ጽዱ ኢትዮጵያ – ለአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ

በዓለማችን ንፁህና ፅዱ ከሆኑ ሀገራት መካከል ጃፓን በቀዳሚነት ትጠቀሳለች። ይህቺ የሩቅ ምሥራቅ ፈርጥ ከተሞቿን፣ የተፈጥሮና የመስህብ ስፍራዎቿን ማፅዳት እንደ ሥራ ሳይሆን ልክ እንደ ባህል አድርጋ ይዛዋለች፤ ጽዱነት በእጅጉ ተዋህዷታል፡፡

ጃፓናዊያን አንድ በፍፁም የማይታሙበት ጉዳይ የቤትና የአካባቢያቸውን ፅዳት መጠበቅ ላይ ነው። ይህ ባህላቸው ታዲያ ዛሬም ለእኛ ምሳሌ ሆኖ ጥንካሬያቸውን እንድናወራላቸው አስገድዶናል። በተለይ ዛሬ ለምናነሳው የሀገራችን የንጽህና እና የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ ጃፓናዊያን ጥሩ ምሳሌ ናቸውና ጥቂት ተጨማሪ ሃሳቦችን ስለዚህች ሀገር የጽዳት ጉዳይ እናነሳና ወደ ዋናው ሀገራዊ ጉዳያችን እንሸጋገራለን።

በጃፓን ስፖርት ዝግጅቶች ምክንያት እዚህም እዚያም ቆሻሻን ማንሳት ግዴታ ሳይሆን ባህል ነው። ይህንን ከፍተኛ የንጽህና ደረጃ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ጭምር ደጋፊ ሆነው የሄዱ ጃፓናዊያን ሲተገብሩት ይስተዋላሉ። በሀገሪቱ ትምህርት ቤቶች የቡድን ፅዳት ሥራ ሁሌም ተግባራዊ ይደረጋል።

ተማሪዎች የህይወት ክህሎቶችን ለመማር ክፍሎቻቸውን ያፀዳሉ፤ የበጎ ፈቃደኞች የጽዳት ዝግጅቶች በየጊዜው ይካሄዳሉ፤ ዝግጅቶቹ ከስነምግባርና ከባህሪ ጋር የተቆራኙ ናቸው። በጎዳናዎች ላይ ምንም አይነት ቆሻሻ አይጣልም፤ በጎዳና ዳርቻና ጥጋ ጥጉ ላይ መፀዳዳት ብሎ ነገር የለም።

በጃፓን ንጽህናን መጠበቅ ለጤናና ውበት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ አዘውትሮ ማጽዳት የባክቴሪያ እና የበሽታ ስርጭትን ለመከላከል እንደሚረዳ ጃፓናዊያን ጠንቅቀው ያውቃሉ። ይህ ባህላቸው ታዲያ በቱሪዝም ዘርፍ በዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ተመራጭ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ የጃፓን ገፅታም በሚያስገርም ሁኔታ አዎንታዊ በሆነ መልኩ እንዲያድግ አስችሎታል። ለመሆኑ እኛ ኢትዮጵያውያን በዚህ ረገድ የቱ ጋ እንገኝ ይሆን?

ኢትዮጵያ የብዝሃነት መገለጫ ነች። በባህል፣ ታሪክ፣ ቅርስና ፈጥሮ ሀብት ከታደሉ ጥቂት ሀገራት መካከልም ትጠቀሳለች። ሕዝቧ የመከባበር፣ እንግዳን ከራስ በላይ አክብሮ የመቀበል፣ የመቻቻልና አብሮ የመኖር ጠንካራ ማህበራዊ መሠረት አለው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከጽዳትና አረንጓዴ ልማት አኳያ የሚከናወኑ ተግባሮች ቢኖሩም፣ ልክ እንደ ጃፓናዊያን እና ሌሎች በአካባቢ ጥበቃና ፅዳት ረገድ ስማቸው ከገነነ ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ ገና እጅግ ብዙ መስራት ይጠበቅብናል።

ከተሞቻችን ከውበትና ፅዳት አንጻር አንድ እርምጃ ወደፊት የተጠጉ አይደሉም። በዚህ ረገድ ደካማ ባህልና የትብብር ማነስ ይታይብናል፡፡ የቱሪዝም መስህብ የሆኑ መዳረሻዎቻችን ሳይቀሩ ትንሽ ሥራ በሚጠይቁ የፅዳት ጉድለቶች መስህብነታቸው ተሸፍኖ ይታያል፤ ለእዚህ ምክንያቱ ደግሞ በጽዳት በኩል ያለን ልማድና ትብብር ማነስ በምክንያት ሊጠቀስ ይችላል።

