“በኮሪደር ልማቱ የተነሱ የቤተክርስቲያን ሀብቶችን መልሶ የማልማቱ ሥራ በትብብር እየተሠራ ነው” – ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ

አዲስ አበባ፡- በከተማዋ በኮሪደር ልማት የተነሱ የቤተክርስቲያን ሀብቶች መልሶ የማልማት ሥራ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በትብብር እየተሰራ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን  ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በኮሪደር ልማት ምክንያት የተነሳውን ጽርሃ ሚኒሊክ (በተለምዶ መሀሙድ ሙዚቃ ቤት) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሕንጻ የመልሶ ግንባታ ሥራ አስጀምረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ የግንባታ ሥራውን ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለጹት፤ በኮሪደር ልማቱ የተነሱ የቤተክርስቲያን ሀብቶችን መልሶ የማልማቱ ሥራ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በትብብር እየተሰራ ነው፡፡ ሰላምና ልማት ለአንድ ሀገር ወሳኝ ነው ያሉት ብጹዕነታቸው፤በከተማው በኮሪደር ልማት የሚሰሩ የልማት ሥራዎች አስደሳች ቢሆንም ጥንቃቄ ማድረግ የሚገባቸው ቦታ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ብጹዕ አቡነ ማቲያስ አክለውም ዜጎች መውደቂያ እንዳያጡ ታሳቢ ተደርጎ የሚሰራ ልማት የሚደገፍ ነው ያሉ ሲሆን፤ በልማቱ የተነሱ ቦታዎች ለምተው እንዲመለሱም ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ለሀገር የምትጸልይ በመሆኗ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ያሉት ፓትርያርኩ፤በመልሶ ማልማቱ የሚሰራው ሁለገብ ሕንጻ በጥራትና በተያዘለት ጊዜ ተሰርቶ ለቤተ-ክርስቲያን ማስረከብ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

እንደ ቅዱስ ፓትርያርኩ ገለጻ፤ ሕንጻው ሲፈርስ ጥናት ተደርጎ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመነጋገር የሚበጀውን የጋራ ውሳኔ ተወስኖ ነው፡፡ ከዚህ ወጪ በሌሎች ቦታዎች በኮሪደር ልማቱ የተነሱ የቤተ-ክርስቲያኑ ሀብቶች ለምተው ተመላሽ መደረግ አለባቸው ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፤ የቀድሞ ሕንጻው ሲፈርስ ከቤተክርስቲያኒቱ አስተዳደርና ከብጹሃን አባቶች ጋር ንግግር ተደርጎ ነው ያሉ ሲሆን፤ በመልሶ ማልማት ግንባታው የኮሪደር ልማቱ በሚፈቅደውና ለአካባቢው ተጨማሪ ድምቀት በሚሆን መልኩ ይገነባል ብለዋል፡፡

ወይዘሮ አዳነች አክለውም፤ በአካባቢው ንብረትነቱ የቤተክርስቲያን ሃብት የነበረው ግራውንድ ፕላስ አራት ሕንጻ ማንሳት ያስፈለገበት ምክንያት ከሌሎች የልማት ሥራዎች ጋር ለማሳለጥና በተሻለ ሁኔታ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ነው፡፡ በመልሶ ግንባታው ግራውንድና አንድ ቤዝመንት እንዲሁም ባለ 4 ወለል ህንጻ ሙሉ በሙሉ በከተማ አስተዳደሩ ወጪ ይገነባል ያሉ ሲሆን፤ ግንባታውም በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ወራት እንደሚጠናቀቅ አስረድተዋል፡፡

እንደ ወይዘሮ አዳነች ገለጻ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የከተማ ፕላንና ልማት እንዲጠበቅ እንዲሁም ከተማዋ እንድትለማ ዲዛይኑ እንዲተገበር በርካታ ትብብር አድርጋለች፡፡

የከተማዋን ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ በአምስት ኮሪደሮች ልማት እየተከናወነ ነው ያሉት ከንቲባዋ፤በተለይ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ከተገነባ ወዲህ ሌሎችም ቅርሶችና ልማቶች ተናባቢ እንዲሆኑ እንዲሁም አንድ ላይ እንዲጎበኙ ለማድረግ እንዲቻል እየታደሱ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You