ሉአላዊነት የአንድ ሀገር የክብር፣ የአይነኬ ስም ነው። እኛ መጠሪያ ስም እንዳለን ሁሉ የሀገራት የክብር ልኬት የልኡላዊነት ድንበራቸው ነው። ሁሉም ሀገራት በዚህ ስም በኩል ሀገርና ታሪክ ያቆዩ ናቸው። ይህ የክብር ስም የሀገር ባለአደራ ከሆነው የመከላከያ ሰራዊት ጋር የተስማማ የአንድ ሳንቲም መንታ ገጽታ መሆኑ ደግሞ ሌላው ውበቱ ነው።
ኢትዮጵያ የሚለው የነጻነትና የእኩልነት፣ የፍትህና የሚዛናዊነት ስም በዚህ እውነት በኩል ተንጸባርቅ ብኩርናን ያገኘ ነው። ማናቸው ላለን እነዛ የነጻነት አድባሮች፣ የሰብዐዊነት ውሀ ልኮች፣ በብዙሀነት ለምልመው፣ በታሪክ አሽተው፣ በአብሮነትና በክብር ፊተኝነትን ያገኙት ሀበሾች ናቸው የምንባለው የሀገር መከታ በሆነ የመከላከያ ሰራዊታችን ነው።
አለም ላይ የጀግንነት ስም እያገኙ ከመጡ ጥቂት የሰላም አርበኞች መሀል የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አንዱ ነው። መነሻውን ሀገርና ህዝብ አድርጎ የተለያዩ ግዳጆችን በብቃት በመወጣት የሀገርና ህዝብን ክብር በማስጠበቅ ረገድ የተዋበ ስም ጽፏል። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለየ አመራርና ተደራሽነቱ በሰፋ ሀገር ተኮር ፍልስፍና ከነበረበት ልቆ የታየበት ሁኔታ አለ።
ራሱን በእውቀት እና በሀገር ፍቅር ስሜት አርቆ፣ በተለያዩ ስልጠናዎችና በዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች ዳብሮ ቁመናውን ከፍ ያደረገ ፤ ከሀገር አልፎ ለሌሎች የአለም ሀገራት ምሳሌ እስከመሆን የደረሰበትን የቅርብ ጊዜ ታሪኩን ማንሳት ይቻላል።ከተለያዩ የአለም ሀገራት ጋር የልምድ ልውውጥ በማድረግ፣ ሰላም ተኮር እሳቤዎች ላይ በማተኮር፣ ከጦርነት በፊት ሰላም በሚል መርህ በሰፋና በገዘፈ መረዳት ውስጥ የሀገር ባለውለታነቱን አስመስክሯል።
ሀገራችን ችግር ውስጥ በነበረችባቸው ጊዜያቶች እንዲሁም አሁን ባለንበት ሁኔታ ዋጋ በመክፈል የፊተኝነት ድርሻውን እየተወጣ ይገኛል። ይሄ በሞት የተሰላ የሀገር ፍቅር ውለታ ወታደር ሲሆን ለሀገር የገባውን ቃል በተግባር የማሳየት ታማኝነት ነው። ይሄ ታማኝነት ወደፊትም የሚቀጥል ሀገርና ህዝብ እስካሉ ድረስ በሰራዊቱ ልብ ውስጥ የሚኖር ነው።
ሉአላዊነት የአንድ ሀገር እና ህዝብ የማንነት ቀለም ነው። መከላከያ ሰራዊት የሚለው ስም ደግሞ ይሄ ቀለም እንዳይደበዝዝና ደምቆ እንዲቀጥል የሚያደርግ ባለአደራ ነው። የሀገርን ዳር ድንበርና የህዝቦችን ደህንነት ከማስጠበቅ አኳያ ሚናው የላቀ ነው። ይህ ደግሞ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚስማሙበት የጋራ እውነታ ነው።
ለሀገር የከፈለውን የአካልና የህይወት መስዋዕትነት በመጣንባቸው የተለያዩ ተግዳሮቶች መሀል አረጋግጠናል። ይህ በማንም ሳይሆን በመከላከያ ሰራዊት ብቻ የሚከፈል የሉአላዊነት ክፍያ ነው። ሀገርን ነቅቶና በቅቶ በመጠበቅ እኛ ሰላም ወጥተን እንድንገባ ራሱን የሰጠ ባለውለታችን ነው።
