ልጆች እንዲያብቡ ያንብቡ

ሰላም ልጆች እንዴት ናችሁ? ልጆችዬ ትምህርት እና ጥናት እንዴት ነው? በርትታችሁ እየተማራችሁ እንደሆነ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ልጆች መቼም ከትምህርት ጋር የተያያዘም ሆነ ከትምህርት ውጭ ያሉ እውቀቶችን ለማግኘት ንባብ አንዱ መሳሪያ መሆኑን ትረዳላችሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ ታዲያ ሳምንት በገባነው ቃል መሠረት ዛሬ ስለ ልጆች የንባብ ባሕል የምንላችሁ ይኖረናል፡፡ ከእናንተ የሚጠበቀው ታዲያ ትኩረት ሰጥታችሁ ማንበብ ብቻ ነው። ወይም ወላጆቻችሁ የሚያነቡላችሁ ከሆነ እነርሱን በጥሞና ብትከታተሉ መልዕክቱን ለመረዳት በሚገባ ያግዛችኋል፡፡

የልጆች የንባብ ባህል እንዲያድግ፣ እንዲስፋፋ እና እንዲጎለብት ከሚሠሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች መካከል ‹‹ኢትዮጵያን ሪድስ›› አንዱ ነው፡፡ ድርጅቱ አራተኛው ዓመታዊ የሕፃናት ንባብ ጉባኤን ‹‹በቅደመ መደበኛ ትምህርት ልጆችን በንባብ መደገፍ›› በሚል መሪ ሃሳብ ሚያዝያ 3 እና ሚያዝያ 4 ቀን 2016 ዓ.ም አካሂዷል፡፡

በዚህ መድረክ ላይ አንጋፋ የሚባሉ ደራሲዎች፣ የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች፣ ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ከተለያዩ ቦታ የመጡ እንግዶች የእናንተን የንባብ ባህል ለማሳደግ በጥቅሉ ‹‹ምን ይሠራ? በማለት ውይይት አድርገዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ውይይት መደረጉ ደስ ይላል አይደል? ‹‹አዎ፡፡›› ምክንያቱም እናንተ አንብባችሁ ተመራማሪ፣ ጠያቂ፣ አስተዋይ እና የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎች እንድትሆኑ ለማገዝ ያለመ ነውና፡፡

ሌላው በዚህ ጉባኤ የ‹‹አምባ ትምህርት ለተቸገሩ በጎ አድራጎት ማሕበር›› ተማሪዎች ለታዳሚዎች የሚከተሉትን መዝሙር አቅርበዋል፡፡

አንቺ እማማ ኢትዮጵያ የእኔ የእኔ፣

እኔም የአንቺ አንቺም ለእኔ፡፡

ርሃብ ጥማቴን አትውጂም አንቺ ፣

ክፋቴን ሲባባ አንጀቴ፡፡

ነፃነት ብርሃን ብሩህ ወጋገንሽ፣

አንድነት ሁሌም ይኖር ለዘላለም፣

እናት ዓለም፡፡

ኢትዮጵያ አንቺ ካለሽ ሁሉ ለእኔ፣

ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የእኔ፡፡

ልጆችዬ መዝሙሩን ወደዳችሁት? ስለ ኢትዮጵያ በጋራ ሲያዜሙ ብትመለከቷቸው ደግሞ በጣም ደስ ይላሉ፡፡ ሌላኛውን መዝሙራቸውን እናስነብባችሁ አይደል?

መተኪያ ለሌላት ፣

እስኪ ልዝፈልንላት፣

እማምዬ እንበላት፡፡

ዘወትር ትኩሳቴን ፣

ለምታዳምጠው፣

ለእማምዬ ልዝፈን ፣

ለማትለወጠው፡፡

ፌቴ ተኮሳትሮ ማየት መች ትሻለች፣

ስደሰት በመሳቅ ሳዝን ትከፋለች፡፡

ሁሉ ልጅ ለእናቱ ገና ልጅ ነውና ፣

እናቱን የማይወድ ምን ፍጡር አለና?

