በባህር ዳር ከ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ የኮሪደር ልማት ሊሠራ ነው

አዲስ አበባ፡ከሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ መነሻ ወጪ ባህር ዳር ከተማን ከአዲሱ ድልድይ፣ ዓባይና ጣና ጋር የሚያስተሳስር የኮሪደር ልማት ሊሠራ መሆኑን የከተማው አካባቢ ጥበቃ፣ ጽዳትና ውበት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የከተማ አስተዳደሩ አካባቢ ጥበቃ፣ ጽዳትና ውበት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብረሃም ወርቁ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ባህርዳር ከተማን ከአዲሱ ድልድይ፣ ዓባይና ጣና ጋር የሚያስተሳስር የኮሪደር ልማት ከሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ መነሻ ወጪ ሊሠራ ነው።

በኮሪደር ልማቱ የከተማዋ ሁለት ዋና መንገዶች 24 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ይሆናል ያሉት አቶ አብረሃም፤ በከተማው የሚገኙ ስድስት ክፍለ ከተሞችን ማልማት የሚያስችል ነው ብለዋል።

በልማቱ ሂደት የሚካተቱ ተጨማሪ ሥራዎች እንዳሉ ሆነው ከሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ መነሻ ወጪ የሚሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ፕሮጀክቱም ቀጣይነት ያለው በመሆኑ ከተጠቀሰው ወጪ በላይ የሚጠይቅ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።

የኮሪደር ልማቱን በተያዘው ዓመት ሰኔ ወር ለመጀመርና በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ቁርጠኝነት መኖሩን ጠቁመዋል። ከተማው በፕላን የተሠራ በመሆኑ ልማቱ ቤቶችን የማፍረስ ሂደት እንደሌለውም አስረድተዋል።

ፕሮጀክቱ የብስክሌት መስመር፣ መብራት፣ ቴሌ፣ውሃና ፍሳሽ፣ መንገድ ዳር ካሜራ በተሟላ ሁኔታ የሚሠራበት መሆኑን በመግለጽ፤ በተጨማሪም ፓርኪንግ፣ የታክሲና ባጃጅ መጫኛ፣ መዝናኛ ቦታዎችን ጨምሮ እግረኛ መንገድ፣ የአስፓልት መንገድና አረጓዴ ልማት ሥራዎች መካተታቸውን ገልጸዋል።

በፕሮጀክቱ የወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራን መሠረት አድርጎ እንደሚሠራ ጠቅሰው፤ በተለይም ነዋሪዎችን ችግር የሚቀርፉ፣ ከተማዋን ውብና ጽዱ የማድረግ የሚችሉ ሥራዎች እንደሚሠሩ ጠቁመዋል።

ባህርዳር ከተማን ለነዋሪዎች ምቹ በማድረግ ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችል ልማት መሆኑንና ልማቱ በከተማዋ ተግባራዊ ለሚደረገው የኮሪደር ልማቱ ባለሀብቶች፣ ልማታዊ ድርጅቶችን ጨምሮ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የራሳቸውን ዐሻራ ማሳረፍ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን ግንቦት 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You