ከዳር ድንበር ማስጠበቁ ጎን ለጎን ከሀገር ለሀገር በሆነ መነሻ ሀሳብ ህዝብ እያገለገለ የሚገኝባቸው በርካታ ማህበራዊ ተሳትፎዎችም አሉት። ከአርሶ አደሩ ጋር አብሮ በማረስና በመጎልጎል በምርት ጊዜም ምርት በመሰብሰብ ረገድ ሚናውን አሳይቷል። የአቅመ ደካሞችን ቤት በመስራትና በማደስ በተፈለገበት በየትኛውም ቦታ ላይ በንቃት በመገኘት አስፈላጊነቱን በተግባር በማሳየት ላይ ይገኛል።
በአንድ ሀላፊነት ላይ ብቻ ያረጋ እኔ የህዝብ ነኝ በሚል ስሙ ራሱን ለሀገርና ህዝብ ሰጥቶ እየደከመ ያለ ሁለገብ ባለሙያ ነው።ባለው የአመራርነት ጥበብ፣ የጦር ክህሎት፣ ጀግንነትና የዲሲፕሊን ልህቀት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በሌሎች ሀገራት በኩል ተመራጭና የአብረን እንስራ ጥያቄ እየቀረበለት ይገኛል። ከጥበብ እና ክህሎት ጋር መከላከያ ሰራዊት መሆን ብዙ ጊዜ የማይቻል ከተቻለም ለአንዳንዶች ብቻ የሚቻል የጥልቅ ስልሳሌ ነጸብራቅ ነው ።
አንድ ሰራዊት ክህሎትን ከዲስፕሊንና ከእውቀት ጋር ካላጣመረ በስተቀር ዘመናዊና የጦር መሳሪያ ስለታጠቀና በሎጀስቲክ ውስጥ ስላለፈ ብቻ ብርቱና አስተማማኝ አይሆንም።የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ደግሞ ብዙዎች ተመኝተው ባጡት የስነልቦና ከፍታ እና የዲሲፕሊን ልህቀት ውስጥ ከእውቀት እና ከስልሳሌ ጋር የታደለ ሆኖ ከፊት የሚቀመጥ ሰራዊት ነው። አሁን ባለው ወታደራዊ አቋም ለየትኛውም ተልዕኮ ብቁ እንደሆነ የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው። በተግባር ተፈትኖም አቅሙን ያስመሰከረ ጀግናና ብልሀተኛ የሚል ስምን ያተረፈ ሰራዊት ነው።
ሰላምን ከማስከበር እና የሀገርን ሉአላዊነት ከማስጠበቅ ባለፈ በተለያዩ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ በስፋት በመሳተፍ አለኝታነቱን ያሳየ እና እያሳየ ያለም ሰራዊት ነው። ከሰሞኑ ደግሞ 61ኛውን የአፍሪካ ቀንን በማክበር ግዝፈቱ እስከየት እንደሆነ አሳይቷል። በመከላከያ የውጪ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት የተዘጋጀው ይህ ዝግጅት አፍሪካን ያሞካሸ፣ አንድነትን የፈጠረ፣ መጪውን ጊዜ አቃፊነት ባለው ወታደራዊ ስርዐት አብሮ ለመስራት ያስተሳሰረ ነበር።
መነሻውን የአድዋ ሙዚየም ያደረገው የአፍሪካ ቀን አምባሳደር ጀማሊዲን ሙስጠፋን እና አምባሳደር ግሩም አባይን ጨምሮ ተቀማጭነታቸው በአፍሪካና ከአፍሪካ ውጪ የሆኑ የአፍሪካ፣ የእስያ፣ የአውሮፓ ወታደራዊ አመራር አምባሳደሮችን በመጋበዝና በማሳተፍ ስለአፍሪካ የአንድነትና የአብሮነት ትስስር አውግቷል።
በዝግጅቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የመከላከያ የውጪ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ተሾመ ገመቹ ‹የአፍሪካ አንድነት ትብብርና የአፍሪካ በጋራ መቆም ለፓን አፍሪካኒዝም ወሳኝ እንደሆነ እና ወታደራዊ ተቋማትም ትልቅ ድርሻ አላቸው› ሲሉ በንግግራቸው አስተላልፈዋል። ቀጥለውም ‹ነጻና አንድነቷ የተጠናከረ አፍሪካን መፍጠሪያ ጊዜው አሁን ነው› ሲሉ ንግግራቸውን ቋጭተዋል።
