ሊያ − የሞዴሎች ቁና!!!

የዛሬው ገጻችን ስለ ኢትዮጵያዊቷ ዓለም አቀፍ ሡፐር ሞዴል፤ እአአ በጃንዌሪ 3፣ 1998 “ልእለ ኃያል” ለመሆን ስለ በቃችው፤ ተዋናይት፤ አክትረስ፤ እንዲሁም፣ በታዋቂነቷ እና በመልካም ተግባሯ የዓለም የጤና ድርጅት በእናቶች፣ አዲስ በሚወለዱ ሕፃናት እና የሕፃናት ጤና ጥበቃ የበጐ ፈቃድ አምባሳደር ስለሆነችው፤ የአልባሳት ዲዛይን አውጪነቷን፤ እንዲሁም፣ የመድረክ ንግሥትነቷን አስመልክተው ብዙ የተባለላት፤ በእውቅ ዓለም አቀፍ የፋሽን መጽሔቶች ላይ ለበርካታ ጊዜ የውጭ ሽፋን (ከቨር ስቶሪ) ላይ በዋናነት በመውጣት ስለምትታወቀው፤ በእ.አ.አ. 2007 አመት ከዓለማችን 11ኛ ከፍተኛ ተከፋይ ስለሆነችው (“ፎርብስ″ እንደዘገበው) ሊያ ከበደ ይሆናል።

እ.አ.አ. ጃንዌሪ 3፣ 1978 አዲስ አበባ የተወለደችውን ሊያ፤ ትምህርቷን በሊሴ ገብረማርያም ስለ ተከታተለችው ሊያ፤ በTime’s Style & Design እና የመሳሰሉት መጽሔቶች ላይ የሽፋን ቦታን በተደጋጋሚ ለመያዝ ስለ በቃችው ሊያ፤ እ.አ.አ. በ2003 ለ“Estée Lauder ኮስሞቲክስ” በ57 አመት ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊ ተወካይ በመሆን የ3 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ስለ ፈረመችው ሊያ፤ በፎቶ ትዕይንቶች ላይ ጎልተው ከሚታዩ ጥቂት የአፍሪካ ሞዴሎች አንዷ ስለሆነችው ሊያ፤ “ይህንን ስሜት የፈጠረብኝ አፍሪካ ውስጥ ተወልጄ ማደጌ ነው። በድህነት ተከበው እየኖሩ ስለድህነት አለማሰብ ፈፅሞ የማይቻል ነገር ነው። ልጅህን በምትወልድበት በዚያችው ደቂቃ ነው ለልጅህ የተሻለች ዓለም ትተህ ማለፍ እንዳለብህ ማሰብ የምትጀምረው” በሚለው ቋሚና ዘላቂ አባባሏ ዘወትር ስለ ምትነሳው ሱፐር ሞዴል ሊያ ከበደ የምንለውን ልንል ነው ዛሬ ወደዚህ አስታዋሽ ገጽ የመጣነው።

የግንቦት 10 ቀን 2010 የታይም መጽሔት እትም ላይ ዲዲዮር ድሮግባ፣ ስኮት ብራውን፣ ጀምስ ካሜሮን፣ ዛሃ ሀዳድ፣ ቤንስቴለር፣ አሽተን ኩቸር፣ ሣራ ፖሊን፣ ቢል ክሊንተን፣ ካትሪን ቢግሎው፣ ሳንድራ ቡሎክ፣ ሳይመን ኮዌል፣ ሀን ሀን፣ ኦፕራ ዌንፍሬይ፣ ባራክ ኦባማ እና ሌሎችም ተርታ በመሰለፍ በፎርብስ መጽሔት ላይ ከ100 ተፅእኖ ፈጣሪዎች አንዷ የሆነችው ሊያ፤ በአንድ ወቅት 2.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በማግኘት ከዓለማችን 15 ከፍተኛ ተከፋይ ሡፐር ሞዴሎች መካከል 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ሱፐር ሞዴል ሊያ፤ The Good Shepherd እና Lord of War የተባሉ የሆሊውድ ታላላቅ ፊልሞች ላይ በመለስተኛ ተዋናይነት ስለ ተሳተፈችው ሊያ ከበደ ጥቂት ለማለትና ዝናዋን ዳግም ለማንገስ በማሰብ ዛሬ ወደዚህ ውለታ ከፋይ ገጽ ብቅ ብለናል።

