የማስታወቂያዎች ጉዳይ …

በቅርቡ አንደ ወዳጃችን ‹‹በመንገዴ ታዘብኩት›› ያለውን አንድ እውነት እየተደነቀ አጋራን። የሰማነው ጉዳይ ፈገግ ባያስብልም ሀሳቡን ያደመጥነው በጨዋታ አዋዝተን ነበር። እሱ እንደነገረን በእግሩ እየተጓዘ ሳለ ከአንድ ሕንጻ አናት ላይ የተሰቀለው አንድ ምስል ትኩረቱን ይስበዋል። ጠጋ ብሎ ሲያስተውለው በላዩ ‹‹የቁንጅና ማሰልጠኛ›› የሚል ጽሁፍ ተለጥፎበታል። እይታው በዚህ ብቻ አልተቋጨም።

በጉልህ የምትታየው አንዲት ጥቁር ሴት ከፊል አካሏ ልብስ አልባ ሆኖ እርቃኗን ተጋልጣለች። ይህቺ ሴት በተራቆተ ሰውነቷ ምን ማስተላለፍ እንደተፈለገ ባይታወቅም የማስታወቂያው መለጠፍ ግን ቁንጅናና ውበትን ለሚሹ ሁሉ ስልጠና ለመስጠት መሆኑን ያመላክታል።

እኛም ይህን የአደባባይ ላይ ማስታወቂያ መነሻ አድርገን እየተስተዋለ ያለውን እውነታ በመጠኑ ዳሰስነው። እውነትም ጉዳዩ አሳሳቢ በሚባል መልኩ መረን መልቀቅ ጀምሯል። የዘመናችን ማስታወቂያዎች ያለ ሴቶች ድምቀት አይሰሩ ይመስል በእያንዳንዱ ጉዳይ እነሱን ስንቅር ማድረጉ ተለምዷል። እርግጥ ነው ሴት ልጅ ድንቅ ውበት ይገለጽባታል። እንዲህ ሲባል ግን የክቡር አካሏ ጥቅመኞች እንዳሻቸው ይዘዙባት ማለት አይደለም። አሁን ላይ በስፋት የሚስተዋለው ግን ይህን ሀሳብ የሚቃረን ሆኗል። ሴት የኮስሞቲክስ ማሳያ፣ ሴት የሳሙናና የልብስ አጠባ መገለጫ፣ ሴት የአጉል ዳንሶች መማረኪያ መሆኗ ብርቅ እየሆነ አይደለም።

ይህ ብቻም አይደለም። በእኛ አገር የማስታወቂያ ተሞክሮ ሴት ልጅ ከፍታዋ ሳይሆን ዝቅታዋ ብቻ የሚመሰከርባቸው መገለጫዎች ሞልተውናል። እንዲያም ሆኖ ከሚመለከታቸው አካላት የአሰራር መመሪያና ጠበቅ ያለ እርምጃ ሲተገበር አይስተዋልም። ከዓመታት በፊት ይስተዋሉ የነበሩ ክፍተቶች አለመደፈናቸው ደግሞ ሌሎች በተቀደደላቸው ቦይ ኮለል ብለው እንዲፈሱ ምክንያት ሆኗል።

የማስታወቂያ ነገርን ስናነሳ በርካታ ጉዳዮችን መምዘዝ ይቻላል። አሁን ላይ ብዙዎች ራሳቸውን የሚገልጹበት፣ የስራ መስካቸውን የሚያሳዩበት አቋራጭ መንገድ የማስታወቂያው ዘርፍ ነው ለማለት ያስደፍራል። እንዲህ መደረጉ ክፋት የለውም። ማንነትን በቅጡ ለማሳየት የስራ ውደድርን በተግባር ለማውጣት ያግዛል። ምንም እንኳን በተለምዶ ‹‹ጥሩ ዕቃ ማስታወቂያ አያሻውም›› ቢባልም ይህን ዘርፍ በአግባቡ ለተጠቀመበት ግን አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም።

አንዳንዴ ደግሞ ሰዎች አውቀውም ይሁን ሳያውቁ በማስታወቂያቸው ያልተገቡ ጉዳዮችን ሲነካኩ ይስተዋላል። ለዚህ እውነታ አንድ ጉዳይን ልጥቀስ። ኢትዮጵያ የግብረሰዶማውያንን ዓላማና ድርጊት ከሚቃወሙትና ፍጹም ከማይደግፉት ሀገራት መሀል ግንባር ቀደሟ ናት።

