የፋይናንስ አቅርቦት – የአምራች ዘርፉ የጀርባ አጥንት

በምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ጉልህ ሚና ካላቸውና የጀርባ አጥንት ሆነው ከሚያገለግሉ ግብዓቶች መካከል አንዱ የፋይናንስ አቅርቦት ነው። ይሁንና በኢትዮጵያ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ እድገት ላይ ከተጋረጡ ዋና ዋና ችግሮች መካከል አንዱ የፋይናንስ አቅርቦት እጥረት ሆኗል። ይህ ችግር ከሌሎች የዘርፉ ተግዳሮቶች ጋር ተደምሮ ኢንዱስትሪዎች የአቅማቸውን ግማሽ ያህል ብቻ እንዲያመርቱ እንዲሁም የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከአጠቃላይ ጥቅል ሀገራዊ ምርት ያለው ድርሻ ዝቅተኛ እንዲሆን አስገድዷል።

የኢንዱስትሪው ዘርፍ ችግሮችን ለማቃለል እየተተገበሩ ከሚገኙ የመፍትሄ እርምጃዎች መካከል አንዱ በሆነው ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሀገራዊ ንቅናቄ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል በፋይናንስ አቅርቦት ረገድ የሚታዩ ችግሮችን በቅንጅታዊ አሰራር መፍታት የሚለው ይጠቀሳል።

በአሁኑ ወቅት በቂ የፋይናንስ አቅርቦት የሌለው የአምራች ዘርፍ ሀገራዊ የማምረት አቅምን ማሳደግና መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግርን እውን ማድረግ አይችልም። ይህን ታሳቢ በማድረግ የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለመደገፍ የተረጋጋ የዋጋ ሁኔታና የውጭ ምንዛሬ ሥርዓትን የማስፈን እንዲሁም የፋይናንስ ዘርፉን ጤናማነት የመጠበቅ ሥራዎች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እየተሠራባቸው እንደሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ ይገልፃሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት፣ የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ፣ የተረጋጋ የዋጋ ሁኔታ እና ጤናማ የፋይናንስ ሥርዓት የሚፈልግ በመሆኑ ባንኩ እነዚህን ጉዳዮች ለማሳካት የተለያዩ የአሠራር ማሻሻያዎችን አድርጓል። ይህም ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የፋይናንስ ተደራሽነት ጉልህ ሚና አለው።

የባንኩ ገዥ ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ የአምራች ዘርፉን በልዩ ትኩረት ለመደገፍ እድል እንደሚፈጥር ይገልፃሉ። ብሔራዊ ባንክ የተረጋጋ የማክሮ-ኢኮኖሚ ከባቢ እንዲፈጠር የማድረግ ኃላፊነቱን ለመወጣት የወሰዳቸው እርምጃዎች በአምራች ዘርፍ ኢንቨስትመንት የሚሰማሩ ባለሀብቶች ቁጥር እንዲጨምር አግዟልም ይላሉ።

‹‹ብሔራዊ ባንክ የተረጋጋ የማክሮ-ኢኮኖሚ ከባቢ እንዲፈጠር የማድረግ ኃላፊነት አለበት። ባንኩ የተረጋጋና ስርዓት ያለው የገንዘብ ፖሊሲ፣ ጤናማ የፋይናንስ ስርዓት እንዲሁም አመርቂ የኢንቨስትመንት ከባቢ እንዲፈጠር የተለያዩ ተግባራትን ያከናውናል›› ሲሉም ይናገራሉ። የተረጋጋ የማክሮ-ኢኮኖሚ ከባቢ ከተፈጠረ፣ ባለሀብቶች በአምራቹም ሆነ በሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ይበረታታሉ። ባንኩ በሀገሪቱ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ እንዲኖር በማድረግ የተረጋጋ የዋጋ ሁኔታ እንዲፈጠር እና የብድር አቅርቦት እንዲስተካከል በማድረግ ረገድ ጥሩ ውጤቶችን አስመዝግቧል በማለት ያብራራሉ።