የፊልሙ መነሻ ድርሰት፣ ሶማሊያዊቷ ዋሪስ ዳሪ ከጻፈችው ግለታሪኳ የተወሰደ ሲሆን፣ መጽሐፉ በተለያዩ ሀገሮች ውስጥ በከፍተኛ ቁጥር በተሸጠው፤ በ2009 እ.አ.አ በተለቀቀውና በአፍሪካ ሴቶች ላይ የሚፈጸመው ግርዛት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት መሆኑን በቁጭት የሚያሳየው፤ በራሷ በዋሪስ ዳሪ በተዘጋጀውና የጀርመንና የአሜሪካ ዜግነት ባላት የፊልም ዳይሬክተር በተቀናበረው፤ ቀረፃው በጅቡቲ፣ በኒውዮርክ፣ በኮለኝና በሙኒክ ከተማዎች The Desert Flower (የበረሃዋ አበባ) በተሠኘው ፊልም ላይ የቀድሞዋን ሡፐር ሞዴል Waris Dirieን በመሆን በመሪ ተዋናይትነት በመሳተፍ ከፍተኛ ዕውቅናን ያገኘችው ሊያ በእርግጥም አድናቂዎቿን ብቻ ሳይሆን እማያውቋትን ሁሉ እጃቸውን አፋቸው ላይ ያስጫነች፤ ከልዩም ልዩ ነችና አድናቆት ሲያንሳት እንጂ ሊበዛበት አይችልም።

በ2008 የሀበሻ እጅ ጥበብ ያረፈባቸውን የሕፃናትና የሴቶችን ልብሶችን የሚያመርተውን “የሊያ ከበደ የልብስ አምራች ድርጅት″ (http://www.lemlem.com/ በሚል የዘረጋችውን ድረ-ገፅ ይጎብኙ) የከፈተችውን ሊያ፤ “ሰዎችን እንደመርዳት” የሚያስደስታት ነገር የሌላት ሊያ፤ የሀገሯን ባህል ለማስተዋወቅ ለአፍታ እንኳን የማትታክተው ሱፐር ሞዴል ሊያ፤ እ.አ.አ. በ2000 የhedge fund ማናጀር ከሆነው ባለቤቷ፣ ኬሲ ከበደ ጋር በትዳር የተሳሰረችውና ሁለት ልጆችን (ስሁል (ወንድ) እኔ ሴቷ ሬይ) ያፈራችው ሊያ አስቀድሞ የሞዴሎች ሁሉ ቁና መሆኗ የተመሰከረላት ናትና እዚህ ስናነሳት በኩራት ይሆናል።

ከጅምሩ፣ የሕይወት መስመሯን (ከአንድ የፐርሺያ ኤጀንሲ ጋር) ከአዲስ አበባ ወደ ፈረንሳይ፤ ከፈረንሳይ ወደ ኒውዮርክ ያደረገችው ሊያ፤በጣልያን፣ ጃፓን፣ አሜሪካ፣ ስፔን፣ ፈረንሣይ ሀገራት የተለያዩ ስመጥር የህትመት ውጤቶች ላይ የፊት ሽፋን ቦታን በተለያዩ ጊዜያት ያገኘችው ሱፐር ሞዴል ሊያ፤ የፋሽን ኢንዱስትሪውን ተቀላቅለው የጥቁሮችን ማንነት እና ባህል ለዓለም በመግለጽ በኩል ከተሳካላቸው ምርጥ የአፍሪካ ዲዛይነሮች መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያዊቷ ዓለም አቀፍ ሱፐር ሞዴል እና ዲዛይነር ሊያ ከበደ የሱፐሮች ሱፐር ነችና ለዛሬ ማንሳታችን ስለ ክብሯና ሀገሯን ስለ ማስጠራትና ማስከበሯ መሆኑን ስንገልጽ ደስታችን ወደር የለውም።

