ከጉርምስና እስከ ጉልምስና

አዲስ የገዛሁት ጫማ አቧራ ቅሞ ሳየው መሀረቤን ከኪሴ መዥርጨ አበስ አደረኩት። ወደእሷና ወደእናቴ ስሄድ ተሽቀርቅሬ ነው። እናቴ ፊት ጎስቋላ እሷ ፊት መሀይምና የማይረባ መምሰል አልፈልግም። በቸምቸሞ ጥቁር ጸጉሬ መሀል ያገጠጡ ያለጊዜያቸው የበቀሉ ሽበቶች በማያውቁኝ ሰዎች ፊት አንቱታን ቸረውኛል። በልጅነቷ የምታውቀው ወዜ የለም። ጊዜ አቂሞብኝ ነው መሰል ያለእድሜዬ አገርጅፎኛል። አሁን ማን የልጅነት ፍቅረኛውን የሚጠብቅ ጎልማሳ ብሎ ያስበኛል?

ጉርምስና…

ልጅነቴ አልቆ እንዴት ከአፍላነት እንደወደኩ አላውቀውም። ከስሬ የማጠፋ ከጥላዬ የተካከለች አንዲት ሴት እንደአንገቴ ዶቃ አብራኝ ተሰልፋ እንደነበር ይሄን አስታውሳለው። ከአንዲት እኔን መሳይ ነፍስ በቀር ትዝ የሚለኝ አንዳች የለም። ከእናቴ ጉያ ስሸሽ ማረፊያዬ እሷና ቀሚሷ ናቸው። ባልና ሚስት ሳንሆን የተጫወትነው እቃቃ የለም። ማንም የሚያውቀን እኔ ለእሷ ባል እሷ ለእኔ ሚስት ሆነን ስንጫወት ነው። የሌላ ሴት ባል ሆኜ በተጫወትኩባቸው የእቃቃ ዘመኖቼ አልቅሳ ባሏ ያደረገችኝን ልጅነቴን ሳስታውስና የሌላ እኩያዬ ሚስት ሆና ተደባድቤ ሚስቴ ያደረኩበትን የልጅነት ዘመኔን ሳስብ የማያባራ ሳቅ ይከጅለኛል።

እኩል ነው የጎረመስነው። ልጅነታችንን እስከጨረስንበት እስከ ቅርብ ዓመት ድረስ በቁመት እኩል፣ በሃሳብ እኩል ነበርን። ምኞታችን ራሱ የተወራረሰ ነው። በአንድ አእምሮና ልብ ወንድና ሴት የሆንን እንጂ በሁለት አእምሮና ልብ የምናስብ አንመስልም ነበር። ሰው እንዴት በሃሳብ እኩያ ይሆናል? በምኞት መቀራረብ እንጂ መመሳሰል በማን ላይ ደርሶ ያውቃል? በእድሜ እና በቁመት ይሁን በሃሳብ እኩያ መሆን ለማን ተችሏል? እኔና እሷን ሳስብ ከመደነቂያዬ አንዱ ይሄ ነው። በማላውቀው እና ተመልሶ እንዲመጣ በማልመኘው የሆነ ጠዋት ላይ ከእንቅልፌ ስነቃ ሌላ ሆኜ  ነቃሁ። አድጌና ዘልጌ በእድሜ የሚበልጡኝን ሁለት ታላላቅ ወንድምና እህቶቼን በቁመት በልጬ፣ ከአባቴ አነስ ከተቀሩ ቤተሰቦቼ ከፍ ብዬ ራሴን በእንግድነት አገኘሁት። ያሳሰበኝ ማደጌ አልነበረም ከእንግዲህ እንደማታቅፈኝ ማመኔ ነበር። እኩያ እያለን ያለ ምንም መቸገር ነበር የማቅፋትና የምታቅፈኝ። እኔ ላይ ፊጥጥ እንደማለት የሚቀናት አንዳች የለም።

መጀመሪያ ስታየኝ የተሰማትን ስሜትና የሆነችውን መሆን መቼም አልዘነጋውም። አስታውሳለው ያን ቀን ረፋድ እንደ ሁልጊዜዋ አያቷ ጋ ልንሄድ (የአያቷ ሰፈር ከሰፈራችን በልጅ እርምጃ የ7 ደቂቃ ሰፈር ነው። ጠዋት ጠዋት እንደ ቤተክርስቲያን ገረገራ የአያቷን ቤት የመሳለም ግዴታ ጥላብኛለች። አያቷ ጋ ሳትሄድ እና እታባዬ ብላ ጉንጭዋን ሳታስም ቀን የላትም) በእኛና በነሱ ቤት መካከል ባለው የዛፍ ጥላ ስር ተቀምጣ፣ አንድ የእናቷን አንድ የእህቷን የተለያዩ ጫማዎች ተጫምታ የምንጫወትበትን እቃዎች ስታሰናዳ ነበር ድንገት ያየችኝ። እኔ አልመስል ብያት ለረጅም ሰዓት ስታስተውለኝ እና ከሆነ ሰው ጋር የተመሳሰልኩባት መስሏት ለማመን ስትቸገር አስታውሳለሁ። የምታውቀው እኔና የማታውቀው የሆነ ሰው ተቀይጠንባት ማነህ ምንድነህ ሳትለኝ ሕይወት ቀጠለ።

