. ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸውም ትላንት ከሰዓት በኋላ ችግኝ ተክለዋል
አዲስ አበባ ፡- የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ትናንት በተካሄደው ወርሃዊ ‘’ሰርክ ኢትዮጵያን እናጽዳ’’ የጽዳትና የመንጻት መርሐግብር በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተገኝተው በፅዳትና ችግኝ ተከላ መርሐግብር ላይ ተሳትፈዋል።
ወርሃዊው ሰርክ ኢትዮጵያን እናጽዳ የጽዳትና የመንጻት መርሐግብር አካባቢን ከደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ፣ አዕምሮን ከክፉ ሃሳብ ለማፅዳትና ኃላፊነትን የሚወጣ ኢትዮጵያዊ ለማፍራት ታስቦ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተዘጋጀ ነው፡፡
የጤና ሚኒስትሩ ዶ/ር አሚር አማን በዚህ ወቅት እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ በክረምቱ ወቅት የጤና ተቋማትና ትምህርት ቤቶች ንፁህ እና ሞዴል ሆነው በመጪው አዲስ ዓመት በአዲስ ብሩህ ተስፋ ወደሥራ እንዲገቡ ለማድረግ የሚያስችል ፕሮጀክት መንደፋቸውን ገልፀው የፅዳትና ችግኝ ተከላ ፕሮግራሙ የዚህ ፕሮጀክት አንዱ አካል ነው፡፡
“የጤና ተቋማት ከሌሎች ቀድመው ንፁህ እና ሞዴል ሆነው መገኘት አለባቸው” ያሉ ዶ/ር አሚር “በተለይም በክረምት ወራት የሚከሰቱ ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል የራስንና የአካባቢን ንፅህና መጠበቅ አስፈላጊ ነው፤ ተቋማትን ንፁህ የማድረጉን እና የችግኝ ተከላውን ሥራ ደግሞ በሁሉም ሆስፒታሎች ተግባራዊ እናደርጋለን” ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ኃላፊ አቶ ዳዊት ወንድማገኝ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት የፅዳት ዘመቻው በሀገር አቀፍ ደረጃ የጤና ተቋማትን ለታካሚዎችን ሠራተኞች ምቹ እንዲሆኑ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀው ንቅናቄ ማስጀመሪያ ፕሮግራም ነው ብለዋል፡፡
“ሆስፒታሎች የመብራት፣ ውሀ፣ የፍሳሽ ማስወገጃዎች መዘጋት እና መሰል ችግሮች አሉባቸው” ያሉት ኃላፊው እነዚህን ችግሮች ለመፍታትም በክረምቱ ወራት በበጎ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ ሥራ በሆስፒታሎች ይሠራልም ብለዋል፡፡
በየሆስፒታሎቹ ለዚህ የበጎ ፈቃድ ሥራ የሚሆኑ ችግሮች የተለዩ ሲሆን ለአብነትም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እድሳት እና የመፀዳጃ ቤቶች ጥገናን ጨምሮ አሥር ያህል ሥራዎች እንደሚከናወኑ ኃላፊው ጨምረው ገልፀዋል፡፡
በፅዳት እና ችግኝ ተከላ ዘመቻው የጤና ሚኒስትሩ ዶ/ር አሚር አማንን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሠራተኞች እና የሆስፒታሉ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
በተመሳሳይም ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው እና ም/ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመሆን ትላንት ከሰዓት በኋላ በCMC አደባባይ አካባቢ ችግኝ ተክለዋል፡፡
በድልነሳ ምንውየለት
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2011