁ ልጆች? ሠላም ናችሁ? ትምህርት እንዴት ነው? ባጠናቀቅነው ሳምንት ሁሉም የስድስተኛ እና የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ሞዴል ፈተና እንደወሰዱ ይታወቃል አይደል ልጆች። የተፈተናችሁ ልጆች ፈተና እንዴት ነበር? ለፈተና በሚገባ ተዘጋጅታችሁ ነበር? በጣም ጎበዞች። በቻላችሁት መጠን እንዳጠናችሁ ምንም ጥርጥር የለኝም። ስለዚህም ልጆችዬ ከሞዴል ፈተና ብዙ ተምራችሁ ዋናው ፈተና ሲደርስ በብቃት ፈተናውን ለመውሰድ የተማራችሁትን ትምህርት በመከለስ፤ ለፈተና ራሳችሁን በሚገባ ማዘጋጀት እና ማጥናት ይኖርባችኋል። ሌላው ደግሞ ልጆችዬ ያለምንም መደናገጥ እና ጭንቀት ፈተናችሁን መውሰድ አለባችሁ።
ልጆችዬ፣ በእርግጥ ዛሬ ስለፈተና ልናወራችሁ አይደለም። በሌላ ጊዜ እንዴት መዘጋጀት እንዳለባችሁ፤ እንዲሁም ምን ማድረግ እንደሚኖርባችሁ የሚጠቁም ጽሁፍ ይዘን ለመቅረብ ቃል በመግባት ዛሬ የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን ስለሠሩ ተማሪዎች በጥቂቱ የምናስተዋውቃችሁ ይሆናል።
ሳለአምላክ ምስጋናው ይባላል። ጆይንት ሰክሰስ አካዳሚ ትምህርት ቤት ነው የሚማረው። ለፈጠራ ሥራ የተለየ ፍቅር አለው። ፍቅር ብቻ ሳይሆን ችሎታ እንዳለውም በተግባር አሳይቷል። በ9ኛው ከተማ አቀፍ የሳይንስ ፈጠራ ሥራ አውደ ርዕይ ላይ ተሳትፏል። ተማሪው የሠራው ዘመናዊ መጸዳጃ ቤት ሲሆን፤ ይህ መጸዳጃ ቤት ከሌሎች ለየት ያለ እንደሆነ ይናገራል። መፀዳጃ ቤቱ መስማት ለተሳናቸው ወይም መናገር ለማይችሉ ሰዎች በመጸዳጃ ቤት ውስጥ ሰው እንዳለ መብራት በማብራት የሚያመላክት ነው። ለአይነ ሥውራንም ድምጽ በማሰማት ከሌሎች ጋር የሚግባቡበትን የፈጠራ ሥራ ሰርቷል።
ሌላው ከመጸዳጃ ቤት ጋር በተያያዘ አንዳንድ ሠዎች መጸዳጃ ቤት ከገቡ በኋላ ውሃ አይደፉም። ንጽህናው የተጠበቀ መጸዳጃ ቤት እንዲኖር አንድ ሰው የውሃ መድፊያውን ካልተጫነ በሩ እንዳይከፈት የሚያደርግ የፈጠራ ሥራ ሰርቷል። በዚህ ፈጠራ ሥራ ውሃ መድፋት እንደሚገባ ግንዛቤ ለመስጠት በሚገባ ይጠቅማል ብሎ ያምናል። እርሱ ይህን የፈጠራ ሥራ ለመሥራት ምክንያት የሆነው በብዙ አካባቢዎች ላይ ንጽህናቸውን ያልጠበቁ መጸዳጃ ቤቶች መኖራቸውን በማየቱ ነው። ደግሞም ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ባለመሆናቸው ይህ ነገር ሊታረም ይገባል በሚል መልካም ሃሳብም ተመሥርቶ ነው።