እጹብ የምትገርም የሕይወት ዛፍ ናት። ሞት ያለባት እጸበለስ ብትሆን እንኳን በድፍረት ቀንጥሻት የሞት ሞትን ልሞትባት ወደኋላ የማልላት ታሪኬ ናት። በሕይወቴ ደምቀው ከተሳሉት ዋናዋን ናት። ወደእኔ ስትመጣ በተንሻፈፈ ታሪክ ነው..በወጉ ለብሳ አንድም ቀን አይቻት አላውቅም። ልብስ ስትለብስ የሆነ ቦታ ላይ ትሳሳታለች። ብዙ ጊዜ እጅጌውን አንገቷ ውስጥ አስገብታ የተለየች ፍጥረት ሆና፣ የቀሚሷን ፊትና ኋላ አዙራ፣ በአንድ የጆሮ ጉትቻ አሊያም በማይመሳሰሉ ጌጦች ልጅነቷን የቋጨች ናት። በማይመሳሰሉ ጫማዎች፣ በተዘባረቁ የጆሮ ጌጦች ሴት የሆነች ናት። ምንም የማይመስላት..ምንም ቢመስላትም ከቅጽበት የማትርቅ ጀግኒት። ሁልጊዜ አንድ ዓይነት ናት..እሷን እና እሷን መሳይ።

ከዛን ቀን ጀምሮ እኔን ለማቀፍ የምታደርገው ትንቅንቅ  መዝናኛዬ ሆነ። ምነው ባላደኩ የሚለው የዘወትር ጸሎቴ ግን ከአፌ ላይ የሚያብሰው አልተገኘም። በእኔ ድንገተኛ መዝለግ ወዳጅነታችንን እየሸረሸረ ብዙ ጊዜ ራሴን ብቻዬን አገኘው ጀመር። ከዛ ማደግ በኋላ ጥቂት ዓመታት ተቆጠሩ። በሃሳብ ባንራራቅም በቁመት ሳትደርስብኝ ርቄያት ሄድኩ። በሁለት ወር እንደምትበልጠኝ ሰምቻለሁ..ግን ምናችንም እኩያ አይመስልም።

የሆነ ቀን ጠፋች

ቆይቼ ስሰማ አጎቷ ጋ ስዊድን መሄዷን ሰማሁ። በየት በኩል እንደሄደች ግራ ገባኝ። በ24 ሰዓት ውስጥ አብረን የማንሆነው ለመጸዳጃ ቤትና ለሻወር ቤት አንዳንድ ጊዜም ለመኝታ ነው። እኚህንም ብዙ ጊዜ አብረን አድርገናቸዋል። ለዚህ የሚያበቃ መራራቅ በመካከላችን መች ተፈጠረና ራቀችኝ! ሳላይና ሳልሰማ በምን ቀዳዳ እንደሾለከች ባስብ ራቀኝ። እዚህ ላይ ራሴን ብዙ ጠየኩ.. ዓመታት በቅጽበት ሲደበዝዝ፣ ዘመን በአሁን ሲዋጥ ጊዜን ‹‹እናትክን›› አልኩት። ናፍቆት በነበር ሲቀር፣ ትዝታ በመሄድ ሲሻር ዘመንን አቄምኩበት። ስንት ነገር አውግታኝ የለ ምናለ አንድ ጊዜ እፈልገሃለሁ ብላ እቃቃ የምንጫወትበት ጥላ ስር ቆማ ድንገት ስማኝ ቢሆን..ባልና ሚስት ስንጫወት አሳባ ፍቅሯን ብትነግረኝ ስል ብዙ አሰብኩ። ፍቅር እየሱስን የሚመስለው ተጀምሮ ሲያበቃ እንጂ ተጀምሮ ሲቆም አይደለም። ያላለቀ ፍቅር የገሀነም ዙሪያውን ነው።