የጤና ባለሙያዎችን ማሠልጠን እና በገንዘብ መደገፍ ላይ ያተኮረው የሊያ ከበደ ፋውንዴሽን መስራች፤ በቅርቡም አዋላጅ ነርሶችን ከሚያሰለጥነው አመርፍ ኸልዝ አፍሪካ ከተባለው መንግሥታዊ ካልሆነ ድርጅት ጋር በአጋርነት እየሰራች የምትገኘው ሊያ ሲነሳ፤ በኒውዮርክ የምትኖረው ሊያ የእውቅ ኩባንያዎች ሞዴል ሆና ከመስራቷም ባሻገር በፓሪስ፣ ለንደንና ኒውዮርክ የሞዴል ሾው መድረኮች ላይ ስለተምነሸነሸችው ሊያ ሲነሳ፤ ከ2007 ዓ.ም ወዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ከፍታ፤ በተለይ ሴት የጥልፍ ባለሙያዎችንና ሸማኔዎችን እያገዘች ስለምትገኘው ሱፐር ሞዴሊስት ሊያ ሲነሳ ወዘተ ለዝነኝነትዋ መሰረቱ ሞዴሊስትነቷ ብቻ ሳይሆን ሰብአዊ ተግባሯም ነውና ሊያ ልዩ ነች ስንል ያለ ምክንያት አይደለም።

እ.አ.አ. በ2003 ለEstée Lauder ኮስሞቲክስ በ57 አመት ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊ ተወካይ በመሆን የ3 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት የፈረመችው፤ በ2000 የትዳር አለምን የተቀላቀለችው ሊያ ከአንጋፋው የፋሽን መጽሔት ‹‹ቮግ›› (በ2019) ጋር ቃለ-ምልልስ አድርጋ በነበረችበት ወቅት እስከ 18 አመቷ ድረስ በአዲስ አበባ እንዳደገችና ከዚያም ወደ ፓሪስ እንደ ሄደች በቃለምልልሷ ገልፃለች። ከዛስ?

ከአንድ አመት በኋላ በመጀመሪያ ቺካጎ፤ ቀጥላም ኒውዮርክ በመሄድ የሞዴሊንግነት ስራ ላይ መሰማራቷን ያስረዳችው ሊያ፣ በ2007 እ.ኤ.አ ወደ አዲስ አበባ ተመልሳ በመምጣት የተመለከተችውን ችግር ለመቅረፍ በማሰብ ‹‹ለምለም›› የተሰኘን ድርጅት በመክፈት ለበርካታ ሴቶችና የሽመና ባለሙያዎች የስራ እድል የፈጠረችው ሊያ ከበደ እውነትም ከባድ ሚዛን ነች ቢባል ቢያንስ እንጂ ከቶም ሊበዛ አይችልምና “ይበል!!!″ ልትባል የግድ ይሆናል።

‹‹ለምለም›› ከዓለም አቀፉ ‹‹ዘውል ማርክ ካምፓኒ›› ጋር በጋራ ለመስራት በመፈራረሙ ምክንያት በታዋቂው የአውስትራሊያው ብራንድ አማካኝነት ምርቶቹ በመሸጥ ላይ መሆናቸው ሲታወስ፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሴት የጥልፍ ባለሙያዎች የስራ እድል ማግኘታቸውና ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን መቻላቸው ሲሰማ፣ የሞዴሎች ሁሉ ቁና ከመሆኗም በዘለለ ስለ ታዋቂ ኢትዮጵያዊቷ ሡፐር ሞዴል ሊያ ከበደ በጎ አድራጊነት ሳይመሰክሩ ማለፍ አይቻልም።

