እየተገባደደ ባለው በዚህ ሳምንት በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ለአንድ ወር የዘለቀው የረመዳን ጾም በታላቅ ሃይማኖታዊ ስርዓት ተጠናቅቆ አንድ ሺህ 445ኛው የኢድ-አል ፈጥር በዓል በተለያዩ ሀይማኖታዊ ክንዋኔዎች ተከብሯል።
ረመዳን የእስልምና እምነት ተከታዮች በሚከተሉት የቀን አቆጣጠር ዘጠነኛው ወር ነው። የረመዳን ወር በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ የጾም ወር ሲሆን፣ የረመዳን ወርን ማንኛውም እድሜው ለጾም የደረሰ እና ጤነኛ የሆነ የእምነቱ ተከታይ እምነቱ በሚያዘው መንገድ በመጾም፣ በመጸለይና በመስገድ እንዲያሳልፍ እምነቱ ያዛል። በረመዳን ወር የእምነቱ ተከታዮች ቀኑን ሙሉ ይጾማሉ፤ ጾማቸውን የሚፈቱት ጸሀይ በምትጠልቅበት ምሽት ላይ ይሆናል፤ ጾሙን የሚፈቱትም በአብዛኛው ከቤተሰብ እና ከወዳጆቻቸው ጋር በመሆን በማፍጠርና ማእድ በማጋራት ነው።
የእምነቱ ተከታዮች ይህን የጾም ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላቀ መልኩ በመተሳሰብ በማሳለፍ ይታወቃሉ፤ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በናፍቆት የሚጠበቀው እና የሚጾመው ይህ የረመዳን ጾም እና የእምነቱን ተከታዮች ለየት የሚያደርጋቸው በጾማቸው ማብቂያ ላይ የሚኖራቸው የአፍጥር ስነ-ስርዓት ነው፤ በዚህ የአፍጥር ስነስርአት ላይ ቴምር፣ የተለያዩ ጣፋጭ ምግቦች፣ ፍራፍሬዎች በምግብ ጠረጴዛቸው ላይ ማቅረብ የተለመደ ተግባራቸው ነው።
በዚህ የአፍጥር ስነስርአት ወቅት ችግረኞች፣ አቅመ ደካሞች፣ ወዘተ በእጅጉ ይታሰባሉ። ያለው ለሌለው ማጋራቱ የግድ ነው። ይህ በዚህ የጾም ወቅት የሚታይ መረዳዳትና መደጋገፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተና እየሰፋ መምጣቱን ከሚዘጋጁ የአፍጥር መርሀ ግብሮች መረዳት ይቻላል።
በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ የረመዳን ወር የተቀደሰ ወር ነው። በዚህ የተቀደሰ የጾም ወቅት የእምነቱ ተከታዮች ከመጾም እና ከመስገድ ባለፈ በሚጾሙበት እና ጾማቸውን በሚፈቱበት ወቅት ሌሎች የእምነቱ ተከታዮች የሆኑ አቅመ ደካሞችን በማሰብ፣ ማገዝ እና ምግባቸውን ማማሏት ለማይችሉ ያላቸውን ማካፈል ይኖርባቸዋል። ይህ የእምነቱ ተከታዮች ሊያደርጉት ከሚገባ ድርጊት ውስጥ በዋናነት የተቀመጠ ነው።
የዘንድሮውን የረመዳን ወር ጾም ለየት የሚያደርገው ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ዘንድ ካሉ አጽዋማት መካከል በትልቁ የሚነሳው ዐብይ ጾም ወይንም የሁዳዴ ጾም አንድ ቀን መጀመሩ ነው።
ሁለቱም አጽዋማት በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ቦታ ይሰጣቸዋል። በመሆኑም በዚህ የጾም ወቅት የእምነቱ ተከታዮች ራሳቸውን ዝቅ በማድረግ በጾም እና በጸሎት ወደ ፈጣሪያቸው ይቀርባሉ። በዚህ ወቅት የእምነቱ ተከታዮች በተለያዩ ኩነቶች እርስ በእርስ ያላቸውን መረዳዳት እና መደጋገፍ፣ አብሮነታቸውን አሳይተዋል።
የእስልምና እምነት ተከታዮች በዚህ የረመዳን ወር ከታመሙ፣ በእርግዝና ላይ ከምትገኝ አልያም ከወላድ ሴት እንዲሁም ደግሞ በዚህ ወቅት የወር አበባ ከምታይ እንስት በስተቀር ሁሉም የእምነቱ ተከታይ ከንጋት አንስቶ ጸሀይ እስከምትጠልቅ ድረስ ያለውን ጊዜ በሙሉ በጾም እና በስግደት ያሳልፋል።