የቆሻሻ አወጋገዳችን እጅግ ደካማ የሚባል ለጤና እክልና ለአካባቢ ብከለት ጭምር የሚዳርግ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚካሄዱ ንቅናቄዎችና በጎ ጅምሮች እንዳሉ ሆነው፣ አሁንም በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ ያለን አፈፃፀም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። አዲስ አበባ በሚል በአበባ የተሰየመ ከተማ ይዘን የሕዝብ መዳረሻዎቻችን ግን ለእይታም ለጤናም ምቹ ባልሆኑ የንፅህና ጉድለቶች ውስጥ ሆነው ይስተዋላሉ፡፡

ከዚህ አንፃር ለበርካታ ዓመታት የአፍሪካ መዲና የሆነችው፣ በተፈጥሮና በታሪኳ የብዙሃንን ቀልብ የምትስበው ኢትዮጵያ ከፅዳት አኳያ በሚታዩባት ጉድለቶች ገፅታዋ ተበላሽቶ ቆይቷል። ይህን ችግር የመፍታት ሥራ በመንግሥት ትኩረት ተሰጥቶት ሲሠራበት ቢቆይም፤ ከችግሩ ስፋትና በጉዳዩ ላይ ዛሬም ካለው የአመለካከት ችግር ጋር በተያያዘ በቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ እንዲሁም በጽዳት በኩል ብዙ ርቀት መሄድ አልተቻለም፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ ተግባሮች እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ተወስደዋል ተብሎ አይታሰብም፡፡

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግን ይህንን መጥፎ ገፅታ የሚቀይሩ በጎ ጅምሮችን እያስተዋልን ነው። በኢኮሚኖሚም በማህበራዊም ዘርፎች ሁለንተናዊ እድገት

ለማስመዝገብ ከሚደረጉ ጥረቶች ጎን ለጎን በአካባቢ ጥበቃ እና ፅዱና ውብ ከተማን ለመገንባት ተግባራዊ የተደረጉ እርምጃዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው።

ውብ አሊያም ፅዱና ተፈጥሮው የተጠበቀ ሀገርና ከተሞች ለመገንባት ከምንም በላይ ትብብርና ቁርጠኝነት ያስፈልጋል። ከዚህ እሳቤ ጋር የተሳሰሩና የማህበረሰባችንን ግንዛቤ የሚቀርፁ ባህሎቻችንን አውጥተን ልንጠቀምባቸው ይገባል፤ ባህሎቻችን ይህን ለማድረግ የሚያነሱን ከሆነም ከውጪም ማምጣት ይቻላል፤ ብቻ ጽዱና ውብ እንሁን፡፡

በቅርቡ የተጀመረው የፅዱ ኢትዮጵያን መሰል ንቅናቄም በዘላቂነት የሚተገበርበት ሁኔታ መፈጠር ይኖርበታል፡፡ በዚህ ንቅናቄ ለመገንባት ለታሰቡ የመጸዳጃ ቤቶች ገቢ ለማሰባሰብ በተደረገ ጥረት ከእቅድ በላይ ሀብት ማግኘት ተችሏል፡፡ በዚያው ልክም ንቅናቄውን የሚደግፉ ሰዎችን ማፍራትም ተችሏል። ይህን ትልቅ አቅም ከፋይናንስ ድጋፉ በተጨማሪ ለማስተባበር ሥራም በሚገባ መጠቀም ይገባል፡፡

ከንቅናቄው እንደተገነዘብነው ፤ መንግሥት ከተ ሞችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ፣ ለኢትዮጵያ የሚመጥኑና ለዜጎች ምቹ እንዲሆኑ ለማድረግ የተቀናጀ የከተማ ልማት ፕሮግራም በመንደፍ ሰፋፊ ሥራዎችን በቁርጠኝነት እየሠራ ነው። የፌዴራል ተቋማት፣ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በከተሞች የሚካሄዱ ዘመናዊ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ እንዲሁም የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው የሕዝብ ንቅናቄ የመፍጠር ዓላማ ያደረጉ ሥራዎች መጀመራቸው በቆሻሻ አወጋገድና በጽዳት አጠባበቅ ላይ ያለውን ስር የሰደደ ደካማ ልማድ ለመቀየር ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል።

