መጽሐፉ ከምግብ ቀውስ ነፃ ለመውጣት የሚያስችሉ መንገዶችን የሚጠቁም ነው

አዲስ አበባ፦ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ያስመረቀው መጽሐፍ ኢትዮጵያን ከምግብ ቀውስ ነፃ ለመውጣት የሚያስችሉ መንገዶችን የሚጠቁም መሆኑን ተገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ “ኢትዮጵያ፦ ግብርናና ከምግብ ቀውስ ነፃ ስለመውጣት፤ ተቋማዊ ዝግመተ – ለውጥና የግብርናና ገጠር ልማት ሽግግር ጎዳና” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ መጽሐፍ ባለፈው ሳምንት አስመርቋል።

የመጽሐፉን ይዘት ያብራሩት ታደለ ፈረደ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደተናገሩት፤ የመጽሐፉ ጸሐፊ በኢትዮጵያና በሌሎች ሀገራት ያለውን የግብርና ልማትና ዘዴ ተመልክተው የፃፉት ነው። ይህም ቁጭት፣ እልህና ቁርጠኝነት ያለበት ነው።

መጽሐፉ የኢትዮጵያ የመቶ ዓመታት የግብርና ስሪት፣ አወቃቀርና አፈፃፀምን በጥልቀት ይዳስሳል ያሉት ታደለ ፈረደ (ዶ/ር)፤ መጽሐፉ ባለፉት መቶ ዓመታት ለምግብ ቀውስ መንስዔ የሆኑ ችግሮችን ለይቶ በማስቀመጥ ከችግሩ ለመውጣት የሚስችሉ መንገዶችን ይጠቁማል ብለዋል።

መጽሐፉ የግብርናውን ዘርፍ በተረጋጋና በሰከነ አስተሳሰብ መመልከት እንደሚገባ እንዲሁም ዘርፉን ለማሳደግ ቅንጅታዊ አሠራር መዘርጋት እንደሚገባ ያነሳል ያሉት ታደለ ፈረደ (ዶ/ር)፤ ይህንንም ከጊዜ፣ ከተቋም አሠራር፣ ከቴክኖሎጂ፣ ከንግድ ሰንሰለቱ እንዲሆኑ ከተጠያቂነት አንፃር በጥልቀት እንደሚዳስስ ገልጸዋል።

በግብርናው ዘርፍ ያሉ ጠንካራ ጅምር ሥራዎችን በማስፋፋትና በማጠናከር እንዲሁም በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በፍጥነት በመፍታት የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እንደሚቻል በመጽሐፉ በስፋት ይዳሰሳል ብለዋል።

በሀገሪቱ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደ ሕዝብ በጋር መሥራት ያስፈልጋል። ለዚህም ሁለንተናዊ ትብብር ሊኖር እንደሚገባ መጽሐፉ ይጠቁማል ያሉት ታደለ ፈረደ (ዶ/ር)፤ መንግሥት ከተቋማት፣ ተቋማት ከተመራማሪዎች፣ ተመራማሪዎች ከአርሶ አደሩ እና አርሶ አደሩ ከነጋዴው ማኅበረሰብ ጋር እጅና ጓንት ሆነው የሚሠሩበትን መንገድ ያመላክታል ብለዋል።

መጽሐፉ በጌታቸው ድሪባ (ዶ/ር) የተፃፈ ሲሆን እሳቸው በበኩላቸው፤ የግብርናው ዘርፍ በርካታ ችግሮች አሉበት። ይህም ከማዳበሪያ፣ ከቴክኖሎጂ፣ ከአቅም ማነስ፣ ከንግድ ሰንሰለት መርዘም ጋር የተያያዘ ነው። መጽሐፉ ለረዥም ዘመን ሲንከባለል የቆየውን ችግር ከምግብ ዋስትንና ሉዓላዊነት አንፃር በጥልቀት ይዳስሳል ብለዋል።

መጽሐፉ በኢትዮጵያ የ100 ዓመታት የግብርና ታሪክ ውስጥ የተወሰዱ ርምጃዎችን እና የተገኙ ውጤቶችን ይዳስሳል። በዚህም ኢትዮጵያ የተለመደና የቆየ የአስተራረስ ዘዴ ተግባራዊ እያደረገች መሆኑን ይገልፃል ያሉት ጌታቸው ድሪባ (ዶ/ር)፤ መጽሐፉ ይህ ዘመኑን እንደማይመጥን ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮና ልምድ አንፃር ይዳስሳል ብለዋል።

መፅሐፉ የግብርናው ዘርፍ አፈፃጸም ላይ ያተኮሩ 12 ምዕራፎች አሉት። ይህም በአማርኛ እና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች የታተመ ነው። በአማርኛ ቋንቋ የታተመው 347 ገጾች ሲኖሩት በእንግሊዘኛ ቋንቋ የታተመው ደግሞ 435 ገጾች ያሉት መሆኑንም ገልጸዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16/2016 ዓ.ም

Recommended For You