የኅብረተሰብ ተወካዮች ከባለድርሻዎች ጋር የከተማዋን አጀንዳ ለማቅረብ ይወያያሉ

  • የባለድርሻዎች የውይይት መድረክ ተጀምሯል

አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ማህበረሰብ ተወካዮች ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ የከተማዋን የሀገራዊ አጀንዳ ለማቅረብ እንደሚወያዩ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ፡፡ የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ ትናንት ተጀምሯል፡፡

በውይይት መድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን፤ በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ከአዲስ አበባ 119 ወረዳዎች የተወጣጡ የኅብረተሰብ

ተወካዮች ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሰባሰብ የአዲስ አበባ ከተማ የሀገራዊ አጀንዳ ለማቅረብ እንደሚወያዩ አመላክተዋል፡፡

በሀገር እድገትና ሰላም ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሰዎች በምክክሩ ያላቸው ድርሻ በኮሚሽኑ ትልቅ ቦታ እንደተሰጠው የገለጹት ፕሮፌሰሩ፤ኮሚሽኑ የማህበረሰብ ተወካዮች ከባለድርሻ አካላቶቹ ጋር በቀጣዮቹ ቀናት መክረው ለአጀንዳ ስብሰባው የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እንደሚጠብቀው ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ ሥራዎችን በአራት ትልልቅ ምዕራፎች በመከፋፈል የቅድመ ዝግጅት ፣የዝግጅት፣የምክክርና የትግበራ እና የክትትል ሂደት በማለት ሥራውን መሥራት መጀመሩን አስታውሰው፤ አሁን የቅድመ ዝግጅት እና የዝግጅት ምዕራፎችን በማጠናቀቅ ወደ ምክክር ምዕራፍ መግቢያ መድረሱን ጠቁመዋል፡፡

ኮሚሽኑ ከ44 ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በቅርበት በመሥራት የዩኒቨርሲቲዎቹን ምሁራንና ሎጅስቲክስ መጠቀም መቻሉን ተናግረው፤ በቀጣይነትም አምስት ትልልቅ ተባባሪ አካላትን የፖለቲካ ፓርቲዎች፣የሃይማኖት ተቋማት፣መምህራንን እና እድሮችን በመለየት ወደዚህ ሥራ ማስገባት መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በ10 ክልሎች እና በሁለቱ ከተማ መስተዳድሮች የተሳታፊዎች ልየታና መረጣ ተካሂዶ የአዲስ አበባ የአጀንዳ ስብሰባና የምክክር ምዕራፍ እየተከናወነ መሆኑን የተናገሩት ፕሮፌሰር መስፍን፤ አንድ ሺህ በሚሆኑ ወረዳዎች ኮሚሽኑ ሥራዎችን መሥራቱን ገልጸዋል፡፡

አጀንዳ በአዋጁ መሠረት ከታች ወደ ላይ የሚሰበሰብ መሆኑን ተናግረው፤ አርብቶ አደሩን፣ አርሶ አደሩን፣ ሴቶችን፣ ወንዶችን፣ አካል ጉዳተኛዎችን፣አረጋውያንንና ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ባሳተፈ መልኩ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የማህበረሰብ የተቋማት መሪዎችን፣ምሁራንን እና ልሂቃንን በማግኘት በጎንዮሽም የአጀንዳ ስብሰባ እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በመድረኩ የተሳተፉት ባለድርሻ አካላት በአዲስ አበባ ከተማ ላይ የሚንቀሳቀሱ ሲቪክ ማህበራት ፣ የሃይማኖት ተቋማት ፣የፖለቲካ ፓርቲዎች ፣የአካል ጉዳተኞች ማህበራት፣የሴቶች ማህበራት ፣ወጣቶች፣ መምህራን፣የቀድሞ ሠራዊት ፣ሠራተኞች፣ የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶች፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት፣የአዲስ አበባ ከተማ ሥራ አስፈጻሚ እንዲሁም የተለያዩ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ናቸው።

መዓዛ ማሞ

አዲስ ዘመን ግንቦት 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You