‹ኢትዮጵያ በተለያዩ የአፍሪካ ክፍሎች ያሉ ቅኝ ገዢዎችንና የአፓርታይድ አራማጆችን በመዋጋት ንቁ ተሳትፎ እንዳደረገች በማስታወስ፣ አህጉሯዊ ተቋማት ግባቸውን እንዲመቱ ያላሰለሰ ሚና እየተጫወተች በመሆኗ ሚናዋን አጠናክራ እንድትቀጥል የአደራ መልዕክት ያስተላለፉት ደግሞ አምባሳደር ጀማሉዲን ሙስጠፋ ናቸው። በኢትዮጵያ የሴራሊዮን ወታደራዊ አታሼ ብርጋዴር ጀነራል አቡበከር ኩንቴ በበኩላቸው ‹የበአሉ መከበር በአፍሪካ ነጻነትና ተግዳሮቶች እልባት የሚሰጥ በመሆኑ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጋር በጋራ ለመስራት እድል የሚሰጥ ነው› ሲሉ ተናግረዋል።
አቃፊ በሆነ መርህ አፍሪካን በአንድ አላማና ግብ ማስተሳሰር የዝግጅቱ ዋና አላማ ሆኖ የሚነሳ ሲሆን ‹የአፍሪካ ቀን በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ ያለው ድርሻ› በሚል ርዕሰ ሀሳብ ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይትና አቅጣጫ ተቀምጦበታል። አፍሪካ ነጻነቷን ካወጀችበት ማግስት ጀምሮ የፈነጠቀው የነጻነት ጮራ አፍሪካ ቀኗን እንድታከብር እድል እንደሰጣት እንዲሁም የዚህ ቀን መከበር በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ ስላለው ዘርፈ ብዙ ትርጉም ያወሳል።
ከጥናታዊ ጽሁፉም ሆነ ከዝግጅቱ ላይ የተወሰዱ አጠቃላይ አበይት ቁም ነገሮች በርካታ ሲሆኑ አፍሪካን በመተማመን፣ በአንድ በጎ አላማ ማስተሳሰር የሚለው ግን የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል። ሀሳቡን እውን ለማድረግ ዲፕሎማሲና የጋራ መርህ እንደሚያስፈልግ የተጠቆመ ሲሆን የጋራ ተጠቃሚነት የሚስተዋልበት የአብሮነት ማዕቀፍም ቀጣዩ የቤት ስራ እንደሆነ በመተማመን ተቋጭቷል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በሁሉም መልኩ የነቃና የበቃ እንዲሆን በተለያዩ ስልጠናዎች በኩል እያለፈ ነው። ከዚህ ጋር አብሮ የሚነሳው ዘመኑን የዋጀ የኮማንዶና የአየር ወለድ ስልጠናዎች ናቸው። በወታደራዊና ባህር ሀይል ኮማንዶ፣ በጸረ ሽብር፣ አየር ወለድ፣ እንዲሁም በተለያዩ ስልጠናዎች ብቁ ሙያተኞች እየወጡ እንደሆነ የመከላከያ ኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጀነራል ሹማ አብደታ ተናግረዋል።
ቀጠናዊና አለም አቀፍ ሁኔታዎችን ባገናዘበ መልኩ የአሰልጣኞችን አቅም ለማሳደግ ወደተለያዩ ሀገራት ተልከው ልምድ እየቀሰሙ፣ ከተለያዩ ሀገራትም አሰልጣኞችን በማምጣት የልምድ ልውውጥ በማድረግ የሰራዊቱን ቁመና በማሳደግ ላይ እንደሚገኙ አክለዋል።
