የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የግንባታ ጥራት በጥብቅ ቁጥጥር እየተመራ ይገኛል

 ኮይሻ፡- የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የግንባታ ጥራት ከግብዓት አቅርቦት እስከ ሥራው ሂደት በጥብቅ ቁጥጥር እየተመራ መሆኑ ተገለጸ፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የሲቪል ሥራዎች ቡድን መሪ ኢንጂነር እሸቱ ወርቁ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የግንባታ ጥራት ከግብዓት አቅርቦት እስከ ሥራው ሂደት ድረስ፤ በግንባታው ላይ የየራሳቸው የሥራ ድርሻ ባላቸው ሦስቱም ባለድርሻ አካላት በጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እየተመራ ነው፡፡

በሥራ ተቋራጩ “ዊ ቢውለድ”፣ በሥራው ባለቤት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና በአማካሪው “ስታንቴክ” በኩል የግንባታው የጥራት ደረጃ በተቀመጠው መመዘኛ መሠረት መሠራቱን የመከታተል፣ የመቆጣጠርና የማረጋገጥ ሥራ በመናበብ ይሠራል ብለዋል፡፡

ሦስቱም ባለድርሻ አካላት የግድቡን የጥራት ደረጃ ከማረጋገጥ አንጻር እንደ ተሰጣቸው ኃላፊነት 24 ሰዓት ጥብቅ ክትትል ያደርጋሉ ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በይበልጥም የግንባታውን የጥራት ደረጃ የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለው የተናገሩት ኢንጂነር እሸቱ፤ የግድቡን ሙሌትና የኃይል ማመንጫ ግንባታ 24 ሰዓት እየተከታተለ በጥራት ደረጃው ዝርዝር ላይ በተቀመጠው መሠረት ስለመከናወኑ እያረጋገጠ መሆኑን አስረድተዋል።

የድርጅቱ የጥራት ደረጃ ተቆጣጣሪዎች ችግር አለበት ብለው ያመኑበት ነገር ቢኖር እንኳን ከሚመለከታቸው አመራሮች ጋር በመነጋገር አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጥ ያደርጋሉ ብለዋል፡፡

የጥራት ደረጃን የማረጋገጥ ሥራው ከግንባታው አስቀድሞ በነበረው የቦታ መረጣ እንዲሁም ግድቡን ከሚሸከመው የመሬት አቅም ጀምሮ እንደተረጋገጠ አስታውሰው፤ የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የጥራት ደረጃ እስከ ግድቡ መጠናቀቅ ድረስ በሦስቱም ባለድርሻ አካላት ትብብር ፣ ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገበት የሚቀጥል መሆኑን ኢንጂነር እሸቱ አስረድተዋል።

የተቋራጩ “ዊ ቢውልድ” የጥራት ተቆጣጣሪ ሙያተኛ ኢንጂነር ፍቃዱ ቸኮል በበኩላቸው፤ ለግድቡ ሥራ ብቻ እርሳቸውን ጨምሮ 11 የጥራት ተቆጣጣሪ መሐንዲሶች ቀንና ማታ እየተፈራረቁ 24 ሰዓት ሥራቸውን እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል፡፡

የጥራት ደረጃ ቁጥጥሩ ከግብዓት አቅርቦት ጀምሮ እያንዳንዱ ሥራ የተቀመጡ ዝርዝር መስፈርቶችን አሟልቶ ስለመሠራቱም በተዘጋጀ ቼክሊስት አማካኝነት ቁጥጥር እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

አንዱ የሙሌት ንጣፍ አልቆ የሚቀጥለው ሲደረብ፤ በሚደረብበት ንጣፍ ላይ ፍሳሽ ውሃና ቆሻሻ አለመኖሩን ማረጋገጥ ፤ በሁለት ንጣፎች መካከል ጥብቅ ተያያዥነት እንዲኖር የሚያደርገው ማያያዣ አስቀድሞ መደረጉን መመልከት፤ ለሙሌቱ የሚውለው ኮንክሪት የሙቀት መጠን በሚፈለገው ደረጃ ልክ መሆኑን ማረጋገጥ፤ ጥቅጣቆው ጥብቅ መሆኑን በላብራቶሪ ፈትሾ ማረጋገጥ በቁጥጥር ሥራው ትኩረት ከሚሰጣቸው ጉዳዮች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የአማካሪው “ስታንቴክ” ድርጅት የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ፍተሻ ቡድን መሪ ኢንጂነር አቡ ደጀኔ በበኩላቸው፤ ኮንክሪቱ ተብላልቶ ለሙሌት ከመቅረቡ በፊት የተፈጨው ድንጋይና አሸዋ በተቀመጠው ስታንዳርድ መሰረት መመጠኑ ይረጋገጣል ብለዋል፡፡

እያንዳንዱ ግብዓትና የግንባታ ሥራ የጥራት ደረጃው ሳይንሳዊ በሆነ መለኪያ የሚረጋገጥ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በሙሌቱ ወቅትም የተለያዩ ፍተሻዎች እንደሚደረጉና የጥቅጣቆው ጥብቅነትም በእነርሱም በኩል በላብራቶሪ የሚረጋገጥ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የአማካሪ ድርጅቱን ወክለው የሚሠሩ ቢሆንም የግድቡን የጥራት ደረጃ ሲቆጣጠሩ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በተቆርቋሪነት እና በባለቤትነት መንፈስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ እያንዳንዳቸው 300 ሜጋ ዋት የሚያመነጩ ስድስት ተርባይኖች ይኖሩታል።

ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You