በአንድም ይሁን በሌላ እነዚህ አካላት በዚህች ምድር ግብራቸውን ለማስፋፋት ያደረጉት ሙከራ አልተሳካላቸውም። እንዲህ ሲባል ግን በህጋዊ መንገድ አልጸደቀላቸውም እንጂ ጭራሽ የሉም፣ አልተስፋፉም ማለት አይደለም። እንደሚታወቀው ግብረሰዶማውያኑ ራሳቸውን የሚገልጹበት ዓርማና መለያ አላቸው። ይሁንታውን ባገኙባቸው ሀገራትም በመለያቸው ማንነታቸውን እያስተዋወቁ ዓላማቸውን ያስፋፋሉ።

የእነዚህ አካላት መለያ በህብረ ቀለማት የደመቀ ቀስተደመናማ መሳይ ነው። እዚህ ላይ የሚያውቁት ያውቁታልና ዝርዝር ሁኔታውን ማስፈር ተገቢ አይሆንም። አሁን ግን በአንዳንድ ማስታወቂያዎች በግልጽ እንደሚስተዋለው ይኸው ዓርማ የተለያዩ ቁሶች መለያና ማስታወቂያ ጭምር እየሆነ ነው። ይህ ማለት ደግሞ በሌላ አቋራጭ ዓርማና መለያው እየተዋወቀና ዓላማውን እያስፋፋ ነው ለማለት ያስደፍራል።

ይህን እውነት የሚያውቁ አንዳንዶች በማስታወቂያዎቹ መመሳሰል ጥርጣሬ ሊያድርባቸው ይችላል። ምናአልባትም ከዚህ አልፈው እያዩት ያለው ገጽታ በትክክል ምርታቸውን እያስተዋወቀ ነው ብለው አያምኑም ይሆናል። እንዲህ ቢያስቡ ደግሞ አይፈረድም። ተጽዕኖ ፈጣሪውን ጉዳይ ዓይናቸው ቀድሞ አይቷልና ዓይምሯቸው የሚቀበለውን ለይቶ ይመርጣል።

እዚህ ላይ ስለ ማስታወቂያዎቹ ተመሳስሎ ጥያቄ ቢነሳ ‹‹ሳላውቅ ነው›› ይሉት ምላሽ ይሰራ አይመስለኝም። ምንአልባት በጉዳዩ ላይ አጥብቆ ጠያቂ ቢኖር የኃላፊነቱን ጉዳይ ንግድ ፈቃዱን ለሰጠው አካል ያሳልፈው ይሆናል። ይህ ክፍል ቢጠየቅ ደግሞ አስቀድሞ በተመሳሳይ ዓርማና መለያ ለሌላ አካል የሰጠው ይሁንታ እንደሌለ መናገሩ ግልጽ ነው። እንዴት ከተባለም ባለደማቅ አርማዎቹን እነ ‹‹እንቶኔ›› በህጋዊ ፈቃድ የሚንቀሳቀሱ አለመሆናቸውን ማሳወቁ አይቀሬ ይሆናል።

እንደ እኔ ዕምነት ግን ከዚህ ሁሉ ችግር ሰዎች በማስታወቂያቸው ከመንቀሳቀሳቸው በፊት አስቀድመው ሊያስቡበት ይገባል። ውሎ አድሮ በውጤቱ ላይ ስብራት ለሚያስከትልባቸው እንከንም ቅድመ -ጥናት ቢያድርጉ ኪሳራ አይገጥማቸውም።

በቅርቡ አንድ የሜካፕ ማስታወቂያ በተለያዩ ሚዲያዎች ሲንሸራሸር ተስተዋለ። ይህ ሜካፕ በአንዲት ሴት ከዋኝነት የተመራ ሲሆን ዋንኛ ግቡ ለሙሽሮች መዋቢያነት ተብሎ የተዘጋጀ ነበር። ከመልዕክቱ ለማወቅ እንደተቻለው ሙሽሪት በዕለተ ሰርጓ በቬሎ አምራ ስትወጣ ለመድመቂያዋ ዋንኛ ምክንያት በዚህ የፊት ክሬም መፍካትና መቅላት መሆኑን ለማሳየት ነው።

ይህን መልዕክት በታሰበው ልክ ተደራሽ ለማድረግ የበዛ ጥረት ስታደርግ የታየችው ሴት ውሎ አድሮ በግሏ ተቃውሞን ማስተናገዷ አልቀረም። ስለፊት ሜካፑ በጥልቀት እናውቃለን ያሉ በርካቶች ስለጉዳቱ በመረጃ ሲያብራሩ አልዘገዩም። እነሱን ተከትሎ ስለዚህ የመዋቢያ ሜካፕ አደገኛነት በወጉ ማስረዳት የያዙት የቆዳ ሀኪሞችም የጉዳዩን አሳሳቢነት ገሀድ ለማድረግ አስተማማኝ እማኞች ሆነዋል።

