አንድ ጤናማ ሰው ሙሉ ተክለ ሰውነት ያለው ነው። ጤነኛና ደስተኛ ሆኖ መኖር፣ መስራት፣ መማር፣ መንቀሳቀስ … የሚችለው መላ ሰውነቱ ጤናማና የተስተካከለ ሲሆን ብቻ ነው። ከሰውነት ክፍሎቹ አንዱ ላይ ጉዳት ቢገጥመው ሙሉ አካል ያለው ሰው የሚሰራውን ያህል ማከናወን ይሳነዋል። ከጊዜ፣ ከጥራት፣ ከርቀትና ቅርበት፣ ወጥቶ ወርዶ ሁሉንም ነገር ሙሉ ጤናማ እንደሆነው ሰው ያክል ሊያከናውን አይችልም።
እጁ የቆሰለ ሰው የህመሙ ስሜት የሚሰማው እጁ ላይ ብቻ አይደለም። ሌላውም የሰውነቱ አካል በህመም ይታወካል። እንደልቡ መስራትና መንቀሳቀስም ይሳነዋል። እግሩ የተጎዳም ሰው፤ ሰው የሚለውን ስያሜ ባያጣም ልክ እጁ ሲጎዳ ስቃይን እንዳስተናገደው ሰው እሱም ተመሳሳይ ስሜት ይሰማዋል። ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ላይ ምንም አይነት ጉዳት ቢከሰት ጉዳቱ ጉዳት የደረሰበት የሰውነት ክፍልን ብቻ ሳይሆን መላ ሰውነትን ያዳርሳል።
ስለዚህ እያንዳንዱ የሰውነት ክፍል የራሱ የሆነ የስራ ድርሻ አለው፤ሁሉም የራሱን የስራ ድርሻ ይወጣል። በሌላ በኩል ደግሞ እያንዳንዱ የሰውነት አካል የስራ ድርሻውን ለመወጣት ጤናን መታደል አለበት። በዚህም ደም በተገቢው መንገድ እንዲሄድና እንዲመለስ የሚያደርገው ልብ ፣ እስትንፋሳችንን የሚያቀለጣጥፈው ሳንባ እና ሌሎችም የእያንዳንዱ የሰውነት ክፍሎች ተግባር የተሟላ መሆን ይኖርበታል። በአጠቃላይ ተፈጥሯዊ ዑደቱን የጠበቀ መሆን አለበት። ይሄ ሲሆን ነው ሰውነታችን ጤናማ የሆነ ዑደቱን የሚከውነው፤ ጤናማ ሆነን የምንኖረው።
ነገር ግን ከሰውነት ክፍል አንዱ በህመም ከተያዘ ወይም ጉዳት ካጋጠመው መታከም አለበት። ሲታከም አንድም የህመም ስቃዩ ይቀንሳል ፤ የሚገባውን የተለመደውን የስራ ሂደት መቀጠል ይጀምራል። ስለዚህ እያንዳንዱ የሰውነት ክፍል በግል ስራ አለው፤ ከግል ስራው ባሻገር ከሌሎች ጋር ተመጋጋቢ የሆነ ተግባርም ይጠበቅበታል፡፡ የተናጥልና የጋራ ስራ ድምር ውጤት ደግሞ ሰውን ሰው ያደርገዋል፡፡ የአንዱ ሰውነት ክፍል ጤናማ አለመሆን ሌላውንም ይበጠብጣል፤ የሁሉም ጤናማ መሆን ሁሉም የተሟላ ስራን እንዲሰራ፣ ጤናማና ደስተኛ ሰው ሆኖ መኖር እንዲችል ያደርጋል።
ይሄን ወደ ብሄር ብሄረሰቦች እንውሰደው። የአንዱ ብሄር በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚም ይሁን በማህበራዊ ኑሮው ጤናማ ከሆነ ሁሉም ወደ እዛ ቦታ ሄዶ ይሰራል፣ ይነግዳል፣ ይማራል ፣ሀብት ንብረት አፍርቶ ተጋብቶና ወልዶ ይኖራል። ነገር ግን ሰላም ከሌለ እንኳን ሌላው ወደ እዛ ቦታ መሄድ ቀርቶ እሱም ይፈናቀላል፤ ይሰደዳል። ይሄ ደግሞ ለሁሉም ብሄሮች ሰላም ማጣት ምክንያት ይሆናል። የአንዱ ሰላም መሆን የሁሉም ሰላም መሆን ነው፤ የሁሉም ሰላም መሆን ደግሞ የአገር ሰላምና አንድነትን ያመጣል።
ዘንድሮም የኢትዮጵያን ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ስናከብር ይሄንኑ እያሰብን መሆን አለብን። የእያንዳንዱ ብሄር ብሄረሰብ ሰላም ለኢትዮጵያ ሰላም ፤ የሰላም መደፍረሱ ደግሞ የእዚያ ብሄር ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሰላም ማጣት ነው። የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ማለት ልክ እንደ አንድ ሰው የሰውነት ክፍሎች ሊታዩ የሚችሉ ናቸው። የአንዱ ህመም የሌላውም ህመም፤ የአንዱ ሰላም የሌላውም ሰላም ተደርጎ መቆጠር አለበት። እያንዳንዱ የሰውነት ክፍል እያንዳንዱ ብሄር ቢሆን በተናጥል ብሄር በጋራ ደግሞ ኢትዮጵያዊ የሚኮንበት አንድነት ተምሳሌት ነው።
የዘንድሮው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ከሌላው ጊዜ ለየት ባለ እና ለኢትዮጵያዊ አንድነት ልዩ ትኩረት በተሰጠበት በዚህ የለውጥ ሂደት ወቅት መከበሩ ደስ የሚያሰኝና ታሪካዊም ነው። ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ብሄሮች ብሄረሰቦች ያሏት አገር ናት። የተለያየ ቋንቋ የሚነገርባት፣ የተለያየ ባህል የሚታይባት፣ የተለያዩ ሃይማኖቶች የሚገኝባት ድንቅ አገር ናት። ይሄ መሆኑ ደግሞ ህብረ ብሄራዊ ገጽታን እንድትጎናጸፍ አስችሏታል። አፋር፣ አማራ፣ ቤኒሻንጉል፣ ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ጉራጌ፣ሶማሌ፣ሀረሪ፣ጋምቤላ፣ሲዳማ…ሁሉ ልዩነታችን ውበታችን ፣ የአንዱ መኖር ለሌላችን ብሎም ለአንድነታችን ዋልታና ማገር መሆኑን ልንረዳ ይግባል። በረባ ባልረባው ብሄር እየመዘዝን መጋጨትና መበሻሻቁን አቁመን ህብረ ብሄራዊነት ውበት መሆኑን ጠብቀን አንድነታችንን እናጎልብት።