መልካም የትንሳዔ በዓል!

እንደ ክርስትና ሃይማኖት አስተምህሮ የትንሳዔ በዓል ስለሰው ልጆች ሃጤያት በቀራኒዮ መስቀል ላይ ሕይወቱን የሰጠው መድሃኒት፣ ጌታ እና አምላክ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ በትንሳዔ የድል መንፈስ የተነሳበትን ቀን ለማስታወስ የሚከበር አጅግ ታላቅ በዓል ነው። ትንሳዔ የድል እና የመነሳት በዓል ነው ።

ዕለቱ ከዚህም ባለፈ በሰው እና በፈጣሪ መካከል በሰዎች አለመታዘዝ ምክንያት የተፈጠረው መለያየት ፤ በእርቅ የተቋጨበት ፤ የሰው ልጅ የቀደመ ጥፋቱም በክርስቶስ በሆነ ቤዛነት የተሻረበት፤ በአዲስ ሕይወት ፣ በትንሳዔው መንፈስ የዘላለም ሕይወት የተጎናጸፈበትና ሰማያዊ ዕድል ያገኘበት ፣ የአዲስ ታሪክ ትርክት ጅማሬ ነው።

ቀኑ እንዲመጣ ክርስቶስ በጭለማ ሃሳብ ተፈትኗል ፣ በብዙ ተወግዟል ፣ በብዙ ተብጠልጥሏል፤ ተሰድቧል ፤ ተተፍቶበታል ፣ በብዙ ተክዷል፤ ተገርፏል፤ ተሰቅሏል፡፡ ብዙ ብዙ መከራን ተቀብሏል፡፡ ይሁንና ስለፍጻሜው የተስፋ ብስራት ሲል ሁሉን ተቀብሏል። ራሱን ዝቅ ዝቅ አድርጎ የመስቀልን ሞት ተቀብሏል። በዚህም በጨለማ ለሚኖሩ አዲስ የብርሃን ወገጋገን ሆኗል።

ትንሳኤ ብርሃን ነው፡፡ ከብዙ ጨለማና ጭለማ ከወለደው ድንግዝግዝ በኋላ የመጣ ንጋትም ነው። ብዙ ውጣ ውረዶች በርትተው ተስፋ መቁረጥ በበዛበት የተገኘ የተስፋ ብስራት አዋጅም ነው። ከዚህም ባለፈ ትንሳዔ ተስፋቢስነትን ፍጹም ወደሆነ ተስፋ የለወጠ ነው ፡፡

ከመከራ በኋላ ትንሳዔ ሁልጊዜም አለ፡፡ ከጨለማ በኋላ የሚነጋ ቀን አለ፡፡ ትንሳኤ ከሀገራችን አሁናዊ እውነታ ጋር የሚነጻጸር ነው፡፡ ሀገራችን በብዙ ፈተናዎች፣ በብዙ ውጣውረድ ውስጥ እያለፈች ነው፡፡ እነዚህ ውጣ ውረዶች የትንሳዔያችን አብሳሪዎች ናቸው ።

አሁናዊ ሀገራዊ እውነታችን ፣ ከትንሳዔ በፊት ካለው ጊዜ ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡ እያለፍንበት ያለውም ጊዜ ወደትንሳዔያችን እየተቃረብን እንደሆነ የሚያመላክት ነው፡፡ እንደሀገር ስለተስፋችን እየከፈልን ያለው ዋጋ የነገ ትንሳዔ አብሳሪ ጉልበታችን ነው ፡፡

ጌታ ኢየሱስን ለመያዝ፣ ለማሰቃየት፣ ለመግረፍ፣ ለመስቀል የተሴረው ሴራ ከሀገራችን አዋኪ ትርክቶች ጋር ይመሳሰላል፡፡

ይሁዳ እየሱስን እንደሚወደው የውሸት ሲስመው፣ በኋላም በሰላሳ ዲናር አሳልፎ ሲሸጠው፣ ይሄን ከሀገር በልተው ወጪት ሰባሪ የሆኑ ግለሰቦችን ያስታውሰናል ፡፡ በአንድ ሌሊት የጴጥሮስ ክህደት፣ የነይሁዳ ወጥቶ መቅረት ያመኑ መስለው ሀገር የከዱን ያመላክተናል፡፡

ከመስቀሉ ስር ያልተለዩት እንደነ ዮሃንስ አይነቶቹ ደግሞ ለሀገር ታምነው፣ በእውነትና በጽናት የቆሙትን ሰብዐ ፍጡሮችን ያስታውሱናል፡፡ ከዚህ ሁሉ የማይነጋ ከሚመስል አስጨናቂ ለሊት በኋላ እንደሀገር ጭለማችን እየነጋ ነው፡፡ የማያልፍ ከመሰለ ወጀብ እየወጣን መሻታችንን ለመጨበጥ እየተንጠራራን ነው።

ትንሳዔ ከዚህም ባለፈ ከጨለማ ወደብርሃን፣ ከዝቅታ ወደከፍታ፣ ከሽንፈት ወደ ድል የሚወስድ መንገድም ነው፡፡ በሀገራችን እና በሕዝባችን ላይ እየሆነ ያለው ሰላም ማጣት፣ ስደትና መከራ ከትንሳዔ በፊት እንዳሉ የክርስቶስ ዘመኖች ናቸው፡፡ ለማያልፍ የተስፋ ቀን ለመታጨት በወጀቡ መሀል መሄድ ግድ ነው ፡፡

“ዘ ወረደ“ ብለን ሆሳዕና ላይ ስንደርስ ፣ መነሻችን ውጣ ውረድ ቢሆንም፣ መድረሻችን ግን ትንሳዔ ነው፡፡ መከራዎቻችን ለምንጠብቀው ትንሳዔያችን /መነሳታችን ጉልበት ሆነው ድል ሊያቀናጁን ከበር አድርሰውናል፣ የመጨረሻ መስመር ላይ አቁመውናል።

የትንሳዔያችን ጀምበር ምስራቅ አድማስ ላይ እየወጣች ነው፡፡ ትንሳዔያችንን የማዋለድ ምጥ ሲያበቃ ያን ጊዜ የኢትዮጵያ አበሳዎች እንደጉም ይተናሉ፡፡ ትንሳዔዋም ከቃልነት አልፎ የሚጨበጥ እውነት ይሆናል። መልካም የትንሳዔ በዓል!

አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You