እያሰብኳት ወደነገ በረርኩ። በጉርምስናዬ ላይ ብዙ ዓመታት ተጨምረው ወጣትነት አፋፍ ላይ ደረስኩ። እሷ የሌለችበት እኔ፣ ጥላዋ ያልደረሰበት ወጣትነት እጅግ ፈታኙ ጊዜዬ ነበር። ራሴው ለራሴ ከበደኝ። ከአዲሱ ማንነቴ ጋር ለመላመድ እጅግ ከብዶኝ ነበር። ከቤታችን ስወጣ እና ዓይኔን ወደቤታቸው ስሰድ በቁመት ከሚበልጣት ጆግ ውስጥ ውሀ እየጨለፈች ፊቷን ስታብስ የማውቀው ታሪክ እና ባልና ሚስት ሆነን የተጫወትንበት የጥላው ዛፍ ልቤ ውስጥ እሷን ማስታወሻ ሀውልት ሆነው በስሟ ቆመዋል። የልጅነታችን አድባሮች አሁን የሉም..ቤታቸው ፈርሶ አዲስ በተሠራ ሕንፃ ታሪኬ ድምጥማጡ ጠፍቷል። የጥላው ዛፍም ቦታው ላይ የለም። እንደነበር የሚቀጥል የለም ስል የምፈራው ይሄን እኮ ነው! እኔና እሷስ መች እንደነበርን ቀጠልን?

ቤተሰቦቿ ግቢያቸውን ለአንድ ድርጅት አከራይተው ከእኛ መንደር ፈቀቅ ብለዋል። ሕንፃው ሲሰራ ያን ዘወትር ማለዳ አብሯት የማየውን ቀይ ጆግ ስንት ታሪክ እንዳልጣፈ ቆሻሻ ገንዳ ላይ ሳየው ታሪኬን አውጥተው የጣሉት ነበር የመሰለኝ። ማታ ማንም ሳያየኝ ከቆሻሻ ገንዳው ላይ አንስቼ ከቤት ስወጣ ፊት ለፊት እንዳየው አድርጌ እንደ ሰንደቅ አላማ ከቤታችን ጣሪያ ላይ ከአንድ ከፍ አርጌ ሰቀልኩት። ከመጥፋት ግማሽ ትዝታዬንና ግማሽ ነፍሷን የታደኳቸው ይመስለኛል..

በአንድ ሰው የናፍቆት ሸለቆ ውስጥ ወድቆ ወደነገ ለመሄድ መቸገር ቅጣት ነው እላለሁ። በዚህም ሰው በመሆን ውስጥ መቅደም ያለበት ቀዳሚው ተማጽኖ ወደነገ ከማያሻግር እርባና ቢስ ሰውና ፍቅር ጠብቀኝ የሚል ይሆናል። በሰው ነፍስ ላይ የፈጣሪ ዱላ እንዲህ ያለው ቅጣት እንደሆነ ማንም አልነገረኝም። የማትመጣን አንዲት ነፍስ መጠበቅ፣ ለማይደርሱበት ለራቀ ታሪክ መንጠራራት ከዱብዳ ሌላ ምን ሊባል ይችላል?

ጊዜ ከትዝታዋ ሳያፋታኝ ጉልምስና እንባ ላይ አሳረፈኝ። ራሴ ሁለት ዓይነት ፀጉር ወለደ። አላገባሁም..ፍቅረኛ የምትሆን ጉብልም አልከጀልኩ። ያቺን የጠዋት ጀምበር እየሞኩ በሄደችበት መንገድ መመለሻዋን አስተውላለሁ። የሆነ ጠዋት ትዝታዬን ከሰወረብኝ ሕንጻ ላይ ዓይኔን ተክዬ ከእናቴ በኩል መምጣቷን ሰማሁ። አንዳንድ ቅጽበቶች አሉ ምንም እንዳንናገር የነፍሳችንን አፍ አድብነው በዝምታ የሚለጉሙ.. አንዳንድ ቀናቶች አሉ ከወሰዱብን አልቀው ሊሰጡን በትካዜያችን ሰሞን ከወደቅንበት የሚመጡ። እኔም ቅዝዝ አልኩ..መቼም ከማልደግመው ደስታዬ ጋር።

ላያት ልሄድ ነው..

አዲስ የገዛሁት ጫማ አቧራ ቅሞ ሳየው መሀረቤን ከኪሴ መዥርጨ አበስ አደረኩት። ወደእሷና ወደእናቴ ስሄድ ተሽቀርቅሬ ነው። እናቴ ፊት ጎስቋላ እሷ ፊት መሀይምና የማይረባ መምሰል አልፈልግም። ግን ለምንድነው የምሄደው?

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ግንቦት 2 /2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You