አዲስ አበባ:- በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ዘርፍ ወደ ተሻለ ደረጃ ለመሸጋገር የሚያስችል ቅንጅታዊ አሰራር አለመኖሩ ተገለፀ።
የኢትዮጵያ የሆቴል ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አስቴር ዳዊት በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት ዘርፉን የኋልዮሽ እያስኬደው ያለው ችግር የቅንጅት ማጣት ነው። ብዙዎቹ በዘርፉ የተሰማሩ ባለ ድርሻ አካላት ተቀናጅቶ መስራት አይፈልጉም፤ ሁሉም በግሉ ለግሉ ነው የሚሰራው። በዚህ የተነሳ ዋናውና አገራዊው ጉዳይ ተዘንግቷል።
ዘርፉ በርካታ ባለድርሻ አካላት ያሉት ቢሆንም በእነዚህ ወገኖች በኩል ተናብቦ፣ ተወያይቶና ተያይቶ እንደ አገር የመስራት ችግር አለ የሚሉት ወይዘሮ አስቴር ከእቅድ ጀምሮ እስከ ትግበራ ድረስ በተናጠል የመስራት ሁኔታ እንዳለ ጠቁመዋል።የኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ያዕቆብ መላኩ እንደሚሉት ችግሩ ያለው አስጎብኚ ድርጅቶች አካባቢ ግለኝነት በዝቶ ሳይሆን የመንግሥት ደንቦችና መመሪያዎች ባግባቡ ወደ መሬት ወርደው ሥራ ላይ መዋል ባለመቻላቸው ነው። “እንደ ማህበር እኛ ከመንግሥት ጋርም እየሰራን ነው ያለነው” የሚሉት አቶ ያዕቆብ ከተለያዩ ማህበራት ጋርም እንደሚገናኙ ይገልፃሉ።
ዳይሬክተር አስቴር ዳዊት የሚመሩት ተቋም ያከናወናቸውን ጥናቶች ጠቅሰው እንደሚሉት በአሁኑ ሰዓት በአገሪቱ በርካታ በቱሪዝምና ተያያዥ መስኮች ላይ የሚሰሩ መንግስታዊ የሆኑና ያልሆኑ ተቋማትና ድርጅቶች ቢኖሩም እርስ በእርስ ተናበው ባለመስራታቸው የተፈለገው አገራዊ ለውጥ ሊመጣ አልቻለም፤ ይህ ደግሞ በዚህ ሊቀጥል አይገባም። በቅርብ ፀድቆ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው ሰነድ ይመልሰዋል።
የኢትዮጵያ የሆቴል ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ከመማር-ማስተማር ስራዎቹ ጎን ለጎን በርካታ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በመስራት ወደ መሬት ለማውረድ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል የሚሉት ወይዘሮ አስቴር ይህ በእሳቸው የሚመራ ተቋም ጥረት ብቻውን የትም እንደማያደርስ ይናገራሉ። እንደሳቸው አገላለፅ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሁሉ በአንድ ላይ፤ በጋራ መስራትና ኢንዱስትሪውን ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል።
ዳይሬክተሯ እንደሚሉት በዘርፉ በርካታ ችግሮች አሉ፤ የእነዚህ ድምርም የቱሪስቱን ቁጥርና የመቆያ ጊዜውን እየቀነሰው ይገኛል። እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ደግሞ የአንድ ወይም ሁለት ተቋማት እንቅስቃሴ የትም አያደርስም። የሚመለከታቸው ሁሉ እጅ ለእጅ ተያይዘው መስራትና ችግሮቹን በዘላቂነት መፍታት ይጠበቅባቸዋል።
አሁን በተዘጋጀው የቱሪዝም ልማት ስትራቴጂና በቅርቡም ፀድቆ ሥራ ላይ ይውላል ተብሎ በሚጠበቀው ሰነድ መንግሥት ብቻውን ዘርፉን ያለማል የሚል ነገር የለውም የሚሉት ወይዘሮ አስቴር በሰነዱ ላይ ኢንዱስትሪውን የማልማት ኃላፊነት ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሁሉ የተሰጠና ተቀናጅቶ መስራትን የሚያበረታታ ከመሆኑ አንፃር ወደፊት ሁሉም ከዚሁ አኳያ የተቃኘ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2011
ግርማ መንግሥቴ