ይህ ሁሉ የግንዛቤ መነቃነቅ የተፈጠረው ማስታወቂያ ሲሰራ የራስን ጥቅም ብቻ በማስቀደም ስለሌሎች ማሰብ ያልተለመደ በመሆኑ ነው። ማስታወቂያውን ይዛ የወጣችው ሴትም ብትሆን የምታስተላልፈው ጉዳይ ምን ጥቅምና ጉዳት አለው የሚለውን እውነት ያሰበችበት አይመስልም።

ሁኔታው የሚፈቅደው ለሰርግና ለሙሽሪት ስለሆነ ብቻ ቬሎዋን ለብሳ በእርግጠኝነት ‹‹ሞክሪው›› ብላ ስታውጅ ራሷ አድርጋውና አረጋግጣው እንደሆነ ማሳያዎች የሉም። ይህን ያስተዋሉ በርካቶች በሚተላለፈው መልዕክት እርግጠኝነት ተማምነው ምርቱን ለመጠቀም ዓይናቸውን እንደማያሹ መገመቱ ቀላል ነው።

በርካቶቻችን እንደምንረዳው ማስታወቂያ የራሱ የሚባል ኃይል አለው። በብዙዎች ዘንድ በዚህ ዘርፍ የተነገረና የታየ ሁሉ ትክክለኛና እውነተኛ ነው ተብሎ ይታመናል። በተለይ ጉዳዩን ታዋቂ ሰዎች የሚያስተዋውቁት ከሆነ የአመኔታው ጥግ ወደር የለውም። ይህ አይነቱ ሀቅ ባለበት ሜካፕን የመሰሉ ምርቶች በብዙሀን ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ቀላል የሚባል አይሆንም።

ሜካፑን ከመጠቀም በኋላ ለሚደርሱ የቆዳና መሰል ችግሮች ማስታወቂያ አስነጋሪዎቹ ቢጠየቁ ደግሞ አንዳች ማስተባበያ አይኖራቸውም። ኃላፊነቱን ለመውሰድም የሚተባበሩ አይሆንም።

ብዙዎች እንደሚሉት በተለይ ሜካፕና መሰል መገልገያዎችን አስመልክቶ ወደ አፍሪካ የሚላከው ምርት እንደ መሞከሪያ የሚቆጠር ሸቀጥ ነው። ልክ ከሀገረ- ቻይና ለአውሮፓና ለአፍሪካ ተብለው እንደሚለዩት ይዘቶች ሁሉ የሜካፑም ጉዳይ በዚህ ደረጃ የሚታወቅ መሆኑ ይነገራል። ስለዚህ እውነት የሚያውቁም ይሁኑ ‹‹አናወቅም›› ባዮቹ ሸቀጦቹን እንደወረደ ተቀብለው ኪስን በሚያሞቅ ትርፍ ‹‹እነሆ›› ማለታቸው ተለምዷል።

ይህን የሽያጭ መድረክ በማስፋትና በማዳመቅ ታዲያ ትልቁን ድርሻ የሚወጡት የማስታወቂያ አካላት ናቸው። አብዛኞቹ ጉዳዩን ከስሩ፣ ሳያጣሩ ሳይመረምሩ ለትርፋቸቸው ብቻ መሯሯጥን ያውቁበታል።

የአንዳንድ ዕቃዎች ጥራትና የታዋቂነት ጣራም እንዲሁ ነው። በማስታወቂያ ጩኸትና ተጽዕኖ ተጠቃሚው እጅ ከገቡ በኋላ ውጤቱ እንደታሰበው ላይሆን ይችላል። ብዙ ግዜ እንዲህ አይነቱ አጋጣሚ ሲኖር አምራችና አከፋፋዮች፣ በዳግም ማስታወቂያ ችግሩን ለማሳወቅ ይሞክራሉ። የእኛም ጆሮ ቢሆን ‹‹በተመሳሳይ ምርት እንዳትታለሉ፣ የምርታችንን መለያና ዓርማ እወቁ›› ወዘተ.. ይሉ አባባሎችን ለምደናል።

ማስታወቂያን በአግባቡ አውቀንና ተረድተን ከተጠቀምንበት ቱርፋቱ ለብዙሀን ይተረፋል። ዓላማችን ገንዘብና የተለየ ትርፍ ብቻ ከሆነ ግን እየከበርን ሳይሆን በእኩል እየከሰርን መሆኑን ልናውቀው ይገባል። ከምናገኘው ዕውቅና ይበልጥ ብዙሀንን ጎድተን የምናልፍበት መንገድ ደግሞ ምቹ ሊሆን አይችልም።

እንደ ግል ጥቅማችን ሁሉ ከብዙሀን አመኔታን ማግኘት ታላቅ መከበር ነው። ይህ እውነታም እንደ በዛ ትርፍ ይቆጠራል። እንዲህ መሆኑ ጥቂት አትርፈን በብዙ መክበርን ይመሰክራልና የሁልግዜውን ተግባራችንን መልካም ያደርገዋል።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ሚያዚያ 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You