ብሌን አይቼው ሌላኛዋ የፈጠራ ችሎታ ያላት ተማሪ ናት። እርሷ የሠራችው አራት ነገር በአንዴ የሚይዝ ዕቃ ነው። ሳጥን በሚመስል ዕቃ ውስጥ የሻይ ማፍያ፣ ቡና ወይም ውሃ ማፍያ፣ ቡና መፍጫ ስቶቭ ነው። የስራ ፈጠራው በአንድ ቦታ ላይ ቡናው ተቆልቶ፣ ተፈጭቶ እና ተፈልቶ ማጠናቀቅ የሚቻልበት እንደሆነም አስረድታለች። በቀጣይ በፈጠራ ሥራ ላይ በስፋት በመሠማራት፤ እንዲሁም ችግር ፈቺ የሆኑ ምርቶችን የማድረስ ፍላጎት እንዳለት የገለጸችው ተማሪ ብሌን ሌሎች ልጆችም የሚሠሩትን የፈጠራ ሥራ ሌሎች አይተው ሃሳብ እንዲሰጧቸው እንዲያደርጉ ትመክራች።
ዲናኦል መንግሥቱ በአንዶሪ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የስምነተኛ ክፍል ተማሪ ነው። ‹‹ዲናር›› ብሎ የሰየመው በአንድ ጊዜ ሁለት ነገር መሥራት የሚችል ኦቭን (ምግብ ማብሰያ) ነው የሠራው። ጥቅሙ ከኦቭን በላይ ነው ያለው ተማሪው፣ በአንድ ጊዜ ከላይ እንጀራ የሚጋግር፤ ከሥር ደግሞ ድፎ ዳቦ ለመድፋት የሚያስችል ነው። የሠራው የፈጠራ ሥራ በአነስተኛ ዋጋ እና ከወዳደቁ ሽቦዎች የተሠራ እንደሆነም ተናግሯል። በተለይም ጠባብ ቤት ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች በአንድ ዕቃ ሁለት ነገር መሥራት የሚችል በመሆኑ ለጠባብ ቤት እጅግ ተመራጭ እንደሆነ ይገልጻል። በተጨማሪም በአንድ ኤሌክትሪክ ሃይል ሁለት ነገር በአንድ ጊዜ የሚሠራ ስለሆነ የኤሌክትሪክ ፍጆታን በመቆጠብ በኩልም የሚሠጠው ጥቅም እንዳለው ይናገራል።
የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ዲናኦል ለወደፊት በሶፍት ዌር ኢንጂነሪንግ ተመርቆ አገሩን ለማገልገል ከፍተኛ ፍላጎት አለው። በተጨማሪም ፍላጎቱን ለማሳካት በርትቶ እየተማረ እንደሆነ ይናገራል። እንደ እርሱ የፈጠራ ሥራ የሚሠሩ ወይም የሚሞክሩ ተማሪዎች የሠሩትን ለመምህራን እና እውቀቱ ላላቸው ሰዎች በማሳየት፣ በሚዘጋጁ አውደ ርዕዮችም ሆነ ውድድሮች ላይ ቢሳተፉ እሱ እንዳገኘው የልምድ ልውውጥ እና አይተው የማያውቁትን የፈጠራ ችሎታዎችን ለማየት እንደሚያግዛቸው ይጠቁማል።
ልጆችዬ፣ የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን ለመሥራት ከሚጥሩ ተማሪዎች ምን ተማራችሁ? ትምህርት ከመማር ጎን ለጎን የፈጠራ ሥራ መሥራት እንደሚቻል እና በቀላል ወጪ የሚሠሩ የፈጠራ ሥራዎችን መከወን እንደሚቻል በሚገባ ተምራችኋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ልጆችዬ፣ ለዛሬው በዚሁ ብንሠነባበት መልካም አይመስላችሁም? በጣም ጥሩ። ሳምንት በሠላም ለመገናኘት እንዲያበቃን በመመኘት እስከዛው መልካም የእረፍት እና የትምህርት ሳምንት ይሁንላችሁ እንላለን!!
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 25 ቀን 2016 ዓ.ም