ባለፈው ዓመት የነበረው 33 ነጥብ 5 በመቶ አጠቃላይ የዋጋ ንረት ዘንድሮ ወደ 23 ነጥብ 3 በመቶ ቀንሷል። ምግብ ነክ ባልሆኑ እቃዎች ላይ የነበረው 36 ነጥብ 1 በመቶ የዋጋ ንረትም ወደ 18 ነጥብ 1 በመቶ ዝቅ ብሏል። በበጀት ዓመቱ ማጠናቀቂያ ላይ አጠቃላይ የዋጋ ግሽቱን ወደ 20 በመቶ ለመቀነስ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል። እንዲህ ዓይነት የተረጋጋ የዋጋ ሁኔታ ሲኖር የአምራች ዘርፉ ኢንቨስትመንት እድገት ያስመዘግባል፤ በገንዘብ ፖሊሲው ላይ የተከናወኑት ተግባራትም ለአምራች ዘርፉ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያበረከቱ ናቸው።

እንደአቶ ማሞ ማብራሪያ፣ መረን የለቀቀውን የብድር ስርዓት ለማስተካከል የተወሰዱ እርምጃዎች የዋጋ ንረት እንዲረጋጋ አስተዋፅዖ ከማበርከታቸው ባሻገር ባንኮች ከሚያቀርቡት ብድር ውስጥ ለአምራች ዘርፉ የበለጠ ትኩረት እንዲሰጡ እገዛ አድርገዋል። የባንኮች ብድር አሰጣጥ ለተረጋጋ የፋይናንስ ስርዓት ወሳኝ ግብዓት ነው። ባንኮች በተገቢው መልኩ ለአምራች ዘርፉ ብድር ሲሰጡ የፋይናንስ ስርዓቱ ጤናማ ይሆናል።

በአምራች ዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች ብድር ሲጠይቁ በባንኮች የሚጠየቁት የብድር ዋስትና ቀላልና ቀልጣፋ የሚያደርጉ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም አቶ ማሞ ያመለክታሉ። የፋይናንስ ዘርፉ በቂ የፋይናንስ አቅርቦትን እውን በማድረግ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ትርጉም ባለው መልኩ እንዲደግፍ የሚያስችሉ እርምጃዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ይገልፃሉ።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለአምራች ኢንዱስትሪው የፋይናንስ አቅርቦት ምንጭ ከሆኑ ተቋማት መካከል አንዱ ነው። የባንኩ ፕሬዝደንት ዶክተር ዮሐንስ አያሌው፤ ንቅናቄው አምራቾች የሚያጋጥማቸውን የፋይናንስ እጥረት ችግር በተቀናጀ መልኩ ለመፍታት እንደሚያግዝ ይገልፃሉ። ባንኩ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ለአምራች ኢንዱስትሪው ብድር እያቀረበ እንደሆነም ይናገራሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት፣ የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ምርታማነትን በማሳደግ፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር እና የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር እውን እንዲሆን በማድረግ ለሀገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገት ወሳኝ ድርሻ ያለው መሆኑ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ዘርፉን ለማሳደግ

ከፍተኛ ብድር እየሰጠ ይገኛል። ባንኩ በብድር አቅርቦት ለአምራች ኢንዱስትሪው የተለያዩ ማበረታቻዎችን ይሰጣል። ብዙዎቹ አምራቾች በግብርናው ዘርፍ ላይ የተመሰረቱ በመሆናቸው ለግብርና ዘርፍ ተበዳሪዎች በዝቅተኛ ወለድ ብድር እያቀረበ ይገኛል። ፕሮጀክቶችን እንደብድር ዋስትና በመያዝ ተጨማሪ የንብረት ዋስትና ላለመጠየቅ የሚያስችል አሰራር ተዘርግቷል።

