ንስር አሞራ እስከ 70 ዓመት የሚኖር የእድሜ ባለፀጋ ነው። ነገር ግን 70 ዓመት ሙሉ በደስታ ከመኖሩ በፊት በእድሜው አጋማሽ ማለትም ከ35 – 40 ባለው እድሜው ላይ ከባድ ነገር ይገጥመዋል። የመጀመሪያው ምግቡን ለማደን የሚገለገልበት ጥፍሮቹ ከመጠን በላይ ስለሚያድጉ ምግቡን ከመሬት ላይ ማንሳት ያቅተዋል። ሁለተኛው አጥንትን ሳይቀር የመስበር አቅም ያለው አፉ (መንቁሩ) ስለሚታጠፍና ስለሚጣመም ምግቡን እንደወትሮው መመገብ ይሳነዋል። ሶስተኛው ክንፉና በአካሉ ላይ ያሉ ላባዎቹ ስለሚከብዱት ያ ሰማየ ሰማያትን እየሰነጠቀ ይበር የነበረው ኃይሉ ይከዳዋል።
እነዚህ ሶስት ከባድ ነገሮች ንስር አሞራ በእድሜው አጋማሽ የሚያጋጥሙት ከባድ ችግሮች ናቸው። አሁን ንስር አሞራ ያለው ምርጫ ሁለት ነው። ወይ ካረጀ አካሉ ጋር ዝም ብሎ ተቀምጦ ሞቱን መጠበቅ አልያም ደግሞ አምስት ወር የሚፈጅ ስቃይና መከራ ያለበት መስዋዕትነትን ከፍሎ ቀሪውን 35 ዓመት በደስታ ማሳለፍ። የመጀመሪያውን ከመረጠ በእድሜው አጋማሽ ይሞታልና ታሪኩ እዛ ጋር ያበቃል። ሁለተኛውን ምርጫ ከመረጠ ግን የሚቀጥሉት አምስት መስዋዕቶች ማለፍ ይጠበቅበታል።
በመጀመሪያ ከፍተኛ ተራራ ላይ በመውጣት የብቻውን ጎጆ ይቀልሳል። ቀጥሎ ጎጆ ከቀለሰ በኋላ የመጀመሪያ ስራው የአፉን መንቁር ከአለት ጋር በማጋጨት ነቅሎ ይጥላል። ይህን ካደረገ በኋላ አዲስ መንቁር ይወጣለታል። መንቁሩ እስኪያድግ ድረስ ታግሶ በጎጆው ምንም አይነት ምግብ ሳይመገብ መቆየት ግዴታው ይሆናል። አዲስ መንቁር ከበቀለለት በኋላ በአዲሱ መንቁሩ የገዛ እግሩን አሮጌ ጥፍር ነቃቅሎ ይጥለዋል።
አዲሱ የእግር ጥፍር ከበቀለለት በኋላ ደግሞ ይህንን አዲስ ጥፍር እንደ መሳሪያ በመጠቀም በሰውነቱ የተጣበቁትን፣ እንዳይበር እንቅፋት የሆኑትን፣ የገዘፉና ያረጁ ላባዎችን ነቃቅሎ ይጥላል። በምትኩ አዲስ ላባ ያበቅላል።
ይህን አምስት ወር በዚህ መልኩ በጀግንነት ከተወጣ በኋላ እንደገና ራሱን በራሱ ወልዶና ወጣት ሆኖ ወደ ንስሮች መንደር ብቅ ይላል። አንተም በተመሳሳይ መንገድ አልፈህ በአዲስ ሕይወት ከፍ ብለህ መብረር ትችል ዘንድ ከንስር አሞራው ሕይወት ትምህርት መውሰድ ይኖርብሃል።
አየህ በብዙ ችግሮች ተተብትበህ ሊሆን ይችላል። ግን ደግሞ ከችግሮችህ ተላቀህ አዲስ ሕይወት መምራት ትፈልጋለህ። አዲስ ሕይወት ለመምራት ደግሞ የውሳኔ ሰው መሆን ይጠበቅብሃል። ግን ደግሞ ለመወሰን ብዙ ታመነታ ይሆናል። ብዙ ሰበብ ትደረድር ይሆናል። ለውሳኔ ግዜው አሁን አይደለም፤ ትክክለኛ ግዜ ሲመጣ እወስናለሁ ልትልም ትችላለህ። በውሳኔ ደግሞ ግዜው አልደረሰም የሚል ነገር የለም። ሁሌም ቢሆን የውሳኜ ግዜው አሁን ነው፤ ዛሬ ነው።