“ለምለም” ድርጅት ከአለም አቀፉ ‹‹ዘውል ማርክ ካምፓኒ›› ጋር በጋራ ለመስራት በመፈራረሙ ምክንያት አሁን የለምለም ምርቶች በዚህ ታዋቂው የአውስትራሊያው ብራንድ አማካኝነት በመሸጥ ላይ መገኘታቸው መነሻና ምክንያቱ ሊያ እንጂ ሌላ ማንም አለመሆኑ ሲታወቅ፣ ታዋቂ ኢትዮጵያዊ ሡፐር ሞዴል፣ ተዋናይት፣ የልብስ ዲዛይነር፤ እንዲሁም፣ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ የአለም የጤና ድርጅት በእናቶች፣ አዲስ በሚወለዱ ሕፃናት እና የሕፃናት ጤና ጥበቃ አምባሳደር ሊያ ከበደ እውነትም የጀግኖች ሁሉ መስፈሪያ ናትና አድናቂዎቿ ስለ አርአያነቷ ወደር የለሽነት ደጋግመው ቢያወሩ ማንንም ሊገርም አይገባም።

ከሰብአዊ ተግባሮቿ ለጊዜው ዞር እንበልና ወደ ጥበብ ስራዎቿ እንመለስ።

የእናቶችን ሞት ለመቀነስ፣ የጤና ባለሙያዎችን ማሠልጠን እና በገንዘብ መደገፍ ላይ የሚያተኩረውን “ሊያ ከበደ ፋውንዴሽን” በመመስረት ትኩረት ሰጥታ በመስራት ላይ ስላለችው፣ ስለ ሊያ ከበደ ከተመሰከሩላት በርካታ ምስክርነቶች ውስጥ የተለያዩ ጥበባዊ ተሳትፎና ስኬቷን በተመለከተ የሰፈሩ ሃሳቦችን እናገኛለን። ከእነዚህም መካከል ሊያ በተለያዩ ኪነጥበባዊ ስራዎች ውስጥ የተሳተፈች ሲሆን፤ እንደ The Good Shepherd እና Lord of War የተባሉ የሆሊውድ ታላላቅ ፊልሞች ላይ እንደ አነስተኛ ተዋናይነት፤ እ.አ.አ. በ2009 የተለቀቀው Desert Flower የተሠኘው ውስጥ በመሪ ተዋናይትነት የቀድሞዋን ሡፐር ሞዴል Waris Dirieን በመሆን የተሳተፈችበት ፊልም ከፍተኛ ዕውቅና እንድታገኝ ያስቻላት መሆኑ ነው።

ከላይ በጨረፍታ የጠቀስንላት፣ በደራሲዋ፣ በራስዋ በዋሪስ ዳሪ ተዘጋጅቶ በአፍሪካ ሴቶች ላይ የሚፈጸመው ግርዛት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት መሆኑን የሚያሳያው ፊልም ላይ መስራቷም ከዚሁ ከኪነጥበብ ተሳትፎዋ ጋር አብሮ የሚጠቀስ ነው።

በፓሪስ፣ ኒውዮርክ እና ለንደን የፋሽን መድረኮች ላይ ስራዎቿን የማቅረብ ልምድ ያላት ዓለም አቀፍ ሞዴል ሊያ ከበደ በግሏ የምታስተዳድረው ሳይት (http://liyakebede.com/) ያላት ሲሆን፤ ድረ-ገፁ የራሷን ማስታወቂያ እና የዕርዳታ ጥሪዎችን ለማስተላለፊያነት የምትጠቀምበት መሆኑንም ለጠየቃት ሁሉ ትናገራለች።

