አገልግሎት ነው፡፡ የፊት ቆዳ እንክብካቤ- የገበያው አማራጮች

የአንድን ሰው ውበት ከሚገልጹ እና ሰዎችም አብዝተው ከሚጨነቁበት ነገር ውስጥ የፊታቸው ቆዳ ነው፡፡ የሰዎች ፊት ጥርት ማለት ያላቸውን ውበት እና ሰላም እንደሚያሳይ ይገለጻል፡፡ ኮሪያውያን በዓለም ላይ ከሚገኙ ሀገራት ከፊት ቆዳ እንክብካቤ ጋር የቆየ ባህ ል እና ልምድ እና ልምድ እንዳላቸው ይገለጻል፡፡

የፊት ቆዳ እንክብካቤ- የገበያው አማራጮች የአንድን ሰው ውበት ከሚገልጹ እና ሰዎችም አብዝተው ከሚጨነቁበት ነገር ውስጥ የፊታቸው ቆዳ ነው፡፡ የሰዎች ፊት ጥርት ማለት ያላቸውን ውበት እና ሰላም እንደሚያሳይ ይገለጻል፡፡ ኮሪያውያን በዓለም ላይ ከሚገኙ ሀገራት ከፊት ቆዳ እንክብካቤ ጋር የቆየ ባህ ል እና ልምድ እንዳላቸው ይገለጻል፡፡

የፊት ቆዳ በየእለቱ ለፀሐይ እና ለንፋስ የተጋለጠ በመሆኑ እንዲሁም በውስጣችን ባሉ የጤና እክሎችም ሆነ በእድሜ ምክንያት በሚመጡ ችግሮች ምክንያት የፊት ቆዳ በቀላሉ ለጉዳት ሊዳረግ ይችላል፡፡ ሰዎችም ፊታቸው ላይ የሚያዩዋቸውን ምልክቶች ለማጥፋት እና ጥርት ያለ የፊት ቆዳን ለመያዝ የተለያዩ ግብዓቶችንና ምርቶችን ይጠቀማሉ፡፡

ውበትን ለመጠበቅ ዘመን አመጣሽ ተጨማሪ መዋቢያ ምርቶችን ከመጠቀም ይልቅ ሰዎች በቻሉት መጠን ያላቸውን ጠብቀውና አጉልተው መቆየት እንደሚችሉ የሥነ-ውበት ባለሙያዎች ቢመክሩም፣ ሰዎች ከዚህ ይልቅ ለተለያዩ ሕክምናዎች ወደ ጤና ተቋማት ይሄዳሉ ወይም የውበት መጠበቂያ ድርጅቶች ሲያመሩ ይስተዋላሉ፡፡

በሀገራችን በስፋት የሚታወቀው የቆዳ ሕክምና ሲሆን፣ ሰዎች ቆዳቸው ላይ የሚመለከቷቸውን ችግሮች ለመታከም የቆዳ ሐኪሞች ወደሚገኙበት የጤና ተቋም ያመራሉ፡፡ ይሁንና ፊትን አልያም ከአንገት በላይ ያለን ቆዳ መንከባከብ የሚያስችል ተቋም ብዙም አልተለመደም፡፡

ዶክተር ሮዚና አረጋዊ በ‹‹ ኤቨር ግሪን ሜዲካል ስፓ›› ውስጥ የፊት እንክብካቤ ባለሙያ (facial treatment specialist) ናት፡፡ ተቋሙ የፊት እንክብካቤ፣ የቆዳ ሕክምና እና የጸጉር ንቅለ ተከላ አገልግሎትን ይሰጣል፡፡ እንደ ዶክተር ሮዚና ገለጻ፤ የቆዳ ሕክምና የሚባለው ከጸጉር ቆዳ እስከ ጥፍር ያለውን የሚያክም ራሱን የቻለ ስፔሻሊስቶች ያሉት ነው፡፡ የፊት እንክብካቤ ደግሞ የፊታችንን የቆዳ ዓይነት፣ የተጎዳበትን ምክንያት ለይቶ በማጥናት በተለያዩ ሳይንሳዊና ተፈጥሯዊ መንገዶች ወደቦታው እንዲመለስ የሚያደርግ አገልግሎት ነው፡፡