ለመሆኑ ችግርህ ምን ኖራል? ከተቀጣሪነት ተላቆ የራስን ቢዝነስ መጀመር ነው?፣ ካለብህ ሱስ መላቀቅ ነው?፣ ትዳር መመስረት ነው?፣ ትምህርት መማር ነው? መንፈሳዊ ሕይወትህ ላይ መጠንከር ነው? ጤናህን መጠበቅ ነው? ወይስ ሌላ ችግር? ብቻ በሕይወትህ እስከመጨረሻው ድረስ መለወጥ የምትፈልገው አንድ ነገር ይኖራል፡ ፡ ጥያቄው ይህን ነገር እንዴት ታሳካዋለህ የሚለው ነው። ለዚህ ደግሞ ከላይ የተነሳው የንስር አሞራ ሕይወት ጥሩ ምሳሌ ይሆንሃል።
ልብ ብለህ ከሆነ ንስር አሞራው ሰባ ዓመት መኖር የሚችለው ሰላሳ አምስት ዓመቱ ላይ ሲደርስ ቆራጥ ውሳኔ ማሳለፍ የሚችል ከሆነ ብቻ ነው። አለበለዚያ ግን ሰባ ዓመት የመኖር እድል አያገኝም። ተፈጥሮ የሰጠችውን እድል ከዳር ማድረስ አይችልም። አንተም ቢሆን አስካሁን ድረስ በሕይወትህ ትርጉም ያለው ለውጥ አላመጣህ ይሆናል። በስራህና በገቢህ ደስተኛም ላትሆን ትችላለህ፣ የጤንነትህ ሁኔታም አደጋ ላይ ሊሆን ይችላል። ትምህርትህ፣ የፍቅር ግንኙነትህም ጥቁር ጥላ አጥልቶበት ሊሆን ይችላል።
እናም አሁንም አልረፈደምና ሕይወትህን እስከወዲያኛው ድረስ ለመቀየር ከፈለክ እንደ ንስር አሞራው አሁኑኑ መወሰን ይኖርብሃል። ይህ ሲባል መጥፎ ልማዶች ካሉብህ ማቆም፣ ጤናህ አደጋ ላይ ከሆነ ስፖርት መስራት፣ ተቀጣሪነት ከሰለቸህ በራስህ ቢዝነስ ለመፍጠር ዝግጁ መሆንና ወዘተ የመሳሰሉትን ለማድረግ ፍቃደኛ መሆን ይጠበቅብሃል። ይህን ለማድረግ ዝግጁ ከሆንክና ካደረከው ደግሞ ልክ እንደ ንስር አሞራው አሁን የገጠመህን ችግር ቀርፈህ በቀጣይ የተሻለ ሕይወት የመኖር እድል ይኖርሃል።
አይተህ ከሆነ ንስር አሞራው በእድሜው አጋማሽ ላይ የገጠመውን ችግር ለማለፍ ብርቱ መሰዋዕትነትን መክፈል አለበት። ስለዚህ አንተም የምትልግው የሕይወት ደረጃ ላይ እስከምትደርስ ድረስ ዋጋ መክፈል አለብህ። ውጣ ውረዶችን ማለፍ ይጠበቅበሃል። ለችግሮች እጅ መስጠት የለብህም። ያለበለዚያ ግን በተለመደው የሕይወት መንገድ ለመቀጠል ወስነሃልና በሕይወትህ አዲስ ነገር አይኖርም። ተመሳሳይ ሕይወት ነው የምትኖረው። የሚቀየር ነገር አይኖርም። ስለዚህ ምርጫው ያንተ ነው። ወይ ትንሽ ተሰቃይቶ በዘለቄታው ሕይወትህን መቀየር፤ አልያም ደግሞ አሁን ያለውን ሕይወትህን ተቀብለህ መኖርና ይችን ምድር ተሰናብቶ መሄድ!
