አገልግሎቱ የትራፊክ አደጋ ላይ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት መሥራት ይጠበቅበታል

አዲስ አበባ፡– የመንገድ ደኅንነት እና መድን ፈቃድ አገልግሎት የትራፊክ አደጋ ላይ መሠረታዊ ለውጥ እንዲመጣ መሥራት እንዳለበት የከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመንገድ ደኅንነት እና መድን ፈቃድ አገልግሎት የ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወር እቅድ አፈፃፀም በትላንትናው እለት ገምግሟል።

በግምገማው የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥና የተሽከርካሪ ምርመራ ላይ ያለው አሠራር ክፍተት እንዳለበት የተነሳ ሲሆን የተቋሙ የለውጥ ሥራዎች አፈፃፀም በሚመለከት አደረጃጀቱን መሠረት ባደረገ መልኩ ሪፖርት አለማድረግ እና ሪፖርቶች ወቅታዊ የመረጃ ፍሰትና የመረጃ ተዓማኒነት የሌላቸው መሆኑ ተነስቷል።

በወቅቱ የቋሚ ኮሚቴው ዋና ሰብሳቢ ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ እንደገለጹት፤ በሃገራችን በመንገድ ትራፊክ አደጋ ምክንያት የሚከሰተው ሞት፣ የአካል ጉዳትን እና የንብረት ውድመት ቀላል የሚባል አይደለም። በዚህም አገልግሎቱ የትራፊክ አደጋ ላይ መሠረታዊ ውጤት እንዲመጣ መሥራት ይኖርበታል ብለዋል።

ሰብሳቢዋ፤ አገልግሎቱ አሁን እየተገበረው ያለው የመረጃ አያያዝ ሥርዓት አመኔታ የጎደለውና የተዝረከረከ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ የመረጃ ሥርዓቱን ለማዘመን እየተሠራ ያለው ሥራ እንዲፋጠንና ውጤት እንዲመጣ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት ይኖርበታል ሲሉ ጠቁመዋል።

በአፈጻጸም ሪፖርቱ የቀረበው የአገልግሎት እርካታ ቁጥር የተጋነነ መሆኑን የገለጹት ሰብሳቢዋ፤ አገልግሎቱ የአገልግሎት እርካታ በውስን ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ተግባራት መሆን ይኖርበታል ብለዋል።

አገልግሎቱ የተለያዩ ሁነቶችን በማዘጋጀት ለኅብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የተጀመረው አሠራር የሚበረታታ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ተናግረዋል።

የአገልግሎቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አባሶ በበኩላቸው፤ የመንጃ ፍቃድ አሰጣጡን ለመቆጣጠር በክልል ደረጃ አቅጣጫ በማስቀመጥ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኘ ጠቁመው፤ በዚህም የተሽከርካሪ ምርመራ ሲካሄድም በኦንላይን መከታተል የሚያስችል ሶፍትዌር ከኢትዮ- ቴሌኮም ጋር በመሆን የማበልፀግ ሂደት ላይ ነው ብለዋል።

አገልግሎቱ መረጃዎችን በአግባቡ መመዝገብ የሚያስችለውን የዲጂታላይዜሽን ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፤ በቅርቡ ወደ ተግባር የሚገባ ይሆናል ሲሉ አብራርተዋል።

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ ፤ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ተቋሙ የተለያዩ ሥራዎችን አከናውኗል። በዚህም በስድስት ወራት በትራፊክ አደጋ የሞተው የሰው ቁጥር አንድ ሺህ 358 ነው። ይህም ከአምናው ጋር ሲነጻጸር የ514 ልዩነት አለው። ይህም የተሠሩ ሥራዎች ውጤት ማሳያ ነው ብለዋል።

እንደ ሀገር ዘጠኝ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ተሽከርካሪዎች ላይ የቁጥጥር ሥራ ተሠርቷል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ በሀገሪቱ ካለው የመኪና ቁጥር ጋር ሲነጻጸርም በአንድ ተሽከርካሪ በአማካይ ከአምስት ጊዜ በላይ ቁጥጥር ተደርጓል ብለዋል።

ቁጥጥር ከተደረገባቸው ተሽከርካሪዎች መካከል ሁለት ነጥብ 17 ሚሊዮኑ ላይ እርምጃ ተወስዷል። በዚህም አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ለመንግሥት ገቢ ሆኗል ሲሉ አብራርተዋል።

በዋናነት ከሚጠቀሱት የሕግ ጥሰቶች መካከል ትልቁን ቁጥር የሚይዙት የደኅንነት ቀበቶ አለማሰር፣ ትርፍ መጫን እና ቴክኒክ ጉድለቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ዳግማዊት አበበ

 

 

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2016 ዓ.ም

Recommended For You