ሰዎች እንደሚኖራቸው የቆዳ ዓይነት የሚሰጠው አገልግሎትም ይለያያል፡፡ የፊት ቆዳ እንዲፍታታ ማሳጅ በማድረግ፣ የተለያዩ ግብዓቶችን በመጠቀም ፊት ላይ የወጡ ጠባሳዎች፣ በቡጉር ምክንያት የተፈጠሩ ጥቋቁር ነጠብጣቦች እንዲደበዝዙ ማድረግ፣ በፀሐይ የተጎዳን ፊትና በተለያዩ ምክንያቶች ፊት ላይ ወጥ ያልሆነ ቀለም (ዲስከለሬሽን)፣ ዓይን ስር መጥቆር ሲታዩ እነዚህን በማከም የፊት ትክክለኛ መልክ እንዲወጣና እንዲያበራ የማድረግ ሥራን ይሰራሉ፡፡

‹‹በሀገራችን የፊትን ቆዳ መንከባከብና መጠበቅ በአብዛኛው አልተለመደም›› የምትለው ዶክተር ሮዚና፣ በሌሎች ሀገራት ሰዎች ፊታቸው በፀሐይ እንዳይጎዳ የፀሐይ መከላከያ ቅባቶችን፣ ፊት እንዳይደርቅ የሚያደርጉ ማለስለሻዎችን እና ለፊት ቆዳ ብቻ የተለዩ መታጠቢያዎችን እንደሚጠቀሙ ትገልጻለች፡፡

ዶክተር ሮዚና በዚህ ሥራ ውስጥ ሁለት ዓመት ያህል ጊዜ ቆይታለች፡፡ ‹‹ሥራውን ስንጀምር ሰዎች ብዙም ስለቆዳቸው እውቀት አልነበራቸውም፤ አሁን ብዙ ሰዎች ስለቆዳቸው በማወቅ በተለያየ ጊዜ ወደ እኛ ይመጣሉ›› በማለት ጠቅሳ፣ አንዳንዶች ባለማወቅ ፊታቸው ቀይ እንዲሆን ብቻ በማሰብ ወደ ማእከሉ እንደሚመጡም ትናገራለች፡፡

ዶክተር ሮዚና አሁን ላይ የተለያዩ የውበት መጠበቂያዎች እንደሚተዋወቁ ጠቅሳ፣ የፊት ቆዳ ውበት በራስ መተማመንን ያላብሳል የሚሉ ማስታወቂያዎችም በርከት ብለዋል ትላለች፡፡ ሰዎችም የፊት ቆዳቸውን ለመንከባከብና ጥርት ያለ ለማድረግ ከቆዳ መጠበቂያ ምርቶች ባሻገር በቤታቸው ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ግብዓቶችን ቀምመው እንደሚጠቀሙ ትገልፃለች፡፡ ንጥረ ነገሮቹም እርድን ከማር ጋር ፣ የሩዝ ዱቄትና አቮካዶ ከግብዓቶቹ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ እነዚህ ግብዓቶች ቆዳን የማለስለስና የማፍካት ባህሪ ስላላቸው እንደሚስማማቸው ለማወቅ ከተጠቀሙ በኋላ የማሳከክ፣ የማቃጠልና በቶሎ የመቆጣት ነገርን ካስተዋሉ ቢተውት ጥሩ ነገር ካገኙበት ደግሞ የመረጡትን ግብዓት በሳምንት አንዴ መጠቀም እንደሚችሉ ትመክራለች፡፡ የፊት ቆዳ እንክብካቤ ለሴቶች ብቻ ሳይሆን ለወንዶችም እንደሚያስፈልግ ያነሳችው ዶክተር ሮዚና፣ ይህን አገልግሎት አሁን አሁን ወንዶችም ፈልገው ወደ ማእከሏ እንደሚመጡ አስታውቃለች፡፡

እንደ ዶክተር ሮዚና ገለጻ፤ የሰዎች የፊት ቆዳ ዓይነት የተለያየ በመሆኑ ለአንደኛው ሰው ቆዳ የሚስማማ ግብዓትም ሆነ የቆዳ መጠበቂያ ምርት ለሁሉም ሰው አይሆንም። ስለሆነም ሰዎች የቆዳቸውን ጤና ለመጠበቅ ሲያስቡ አስቀድመው ምን ዓይነት የፊት ቆዳ እንዳላቸው ቢያውቁ ደህና ነው ስትል እንደባለሙያ ትመክራለች፡፡