የንስር አሞራውን የመጀመሪያ ውሳኔ ከመረጥክ የተሻለና ዘላቂ ሕይወት ለመኖር ወስነሃልና ልክ ንስር አሞራው ደረጃ በደረጃ ከባድ መስዋዕትነትን በሕይወትህ መክፈል ይጠበቅበሃል። ከራስህ ጋር ምከር። የሚጠቅምህንና የሚጎዳህን ላይ። በዙሪያህ ያሉና ተተብትበው የያዙህ ችግሮች ምን እንደሆኑ እወቅ። አለስራህ ያሉህ እንቅፋቶች የትኞቹ እንደሆኑም አንድ በአንድ ለያቸው። ከዛም ለውሳኔ ዝግጁ ሁንና ወደተግባር ግባ። አይተህ ከሆነ ንስር አሞራው 35 ዓመቱ ላይ ሲደርስ እንደልብ እደዳያድን ካደረጉት የሰውነት ክፍሎች ውስጥ አንዱ መንቁሩ ነው። ስለዚህ በልቶ ለመኖር መንቁሩ ወሳኝ ነውና አዲስ መንቁር እንዲበቅልለት መንቁሩን ከአለት ጋር እያጋጨ ነቅሎ ጥሎታል። በምትኩም አዲስ መንቁር በቅሎለታል።
አንተም ብትሆን ከዚህ በፊት አላሰራ ያለህን መጥፎ ልማድ ተውና በአዲስ ተካው። ትሰራለህ፣ ትደክማለህ ግን በስራህ ውጤት አይኖርህ ይሆናል። ስለዚህ መነቀል ያለባቸውና ያረጁና ያፈጁ አሰራሮችን የምትከተል ከሆነ እነርሱን ተዋቸውና አዲስ፣ ቀላልና ብልህነት የታከለባቸው አሰራሮችን ተከተል። ይህ በስራህ ብቻ ሳይሆን በግል ሕይወትህ ላይም ጭምር ሊሰራ ስለሚችል ተግባራዊ አድርገው። ያኔ ሕይወትህ እየተለወጠ እንደመጣ በግልፅ ይታይሃል።
ንስር አሞራው መንቁሩ ካደገለት በኋላ ለማደን ይገለገልባቸው የነበሩትንና አሁን ግን ያረጁትን ጥፍሮቹን ለመንቀያነት ይጠቀምባቸዋል። ጥፍሮቹ ሲያድጉ ደግሞ ለመብረር የከለከሉትን ክንፎቹን ነጭቶ ይጥልበታል። አየህ ! አንተጋም ያሉት ችግሮች ተደራራቢ ሊሆኑ ይችላሉ። ለአፍታም አስቸጋሪ ሆነው ሊታዩህ ይችላሉ። ነገር ግን በሕይወትህ አዲስ ነገር ለማምጣት እስከፈለክና እስከወሰንክ ድረስ አንዱን ችግር ስትፈታ ሌላኛው ይቀረፋል። ብቻ አንዱን ችግር ለመፍታት አንተ ቁርጠኛ ሁን እንጂ የአንዱ ችግር መፍትሄ ለሌላውም መፍትሄ የማይሆንበት ምንም ምክንያት አይኖርም።
በሕይወትህ ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት የምታደርገው ሂደት በአንድ ጀምበር ውጤት አያመጣም። ልክ እንደ ንስር አሞራው የራሱ የሆነ ግዜ ይወስዳል። ንስር አሞራው ዳግም ወደ ወጣትነት ለመመለስ አምስት ወራት ፈጅቶበታል። ግን ደግሞ ለአምስት ወር የከፈለው መስዋዕትነት ተጨማሪ 35 ዓመታትን እንዲኖር እድል ሰጥቶታል። ሁሉም ነገር በአንድ ጀምበር አልሆነምና በሕህይወትህ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት ከፈለክ አንተም ወስደህ ሕይወትህን ለመለወጥ ስራ። ትእግስት ይኑርህ። ምክንያቱም ትግስትና የምትከፍለው መስዋዕትነት ኋላ ላይ መልሶ ይከፍልሃልና።