የአፍሪካ፣ የጥቁር ባህል እና ማንነት መናኸሪያ መሆኗ፤ የፋሽን ኢንዱስትሪውን ተቀላቅለው የጥቁሮችን ብዝሀነት እና ባህል ለዓለም በመግለጽ በፋሽኑ ዓለም ከተሳካላቸው ምርጥ 14 የአፍሪካ ዲዛይነሮች መካከል አንዷ መሆኗ፤ የአፍሪካ ሀገራትን የባህል አልባሳት በዋናነት በማስተዋወቅ ዓለም አቀፉ የፋሽን ገበያውን ሰብሮ እንዲገባ ስለማድረጓ በአድናቆትና አግራሞት የሚነገርላት ሊያ ከበደ በአፍሪካዊነቷ ድርድር የማታውቅ መሆኗም ሳይነሳ የማይታለፍ ማንነቷ ነው።

ትልቁ ወደ ሆነው የሕይወቷ ምዕራፍ የተሸጋገረችው ቶም ፎርድ የተባለ ግለሰብ Gucci ለተባለ የክረምት ፋሽን ትርኢት እ.አ.አ 2000 ላይ እንድትካፈል ከጠየቃትና ከተካፈለች በኋላ ሲሆን፤ እውቅናዋ እጅጉን የጨመረው በእ.አ.አ 2002 Paris Vogue መጽሔት እትም የውጭ ሽፋን ከሰጣት እና ሙሉ ይዘቱን ማለት በሚቻል ደረጃ ስለ እሷ ካደረገ በኋላ መሆኑ ስለ ሊያ ሲነገር ሳይጠቀስ የማይታለፍ ነው። (በመጽሔቱ የጣሊያን፣ ጃፓን፣ አሜሪካ፣ ስፔን፣ ፈረንሳይ እትሞች ላይ መውጣቷም ከሌሎች መሰል የሙያ ባልደረቦቿ በተለይ ይጠቀስላታል።)

በሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት ገጠመኛቸው ምክንያት አንድ የፊልም ዳይሬክተር አይቷት፤ አይቶም ተረድቷት፤ ተረድቷትም (የዛሬ ማንነቷን አስቀድሞ ተንብዮ) በፈረንሣይ ከፐርሺያው የሞዴል ኤጀንሲ ጋር ያገናኛት ስለ መሆኑ ስለ እሷ፣ ሱፐር ሞዴል፣ ፋሽን ዲዛይነር እና ተዋናይት ሊያ ከበደ በተነገረ ቁጥር በቀዳሚነት የሚጠቀስ በር ከፋች ገጠመኟ ነው።

በnetworthpost.org ላይ ይፋ እንደተደረገው፣ ዓለም አቀፍ ሱፐር ሞዴል ሊያ ከበደ በያዝነው 2024 የተጣራ ሀብት $18 ሚሊዮን (ዜናው “Liya Kebede Net Worth $18 Million″ ሲል ነው የዘገበው) ያላትና የተሰማራችበትን የሙያ ዘርፍ በቁንጮነት እየመራች ያለች፤ እንቁ ኢትዮጵያዊት ዓለም አቀፍ ሞዴል ነች።

በ2013 የGlamour Award for The Role Models አሸናፊ፤ እንዲሁም ግንቦት 10 ቀን 2010 ታይም መጽሔት “ተፅዕኖ ማሳደር ከሚችሉ 100 የዓለማችን ምርጥ ሰዎች (The 100 most INFLUENTIAL PEOPLE IN THE WORLD) ብሎ ካወጣቸው ታዋቂ ሰዎች መካከል አንዷ ለሆነችው፣ እውቁ ዎልማርክ ኩባንያ አዘጋጅቶት በነበረው ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ ዳኛ በመሆን ለዳኛቸው፤ ተነግሮ የማያልቅ ታሪክ ስላላት ሊያ ከበደ የበለጠ ስኬትን በመመኘት ለዛሬ በዚሁ አበቃን።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You