‹‹አምራቾች ካላመረቱ ሀገሪቱ በገቢ ምርቶች ላይ ጥገኛ ትሆናለች፤ የውጭ ምንዛሬ እጥረትም ይከሰታል›› ሲሉ ጠቅሰው፣ ልማት ባንክ ለአምራቾች ብድር በማቅረብ የምርት ስራቸውን በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲያከናውኑ በማድረግ በገቢ ምርቶች ላይ የሚታየውን ጥገኝነት ለመቀነስና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለመጨመር ጥረት እያደረገ መሆኑን ያስረዳሉ። ከለውጡ በኋላ የባንኩ አፈፃፀም መሻሻሉንም ገልጸው፣ ‹‹የብድር አቅርቦቱም ሆነ ትርፉ ጨምሯል፤ ካፒታሉ 38 ቢሊዮን ብር ደርሷል፤በዓመት ከስድስት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር በላይ እያተረፈ ይገኛል፤ እስከ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ማበደር የሚችልበትንም አቅም ፈጥሯል።›› በማለት ያስረዳሉ።

የባንኩ ፕሬዝደንት እንደሚገልፁት፣ ባንኩ በ2015 የበጀት ዓመት ካቀረበው 46 ቢሊዮን ብር ብድር ውስጥ 35 ቢሊዮን ብር ለአምራች ዘርፉ የቀረበ ነበር። በዘንድሮው የበጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት ውስጥ በባንኩ ከጸደቀው የ44 ቢሊዮን ብር ብድር ውስጥ 30 ቢሊዮን ብር ለአምራች ዘርፉ የተሰጠ ነው። ባንኩ ለአምራች ዘርፉ ከፍተኛ ብድር ማቅረቡ ተኪ ምርቶችን በማምረትና የወጪ ንግድን በማሳደግ ለመዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግር አቅም ለመፍጠር ያግዛል።

‹‹አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በሁሉም ክልሎች ተቋቁመው ይሰራሉ። ስለሆነም እነዚህ አምራቾች ፍትሃዊነትን በማስፈን ረገድ ቁልፍ ሚና አላቸው። በበጀት ዓመቱ ከፀደቀው ብድር ውስጥ 18 ቢሊዮን ብር የሚሆነው ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የተሰጠ ነው። የኢንተርፕራይዞቹን ውጤታማነት ለማሳደግ የሼድ ግንባታ ተግባር ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል›› ይላሉ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም በፋይናንስ አቅርቦት ረገድ ለአምራች ኢንዱስትሪው ባለውለታ ነው። በ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ የሚከናወኑ ተግባራት የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ትክክለኛ መስመር ለማስያዝ አቅም እየፈጠሩ እንደሆነ የሚናገሩት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝደንት አቶ አቤ ሳኖ ናቸው። አቶ አቤ እንደሚሉት፤ ንቅናቄው በዘርፉ ባለድርሻ አካላት መካከል ቅንጅት እንዲኖር ማስቻሉ ትልቅ እመርታ ነው። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሚያቀርበው ብድር ውስጥ ግማሹ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚሰጥ ነው፤ ከዚህም ውስጥ አብዛኛው ፋይናንስ ለኃይል አቅርቦት የሚውል ነው። ከባንኩ ብድር ውስጥ 90 በመቶው የረጅም ጊዜ ብድር ነው።

ባንኩ ለአምራች ዘርፉ በልዩ ሁኔታ ብድር የሚያቀርብበትን አሰራር ለመዘርጋት ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ፕሬዝደንቱ ያመለክታሉ። የሀገር ውስጥ ጥሬ እቃዎችን ለሚጠቀሙ አምራቾች ቅድሚያ ለመስጠት እየሰራ መሆኑን በመጥቀስም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቀጣይ አምራች ዘርፉን በፋይናንስ አቅርቦት ለመደገፍ ስለሚያደርጋቸው ጥረቶች ያስረዳሉ።