እንደ እሷ ማብራሪያ፤ ደረቅ የቆዳ ዓይነት ፣ ወዛም (ቅባታማ) ፣ ደረቅ እና ወዛምን አንድላይ የያዘ የቆዳ ዓይነት እና በቶሎ ሊቆጡ የሚችሉ (sensitive) ዓይነት የምንላቸው የቆዳ ዓይነቶች አሉ፡፡ ሰዎች ፊታቸውን በሳሙና በመታጠብ እና ለ15 ደቂቃ በመጠበቅ የቆዳቸውን ዓይነት ማወቅ ይችላሉ። የቆዳ መጠበቂያ ምርቶችን ሲገዙ ምርቱ የያዘውን ግብዓት እና ለየትኛው የቆዳ ዓይነት እንደሚሆን የተሰጡ መግለጫዎችን በማሰብ መግዛት እንደሚገባቸው ገልጻለች፡፡

እነዚህ ምርቶች እና አገልግሎቶች ቅንጡ ዝርዝር ውስጥ ቢካተቱም፣ ዶክተር ሮዚና ግን ፊታችን ከመጎዳቱ በፊት ለመንከባከብ ስም ያላቸውን ምርቶች ከመግዛት  ይልቅ የሚስማማቸውን ምርት ቢገዙ የተሻለ እንደሚሆን ትገልጻለች።

እንደ ዶክተር ሮዚና ማብራሪያ፤ አንድ ደንበኛ የፊት ቆዳው ጉዳይ አሳስቦት ሲመጣ በቅድሚያ ፊቱ ላይ የተመለከተውን ለውጥ የሚጠቀማቸውን ምርቶች እና ምን ዓይነት አገልግሎት እንደሚፈልግ ከባለሙያ ጋር ቆይታ ያደርጋል፤ ከዚያም ስለሚሰጠው አገልግሎት ገለጻ ከተደረገለት በኋላ የቆዳ እንክብካቤ የሚያስፈልገው ከሆነ የፊት አገልግሎት፣ ተከታታይ የቆዳ ሕክምና የሚያስፈልገው ከሆነ ደግሞ ወደ ባለሙያ ይመራል፡፡ የፊት እንክብካቤው የፊት ቆዳን ማጽዳት፣ የተዘጉ ቀዳዳዎች እንዲከፈቱ የሚያደርጉ ግብዓቶችን መጠቀም እና የፊት ቆዳን ዘና እንዲል የሚያደርግ ማሳጅን ያካተተ ሲሆን፣ እነዚህን አገልግሎት ካገኙ በኋላም ማድረግ ያለባቸውን ጥንቃቄና የሚጠቀሟቸውን ምርቶች እንደሚነገሯቸው አብራርታለች።

ለሁሉም የቆዳ ዓይነቶች በአንድ ጊዜ ሕክምና አልያም እንክብካቤ ብቻ መቀየር አልያም ወደቦታቸው እንዲመለሱ ማድረግ ባይቻልም፣ ከአንድ ወር የዘለለ የቆዳ እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸውም ይኖራሉ ትላለች፡፡ አንድ የፊት እንክብካቤ የተደረገለት ደንበኛ ሰውም የፊቱን ውበት የሚያየው ከሁለትና ከሶስት ቀን በኋላ ነው ስትል ታብራራለች፡፡

ሰዎች ለፊታቸው ቆዳ የሚሰጡት ትኩረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የምታነሳው ዶክተር ሮዚና፣ ሰዎች የሠርጋቸው ወቅት ሲደርስ እና የተለየ ፕሮግራም ሲኖራቸው እንደ ኤቨር ግሪን ወዳሉ የፊት እንክብካቤ መስጫዎች ጎራ እንደሚሉም ነው የገለጸችው፡፡ በዚህ ወቅትም ሰዎች ካለባቸው ፕሮግራም አንድ ሳምንት ቀደም ብለው ቢመጡ አገልግሎቱን ካገኙ በኋላ ፊታቸው ላይ ይበልጥ ለውጥ ያዩበታል ስትል ነው ያስገነዘበችው፡፡

ለፊት ቆዳ ተስማሚ የሆነ የፊት መታጠቢያ፣ ማለስለሻ እና የፀሐይ መከላከያ ቅባቶችን አዘውትረው ቢጠቀሙ የተጎዳ ፊታቸውን ወደነበረበት መመለስም ሆነ ያላቸውን ንጹህ ቆዳ እንዳለ እንዲቆይ ማድረግ እንደሚችሉ ዶክተር ሮዚና አረጋዊ ትናገራች፡፡

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You