በመዲናዋ ሠላምን ለማረጋገጥ የተሠራው የተቀናጀ ሥራ ወንጀሎችን መቀነስ አስችሏል

አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ ዘላቂ ሠላም ለማረጋገጥ ከማኅበረሰቡና ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሠራ ያለው የተቀናጀ ሥራ ወንጀሎችን በመቀነስ ተጨባጭ ውጤት ማስገኘቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠላምና ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠላምና ፀጥታ ቢሮ በ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈፃፀም ዙሪያ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትናንትናው ውይይት አካሂዷል፡፡

በወቅቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ፤ በመዲናዋ ዘላቂ ሠላም ለማረጋገጥና የሕግ የበላይነትን ለማስፈን ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሠራ ያለው የተቀናጀ ሥራ በመዲናዋ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን መቀነስ ያስቻለና ተጨባጭ ውጤት ያስገኘ ነው ብለዋል፡፡

የመዲናዋን ሠላም ለመጠበቅ ከ21 ባለድርሻ ተቋማትና ከማኅበረሰቡ ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው ያሉት ኃላፊዋ፤ እስካሁን የተሠራው ሥራም በከተማ የሚፈፀሙ ወንጀሎች መጠን የቀነሰና የሕግ የበላይነትን ያስከበረ መሆኑን ገልጸዋል።

“ሕዝብ ያልተሳተፈበት አሠራር ሠላምን አያረጋግጥም። ሠላምን የመጠበቅ ሥራ የአንድ ተቋም ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ማኅበረሰብ ነው” ያሉት ኃላፊዋ፤ የዜጎችን ባለቤት የማድረግ ሥራ በመሠራቱ ሠላሟ የተጠበቀ ከተማ መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል፡፡

መዲናዋ ትላልቅ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች የሚደረግባትና የቱሪስቶች ማረፊያ መሆኗን ታሳቢ ያደረገ ሠላም የማስከበር ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ በከተማዋ እየተሠሩ ያሉ ልማቶችን ለማስቀጠል የተጠናከረ ሠላምን የማስከበር ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

የቢሮውን የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠላምና ፀጥታ ቢሮ የእቅድ፣ በጀት ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር አቶ ማስረሻ ሀብቴ በበኩላቸው ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለሽብር ሥራ ሊውል ሲዘዋወር የነበረ 140 ሚሊዮን 217 ሺህ ብር በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጸዋል።

እንደ አቶ ማስረሻ ገለጻ፤ 92 ሚሊዮን 147 ሺህ 516 የኢትዮጵያ ብር፣ ሦስት ሚሊዮን 824 ሺህ የአሜሪካ ዶላር፤ 44 ሺህ 414 ዩሮ፣ 10 ሺህ 719 የሳውዲ ሪያድ፣71 ሺህ 440 ድሪያም፤ 80 ሺህ 640 የሱዳን ፖውንድ በሕገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር ተገኝቶ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡

እንዲሁም ሁለት ሚሊዮን 887 ሺህ 691 ሐሰተኛ የኢትዮጵያ ብርና 721 ሺህ 816 ሐሰተኛ የአሜሪካ ዶላር ሲዘዋወር ተገኝቶ በቁጥጥር ስር መዋሉንም ተናግረዋል፡፡

ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርና ሐሰተኛ ሰነድን በመጠቀም የሚሠራ የማጭበርበር ሥራ የሀገርን ኢኮኖሚ ይጎዳል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል ሰፊ ሥራ እንደተሠራም አመልክተዋል።

በተጨማሪም ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር ወንጀልን ለመቆጣጠር በተሠራ ሥራ ዘጠኝ ሺህ 329 ቱርክ ሠራሽ ሽጉጥ፣ 98 ክላሽ ከነሙሉ ካርታው፣ ዘጠኝ ብሬን፣ 47 የብሬን ጥይት፣ 47 ኤስ ኬ ኤስ፣ 21 ቦንብና 16 ሺህ 730 የተለያዩ ተተኳሽ ጥይቶች በቁጥጥር የማዋል ሥራ ተሠርቷል ብለዋል፡፡

በመዲናዋ ለቁማር የተሰበሰበ አንድ ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በቁጥጥር የማዋል ሥራ ተሠርቷል ያሉት ዳሬክተሩ፤ የቁማር ማጫወቻ ቤቶች ላይ ሕጋዊ ርምጃ የመውሰድ ሥራ መሠራቱንም አብራርተዋል፡፡

ታደሠ ብናልፈው

 አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16/2016 ዓ.ም

 

 

 

 

 

Recommended For You