የምንመኛትን ውብና ጠንካራ ሀገር ለመፍጠር የፅዳት ባህላችንና የአካባቢ ጥበቃ ተሳትፏችን ማደግ አለበት። የዚህ ውጤት ቱሩፋቱ ብዙ ነው፡፡ ከቱሩፋቶቹ መካከል በተፈጥሮ፣ በታሪክ፣ በባህል እና በሌሎች ፀጋዎቻችን አማካኝነት ከቱሪዝም ዘርፍ የበለጠ ተጠቃሚ መሆን የሚያስችለው ይገኝበታል። ለመጪው ትውልድ ንፁህና ጠንካራ ሀገር ከማስረከበ ባሻገር ልክ እንደ ጃፓንና ሌሎች የዓለማችን ሀገራት ንፅህናንና አካባቢን የመጠበቅ ተግባር የማንነታችን መገለጫ ሆኖ እንዲታወቅ እድል ይፈጥራል።

በኢትዮጵያ በደካማ የቆሻሻ አወጋገድ እና ውበት አጠባበቅ የሚታወቁት ከተሞቻችን ብቻ አይደሉም። እስካሁን ትኩረት አላደረግንባቸውም እንጂ ፣ ችግሩ ወደ ውብ ተፈጥሮዎቻችን እና የቱሪዝም መዳረሻዎቻችን አካባቢ ተዛምቷል። ንቅናቄው እነዚህን አካባቢዎችንም እንዲታደግ ለማድረግ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ በተፈጥሮ ሀብቷ ታድላለች። በርካታ ፓርኮች እንዲሁም ጥብቅ ስፍራዎች በጉያዋ ይዛለች። በዚህ የተነሳ ቱሪስቶች የጉዞ እቅድ አውጥተው ወደ ተለያዩ መዳረሻዎቿ በመዝለቅ ይጎበኟታል። እነዚህ ጎብኚዎች መልካም ነው፤ ይሁንና ወደ ስፍራው ሲያቀኑ ከአካባቢ ጋር የማይስማሙ እንደ ፕላስቲክና የመሳሰሉት በካይ ቁሶችን ወደ ፓርኮቹ በሚወስዱ አካባቢዎች፣ በፓርኮቹና መስህብ ስፍራዎቹ ላይ ይጥላሉ። ይህ ችግር እየተስፋፋ መጥቷል።

ጎብኚዎች ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚና ገፅታ የሚኖራቸው ፋይዳ እንዳለ ሁሉ፣ ከላይ ያነሳናቸውን አይነቶች አሉታዊ ጎኖችንም ያሳድራሉ። በካይ ቁሶች በአልባሌ ቦታ ላይ ያለ ከልካይ መጣላቸው በቤትና የዱር እንስሳት፣ ሃይቆች፣ አእዋፋትና ብርቅዬ የሆኑ ሀብቶቻችን ላይ ጉዳት ያስከትላሉ። ይህ ድርጊት የውጪ ሀገር ጎብኚውን ብቻ የሚመለከት አይደለም፡፡ የሀገር ውስጥ ጎብኚንም ይመለከታል። በመሆኑም ከወዲሁ ጥብቅ ሕግ ማበጀት በመዳረሻ ስፍራዎች ላይ የቆሻሻ አወጋገድና የመፀዳጃ አጠቃቀም ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል።

ጽዱ ኢትዮጵያ ነገ የምንመኛትን ውብ ሀገር ለመገንባት የሚያስችል መሠረት ይጥላል። ከግለሰብ እስከ ተቋም ርብርብ ሲደረግ እና በአንድነት ለአንድ አላማ ሲሰራ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ለውጥ ማምጣት ይችላል። ይህን መሰል ንቅናቄ የአንድ ጊዜ ብቻ እንዳይሆን እንደ ባህል እንዲሰርፅና ትውልድ የማንነቱ መገለጫ አድርጎ እንዲወስደው ደጋግመን ደጋግመን ልንተገበረው ይገባል የሚለው የዛሬው መልእክቴ ይሁን። ሰላም!

አዲስ መንገድ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You