አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ላይ እየተደረገ ባለው የክትትል ሥራ የግል ትምህርት ቤቶች ከነበሩበት ደረጃ መሻሻሎች እያሳዩ መሆኑ የአጠቃላይ ትምህርት አግባብና ጥራት ሬጎላቶሪ ኤጀንሲ ገለፀ።ነገር ግን አንዳንድ ተቋማት አሁንም ከደረጃ በታች እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙም ተጠቅሷል።
የአጠቃላይ ትምህርት አግባብና ጥራት ሬጎላቶሪ ኤጀንሲ የኢንስፔክሽን ዳይሬክተር አቶ ዘመነ አብዩ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንዳሉት፤ ኤጀንሲው በአሥራ አንድ ወራት የተለያዩ ሥራዎች አከናውኗል።በተያዘው በጀት በዓመት ውስጥ ከኬጂ እስከ መሰናዶ ድረስ ያሉ አንድ ሺ አራት መቶ አስራ አምስት የትምህርት ቤት የውጭ ክትትል ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል።እስካሁን ባለው ክትትል ሥራ የግል ትምህርት ቤቶች ከነበሩበት ደረጃ መሻሻሎች አሳይተዋል።ነገር ግን አንዳንድ ተቋማት አሁንም ከደረጃ በታች እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡
አሁን 90 በመቶ የክትትል ሥራው ተጠናቋል የሚሉት አቶ ዘመነ፤ ተቋማትን ደረጃ አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት እና አራት ተብለው የሚሰየሙ ሲሆን ደረጃ አንድ እና ሁለት የሚባሉ ተቋማት ከስታንዳርድ በታች የሆኑ እና ደረጃ ሦስት እና አራት የሚባሉት ደግሞ ስታንዳርዳቸውን የጠበቁት ትምህርት ቤቶች መሆናቸውን አስረድተዋል። የክትትል ሥራው አጠቃላይ ውጤቱ በቀጣይ እንደሚገለፅ ጠቁመዋል።
የአጠቃላይ ትምህርት አግባብና ጥራት ሬጎላቶሪ ኤጀንሲ የአሥራ አንድ ወር ሪፖርት እንደሚያሳየው፤ በአዲስ አበባ ከሚገኙ የመንግሥትና የግል ትምህርት ቤቶች ቅድመ መደበኛ 701፣ የመጀመሪያ ደረጃ 316፣ ሁለተኛና መሰናዶ 96 እንዲሁም አማራጭና አጋዥ 147 ትምህርት ቤቶች ላይ የክትትል ሥራ እየተደረገ ይገኛል።
በክትትሉ የመንግሥትና የግል ትምህርት ቤቶች በቅድመ መደበኛ ከደረጃ አንድ ወደ ደረጃ ሁለት 24 ትምህርት ቤቶች፣ ከደረጃ ሁለት ወደ ደረጃ ሦስት ደግሞ 52 ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ከደረጃ አንድ ወደ ደረጃ ሦስት አንድ ትምህርት ቤት ሽግግር አድርገዋል።በቅድመ መደበኛ ባሉበት የሚገኙ ደግሞ ደረጃ አንድ 15፣ ደረጃ ሁለት 404፣ ደረጃ ሦስት 67 እንዲሁም ከደረጃ ሁለት ወደ ደረጃ አንድ የተመለሱ አራት እና ከደረጃ ሦስት ወደ ደረጃ ሁለት አስራ አምስት ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ፡፡
እንደ ሪፖርቱ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ከደረጃ አንድ ወደ ደረጃ ሁለት ሦስት ትምህርት ቤቶች እና ከደረጃ ሁለት ወደ ደረጃ ሦስት 40 ትምህርት ቤቶች ሽግግር አድርገዋል።ደረጃ ሁለት 172 እና ደረጃ ሦስት 87 ትምህርት ቤቶች ሽግግር ሳያደርጉ ባሉበት የቆዩ ናቸው። ከደረጃ ሁለት ወደ ደረጃ አንድ አንድ ትምህርት ቤት እና ከደረጃ ሦስት ወደ ደረጃ ሁለት 16 ትምህርት ቤቶች ዝቅ ብለዋል።
በሁለተኛና በመሰናዶ ትምህርት ቤቶች ደግሞ ሽግግር ያደረጉ ከደረጃ አንድ ወደ ደረጃ ሁለት ሰባት ትምህርት ቤት፣ ከደረጃ ሁለት ወደ ደረጃ ሦስት ዘጠኝ ትምህርት ቤቶች ናቸው።ባሉበት የቀጠሉ ደግሞ ደረጃ አንድ አንድ ትምህርት ቤት፣ ደረጃ ሁለት 42 ትምህርት ቤት፣ ደረጃ ሦስት 11 ትምህርት ቤት እንዲሁም 71 ትምህርት ቤቶች ከነበሩበት ደረጃ ሦስት ወደ ደረጃ ሁለት ዝቅ ማለታቸውን ሪፖርቱ ያሳያል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2011
መርድ ክፍሉ