ሌላው የመከላከያን ስም አጉልተው ካስጠሩ ወቅታዊ ጉዳዮች መሀል የመከላከያ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አንዱ ነው። ከተጀመረ ሰላሳ አምስት አመት የሆነው ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል በትውልዱ ጥረት ተጠናቆ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ከሰሞኑ ለምርቃት በቅቷል።
ይሄም ‹ሰው ራዕይ ካለውና ህዝብን ማዕከል አድርጎ ስራዎችን ከጀመረ ጊዜ ይወስድ ይሆናል እንጂ ትውልድ ይጨርሰዋል› በሚል የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ንግግር የተመረቀው ሆስፒታል በቀጣይ ሀገርና ማህበረሰብን በማገዝ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ተጠቁሟል። ለሰራዊቱ ብቻ ሳይሆን ለማህበረሰቡም ከፍተኛ ጥቅም እንደሚሰጥ የተናገሩት ደግሞ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ብርሀኑ ጁላ ናቸው።
ከረጅም ጊዜ በኋላ ተገንብቶ ስራ የጀመረው ይሄ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ግዙፍና በውስጡም ዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎችን ከብቁ ባለሙያዎችና አገልግሎት ጋር የያዘ መሆኑ አሁን ላለው ትውልድ ትሩፋቱ ላቅ ያለ ነው። መከላከያ ሰራዊት በቀጣይም ከሰላምና ከዳር ድንበር ማስጠበቁ ጎን ለጎን እንዲህ ባሉ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ተሳታፊ በመሆን በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ሚናውን እንደሚወጣ እናምናለን።
ሀገር መልክ ካላት ወይም ደግሞ በሆነ አንድ ሀገርኛ መልክ እንመስላት ካልን መከላከያ ሰራዊትን ነው የምትመስለው። ከብሄርና ከጎሳ፣ ከማንነትና ከዘረኝነት ጸድቶ ኢትዮጵያዊነትን ብቻ ባለ እውቀትና አስተውሎት ከትላንት ወደዛሬ የመጣ ወደነገም የሚሄድ ፋና ወጊ አለኝታችን ነው። ይህ ስም፣ ይሄ ቀለም በሀገር ፍቅር ዳብሮ በሉአላዊነት የቆነጀ የሁላችን መልክ ነው። ስለሀገር ነፍሱን አስይዞ፣ ጨርቅ ማቄን ሳይል ስለእኛ በዱር በገደል ሲዋደቅ የኖረ የሰላም ዋስትናችን ነው።
እንዲህ ላከበረን አካልና ነፍስ ከልብ ወዲያ ስጦታ የለም። ‹‹እናመሰግናለን›› በምትል ላመል አንደበት ውለታውን ስንዘክር እንኖራለን። አንዳንድ ነፍሶች እንዲህ ናቸው ስለሌላው ኖረው የሚያልፉ። ስለሌላው ክብርና ሰላም ራሳቸውን በመከራ ውስጥ የሚያሳልፉ። የኩራትና የልዕልና፣ የነጻነትና የአይበገሬ ምንጫችን የሆነው መከላከያ ሰራዊት ከህዝብ ለህዝብ በሆነ ሚናው እየተወጣ ላለው ሃላፊነቱ እያመሰገንን በቀጣይም አኩሪና አስተማማኝ እንደሚሆን እምነቴ ነው ።
ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)
አዲስ ዘመን ግንቦት 24/2016 ዓ.ም