መተኪያ ለሌላት ፣

እስኪ ልዝፈልንላት፣

እማምዬ እንበላት፡፡

በማለት ዘምረዋል፡፡

በጉባኤው ከውይይቶች በተጨማሪ የልጆች መጻሕፍት አውደ ርዕይ ተካሂዷል፡፡ በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ፣ በጉራጌኛ፣ በትግርኛ፣ በፈረንሳይኛ፣ በእንግሊዝኛ እና በተለያዩ ቋንቋዎች የተጻፉ የተረት እንዲሁም ልጆችን ያስተምራሉ ተብለው የተጻፉ መጻሕ ፍት ቀርበዋል፡፡

በጉባኤው የተገኙት አቶ መዝገቡ ባያዝን የትምህርት ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚ ናቸው። እርሳቸው እንደ ትምህርት ሚኒስቴር ‹‹ኢትዮጵያ ሪድስ››ን ጨምሮ በሕፃናት ንባብ እድገት ላይ ከሚሠሩት ጋር በጋራ ለመሥራት ፍላጎት አለን ብለዋል፡፡ የሕፃናት የንባብ ባህል ለማሳደግ የንባብ ቦታዎችን እንዲሁም ሁኔታዎችን ማዘጋጀት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ሕፃናቱ በአቅራቢያቸው ቤተ መጻሕፍት እንዲገነባ እና መሰል ሥራዎችን መሥራት የሁለም ኃላፊነት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የብሔራዊ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት አገልግሎት (ወመዘክር) ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ይኩኖ አምላክ ይባላሉ፡፡ ተረት ተረት ለታዳሚዎች በማቅረብ ልጆች ከተረት ብዙ ነገሮችን መማር እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ‹‹ኢትዮጵያ ሪድስ›› የልጆች ንባብ እንዲያድግ እየሠራ ያለውን ተግባር በማመስገን ከሁሉም የበለጠ መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ልጆችዬ! በአጠቃላይ በጉባኤው የሕፃናት የልጆች የንባብ ባሕልን ለማሳደግ ‹‹ኑ በጋራ እንሥራ›› የሚል መልዕክት ተላልፏል፡፡

እንደ ‹‹ኢትዮጵያ ሪድስ›› ያሉ ድርጅቶች፣ በግለሰብ፣ በመንግሥት፣ በልጆች መጻሕፍት ፀሐፊዎች እንዲሁም ወላጆቻችሁ እናንተ አንብባችሁ እውቀት እንድትሸምቱ ጥረት እንደሚያደርጉ ተገንዝባችኋልን ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ታዲያ እናንተስ የንባብ ክህሎታችሁን ለማዳበር ምን ጥረት እያደረጋችሁ ነው? ከትምህርት እና ከጥናት የተረፋችሁን ጊዜ በንባብ እያሳለፋችሁ ነው? ወላጆቻችሁ ወደ ቤተ መጻሕፍት እንዲወስዷችሁ ትጠይቃላችሁ? በዚህ አጋጣሚ ያገኛችሁትን አጋጣሚ በመጠቀም የምታነቡ ልጆች በጣም ጎበዞች መሆናችሁን መግለጽ እንፈልጋለን፡፡ በዚሁ ቀጥሉበት ማለትም እንወዳለን፡፡ የንባብ ልምምድ ያልጀመራችሁ ወይም ገና የሆናችሁ ልጆች አትጨነቁ ግን ቶሎ ጀምሩ ነው የምንላችሁ፡፡

በሉ ልጆችዬ ለዛሬው በዚሁ እናብቃ አይደል? በሰላምታ እንደጀመርን ሰላም በመመኘት መሰነባበት ተገቢ ነው፡፡ እናም ልጆች መልካም የትምህርት፣ የጥናት እና የንባብ ጊዜ እንዲሆንላችሁ ተመኘን!

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን  ሚያዝያ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You