‹በማንዴላ ካፕ›› ውጤት ያስመዘገበው የቦክስ ቡድን አቀባበል ተደረገለት

በደቡብ አፍሪካ ደርባን ከተማ በተካሄደው የማንዴላ ካፕ የቦክስ ውድድር ውጤታማ ተሳትፎ በማድረግ ኢትዮጵያን በኩራት ያስጠራው የቦክስ ብሄራዊ ቡድን አቀባበል ተደረገለት። በደቡብ አፍሪካው የነጻነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ መታሰቢያ በሆነው በዚህ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን የወከለው ቡድን 3 የብር እና 3 የነሃስ በጥቅሉ 6 ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው።

የቦክስ ቡድኑ ትናንት ከሰዓት ወደ ሀገሩ ሲመለስ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ አቀባበል ተደርጎለታል። በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በተዘጋጀው የአቀባበል መርሀ ግብር ላይም የኢትዮጵያና የአዲስ አበባ ቦክስ ፌዴሬሽኖች ስራ አስፈፃሚዎች፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ተወካዮች በስፍራው ተገኝተው ለስፖርተኞቹ የአበባ ጉንጉን አበርክተዋል።

የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንትና የቡድኑ መሪ አብዱልሰመድ መሐመድ በአቀባበል መርሀ ግብሩ ላይ የቦክስ ብሔራዊ ቡድኑ በማንዴላ ካፕ ውድድር አስደናቂ ተሳትፎ እንደነበረው በማስታወስ፤‹‹ከዚህ በፊት በቦክስ ይሄን ያህል ውጤት ተመዝግቦ አያውቅም፣ በዚህም ደስ ብሎናል›› ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

የአፍሪካ ቦክስ ፌዴሬሽን ፀሐፊ በመሆን በቅርቡ የተመረጡት አቶ ቢልልኝ መቆያ፣ ‹‹እንካን ደስ አላችሁ፣ የተገኘው ውጤት በተወሰነ ድጋፍና በቦክሰኞቹ የግል ጥረት በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል›› በማለት የተናገሩ ሲሆን፤ የአፍሪካ ቦክስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት አዲስ አበባ ላይ በመሆኑ ከዚህ በኋላም ስፖርቱ በተጠናከረ መልኩ እንደሚጠናከር አክለዋል።

በአህጉር አቀፉ ውድድር ላይ 41 ሀገራት በ300 ቦክሰኞቻቸው፤ የአፍጋኒስታን ቡድን ደግሞ በተጋባዥ እንግድነት ተሳትፎ አድርገዋል። በዚህ ውድድር ኢትዮጵያ በ11 ቦክሰኞች ስትወከል ከእነዚህም ውስጥ 4 የሚሆኑት ሴት እንዲሁም 7ቱ ወንድ ቦክሰኞች ናቸው። ከእነዚህም መካከል 5 የሚሆኑትን ተጫዋቾች አዲስ አበባ ፖሊስ ስፖርት ክለብ በማስመረጥ ቀዳሚው ሊሆን ችሏል።

በአጠቃላይ ከቡድኑ አባላት 3ቱ (ቤተልሄም ገዛኸኝ፣ ቤተል ወልዴ እና ተመስገን ምትኩ) ደግሞ በቅርቡ ጋና አክራ ላይ በተደረገው የአፍሪካ ጨዋታዎች ላይ ተሳትፈው ውጤታማ መሆን የቻሉ ቦክሰኞች መሆናቸው ይታወሳል።

አብዛኛዎቹ ተወዳዳሪዎች ለፍጻሜ ሊበቁ የቻሉት በአቻዎቻቸው ላይ ፍጹም የበላይነትን በማስመዝገብ ሲሆን፤ በዝረራ ቀጣዮቹን ዙሮች የተቀላቀሉም አሉ። ከዚህም የተነሳ ለሜዳሊያ ያደረጉት ፍልሚያ ከፍተኛ ቅድመ ግምት ያገኘ ነበር። በዚህም በ50 ኪሎ ግራም በቤተልሄም ገዛኸኝ፣ 54 ኪሎ ግራም ሮማን አስፋ እና በ75 ኪሎ ግራም ተመስገን ምትኩ የብር ሜዳሊያዎች ተቆጥረዋል። የነሃስ ሜዳሊያዎቹ ደግሞ በ 54 ኪሎ ግራም በሱራፌል አላዩ፣ በ60 ኪሎ ግራም በሚሊዮን ጨፎ እንዲሁም በ66 ኪሎ ግራም በቤተል ወልዱ ተገኝተዋል።

ከተመዘገቡት ሜዳሊያዎች መካከል አራቱ በሴት ተወዳዳሪዎች ሲገኙ፤ ሁሉም የአንጋፋው አዲስ አበባ ፖሊስ ስፖርት ክለብ አባላት ናቸው። ቤተል ወልዱ፣ ቤተልሄም ገዛኸኝ፣ ሮማን አስፋ እና ሚሊዮን ጨፎ ደግሞ የሜዳሊያዎቹ ባለቤቶች ናቸው። ሌላኛው በአንድ ዙር ጨዋታ የሞሪሽየስ አቻውን በዝረራ በማሸነፍ ለፍጻሜው ውድድር የበቃውና በ75 ኪሎ ግራም የብር ሜዳሊያ ባለቤት መሆን የቻለው ቡጢኛ ተመስገን ምትኩም የዚሁ ክለብ አትሌት ነው።

በዚህ የውድድር መድረክ ኢትዮጵያን በማስጠራት፣ ባንዲራዋን በማውለብለብ የኩራት ምንጭ የሆኑት የብሄራዊ ቡድን አባላት ከውድድሩ በኋላ በደቡብ አፍሪካ ደርባን ከተማ ነዋሪ በሆኑ ኢትዮጵያውያን፤ ላደረጉት ድንቅ ተሳትፎ ከ450 ሺ ብር በላይ በስጦታ መልክ አበርክተዋል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 16 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You