የንስር አሞራው ታሪክ ላይ ሁለት አይነት የተፈጥሮ ምርጫ ማለትም መኖር ወይም መሞት ያለ ቢሆንም በተፈጥሮ ሕግ መሰረት ማንም ፍጥረት አስከመጨረሻው ድረስ ይፍጨረጨራል እንጂ ራሱን ለሞት አጋልጦ የሚሰጥ የለም። እርግጥ ንስር አሞራዎች ሁለት አይነት ምርጫ ቢኖራቸውም ተስፋ ያልቆረጡት ካልሆኑ በስተቀር አብዛኞቹ የሚጠበቅባቸውን መስዋዕትነት ከፍለው ሕይወታቸውን እስከመጨረሻው ያስቀጥላሉ። ይህ ደግሞ የተፈጥሮ ግዴታም ጭምር ነው።
የሰው ልጅም ቢሆን እንዲህ ሳይፍጨረጨር በተስፋ መቁረጥ ብቻ ውድ ሕይወቱን አሳልፎ አይሰጥም። በዚህች ምድር እስካለ ድረስ ይፍጨረጨራል፣ ላይ ታች ይላል፣ በብዙ ይፈተናል። በመጨረሻም ይህችን ምድር ለቆ ወደማይቀረው ይሄዳል። ስለዚህ አንተም ብትሆን እርግጠኛ ነኝ በሕይወትህ ተስፋ አትቆርጥም። ጥቂት ነገሮች ይዘው ሊሆን ይችላል እንጂ ሕይወትህን እስከመጨረሻው መለወጥ ትፈልጋለህ።
ብዙ ሰዎች ከተስፋ መቁረጥ ወጥተው ሕይወታቸውን በብዙ መልኩ ቀይረዋል። በርካቶች አለቀላችሁ ሲባሉ ዳግም ተፈጥረው ዓለምን ጉድ አሰኝተዋል። አከተመላቸው የተባሉ ብዙ ሰዎች ወደሕይወት ዳግም ተመልሰዋል። ለዚህ ደግሞ የንስር አሞራው ታሪክ ለብዙዎች ትምህርት የሚሰጥ ነው። በተለይ በሕይወት መንገድ ሁለት አማራጭ ቀርበው የተሻለውን ነገር ግን ለጥቂት ግዜ ስቃይ ያለውን ውሳኔ መርጦ እንዴት ሕይወትን መቀየርና ተስፋ ሳይቆርጡ እስከመጨረሻው የሕይወት ፍፃሜ ድረስ መጓዝ እንደሚቻል ትልቅ ማሳያ ነው።
አንተም ቢሆን ቀሪ ሕይወትህ ያማረና የሰመረ ይሆን ዘንድ ከአሁኑ ወስነህ ሕይወትህን መቀየር ይኖርብሃል። በስራህ፣ በኑሮህ፣ በትዳርህ፣ በትምህርትህና በመሳሰሉት ለውጥ ማምጣት ከፈለክ ዛሬውኑ ወስነህ ማስተካከል የሚገቡህን ነገሮች ማስተካከል ይጠበቅብሃል። ከንስር አሞራው ትምህርት ወስደህ ሕይወትህን በዘለቄታው መቀየር ይጠበቅብሃል። አንተ ደግሞ ሰው ስለሆንክ ምን ከማድረግ ምንም እንደማያግድህ ማወቅ አለብህ። ይህን ስታደርግ የመኖር ትርጉሙ ይገባሃል። እንደንስር አሞራውም ከፍ ብለህ ትበራለህ።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5/2016 ዓ.ም