የሀገር ውስጥ ጥሬ እቃዎችን የሚጠቀሙ አምራቾችን የማበረታታት ተግባር በልዩ ትኩረት ሊከናወን እንደሚገባ ይናገራሉ። የታክስና ጉምሩክ ጉዳዮችም ተገቢውን ትኩረት ማግኘት አለባቸው። ከዚህ በተጨማሪም በአምራች ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሀብቶች በበቂ ጥናትና ዝግጅት ላይ ተመስርተው ወደዘርፉ እንዲገቡ ይመክራሉ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው፣ ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ በአስር ዓመት የልማት እቅድ የተቀመጡ ዋና ዋና ግቦችን ማለትም የኢንዱስትሪ ዘርፍ የማምረት አቅም ማሻሻል፣ የውጭ ምንዛሬን ማሳደግ፣ ገቢ ምርትን መተካትና የሥራ እድል መፍጠር እንዲሁም በአጠቃላይ የዜጎችን ኑሮ የማሻሻል ዓላማን ይዞ የተጀመረ መሆኑን ያመለክታሉ። የፋይናንስ አቅርቦት ትልቅ ትኩረት የሚፈልግ ጉዳይ እንደሆነ ያብራራሉ። ስለሆነም መንግሥት የግሉ ዘርፍ በኢንዱስትሪው ክፍለ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚኖረውን ሚና ለማሳደግ የሚያስችል የፋይናንስ አቅርቦትን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያስረዳሉ።

የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ መጠናከር ሌሎቹን የኢኮኖሚ ዘርፎች የሚያሳድግ ግብዓት ነው። ለአብነት ያህል የግብርና ምርታማነትን ለመጨመር ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎችን እንዲሁም የአገልግሎት ዘርፉን ውጤታማነት ለማሻሻል ደግሞ የዘርፉን የስራ እንቅስቃሴ የሚያሳልጡ ግብዓቶችን በብዛት፣ በጥራትና በፍጥነት የሚያመርት አምራች ዘርፍ ያስፈልጋል። አምራች ዘርፉ ከሚጠናከርባቸው መንገዶች መካከል አንዱ በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች በተለይ በፋይናንስ አቅርቦት ረገድ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ማድረግ ነው።

ፖሊሲዎችን ጨምሮ ምቹ ሕጋዊ ማዕቀፎችን ማዘጋጀት፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦቶችን ማስፋፋት፣ የብድር አቅርቦትን ማመቻቸት እና ተደራሽ፣ ቀልጣፋና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት ከድጋፎቹ መካከል ይጠቀሳሉ። በኢትዮጵያም አምራች ዘርፉ የግብርናውን ሚና ተክቶ ምጣኔ ሀብቱን እንዲመራና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት እንዲመዘገብ በአምራች ዘርፉ የሚሰማሩ ባለሃብቶች በፋይናንስ አቅርቦት ረገድ ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች ፈጣንና የተቀናጀ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል።

‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሀገራዊ ንቅናቄ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ጥራትና ተወዳዳሪነት በማሻሻል ገቢ ምርቶችን የመተካት ሽፋንን የማሳደግ፣ በአለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ የኢንዱስትሪ ምርቶችን አምርቶ የመሸጥ እንዲሁም ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ የመተካትና የውጭ ምንዛሬ እጥረትን የመቅረፍ ዓላማዎቹን ሊያሳካ የሚችለው በቂ የፋይናንስ አቅርቦት ሲኖር እንደሆነ ሊዘነጋ አይገባም። ከዚህ በተጨማሪም ባለፉት አምስት ዓመታት መንግሥት ያደረጋቸው ዘርፈ ብዙ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብሮች በፋይናንስ አቅርቦት ረገድ ያሉ ችግሮችን ለማቃለል ወሳኝ ሚና ያላቸው በመሆኑ ለመርሃ ግብሮቹ ትግበራ በትጋት መስራትም ይገባል።

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን ግንቦት 22/ 2016 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You