የጾም ሀሳቡ ራስን ለመንፈሳዊነት ማስገዛት እና ስጋን ማድከም እንደመሆኑ፣ የእምነቱ ተከታዮችም ይህን ተግባር የሚያደርጉት በትልቅ ደስታ ነው። ነገር ግን ለ12 ሰዓት ያህል ከምግብ፣ ከውሀ መከልከል ይኖርባቸዋል። ይህ የጾም ወቅት እና ሰዎች ከሚኖራቸው የእለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴና የስራ ክንውን ጋር ሲገጥም ሊፈጠር የሚችለውን የድካም ስሜት መገመት አከብድም። ይህ ግን ለእምነቱ ተከታዮች ቦታ የለውም።
የእለት ስራቸውን አጠናቀው ጨርሰው እንደየ ስራቸው ባህሪ ጸሀይ ስትጠልቅ ለማፍጠር ወደ ቤት መመለስ ይኖርባቸዋል። ሰዓቱ ከመድረሱ አስቀድሞ ወደ ቤታቸው ያልደረሱ ሲያጋጥሙ በትራንስፖርት አገልግሎት መስጫዎች ላይ የእምነቱ ተከታዮች ብቻም ሳይሆኑ የሌሎች እምነት ተከታዮች ጭምር የሚሰጧቸው ቅድሚያ የመተሳሰቡን፣ የመከባበሩን ልክ ያመለክታል።
በዚህ የረመዳን ወር ከመጾም፣ ከሰላት (ስግደት) ባለፈ ሰደቃ (ምጽዋት) በማድረግ እንዲያሳልፉ እምነቱ ያዛል። አንዳንድ የእምነቱ ተከታዮች ለኢፍጣር ሰዓት ቤታቸው መድረስ ያልቻሉትን በመንገድ፣ በትራንስፖርትና በመሳሰሉት ስፍራዎች ላይ በመሄድ ውሀ እና ቴምር ሲያቀብሏቸው ተመልክተናል።
በዚህ የጾም ወቅት ጾሙ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ያሉትን 30 ቀናት ምዕመናኑ በቤታቸው ከማፍጠር ይልቅ የተለያዩ ምግቦችን፣ ጣፋጭ ብስኩቶችን አዘጋጅተው ወደ ሌሎች የእምነቱ ተከታዮች ቤትና ወዳጆቻቸው ቤት ስንቃቸውን አዘጋጅተው በመሄድ፣ ከአቅመ ደካሞች ጋር እና ከተቸገሩ የእምነቱ ተከታዮች ጋር በመሆን ጭምር ያፈጥራሉ።
ይህ ክንውን እርስ በእርስ ከመጠያየቅ፣ ያለን ከማካፈል ባሻገር አንዱ የአንዱን ችግር እንዲረዳ እና በቅርበት እንዲመለከት የሚያደርግ የረመዳን ወር ታላቅ የእምነቱ እሴት ነው። ይህ የእምነቱ ተከታዮች ከወዳጆቻቸው ጋር በመሆን የሚጋሩት ማዕድንና አብሮነትም በተለያዩ ተቋማት ዘንድ ዘልቆ እየገባ ይገኛል። ተቋማትና ሰራተኞቻቸው በተቋሙ ለሚሰሩ የእምነቱ ተከታዮች የኢፍጣር ስነ-ስርዓት በጋራ በማዘጋጀት ያላቸውን አብሮነት ሲያሳዩም ይስተዋላል።
በሌሎች ሀገራት በረመዳን ወር ላይ ሰዎች በየቤታቸው በር ላይ ለኢፍጣር ሰዓት የሚሆኑ ምግቦችን እና ጣፋጮችን በማዘጋጀት ወደ ቤቱ በመሄድ ላይ ያለ ሰው በመንገድ ላይ ሳለ አፍጥር ስነ- ስርዓት ቢደርስበት በደረሰበት ቤት ገብቶ እንዲያፈጥር የማድረግ የቆየ ልማድ አላቸው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችንም ይህን መሰል የጎዳና ላይ የኢፍጣር ስነ-ስርዓቶች በደማቅ ስነስርአት ማካሄድ ጀምረዋል። ዘንድሮን ጨምሮ ባለፉት ዓመታት በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የተካሄደው ታላቅ የአፍጥር ስነስርአት ለእዚህ በአብነት ይጠቀሳል። በዚህ የጎዳና ላይ ኢፍጣር ስነስርአት የእምነቱ ተከታዮች ከሌሎች የእምነቱ ተከታዮች ጋር በመሆን ከቤታቸው ወጥተው በአደባባይ ላይ በመሰብሰብ በጋራ የአፍጥር ስነ-ስርዓቱን ያካሂዳሉ። ቦታውን ለአፍጥር ሰዓት ዝግጁ በማድረግ በኩል ደግሞ የሌላ እምነት ተከታይ የሆኑ ኢትዮጵያንም በተለያዩ ተግባራት ላይ ተሳትፈው በማድረግ አብሮነታቸውን እያሳዩ ናቸው። ይህ የአንዱ እምነት ተከታይ ሌላው እምነት ተከታይ አብሮነቱን የሚገልጽበት ሁኔታ እየተጠናከረ መጥቷል፤ የአንዱ እምነት ተከታይ የሌላው እምነት በአልና ስርአት በደማቅ ስነ ስርአት እንዲካሄድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተም ይገኛል።
ይህ የረመዳን ወር የእምነቱ ተከታዮች በደስታ የሚጾሙት እና እምነቱ የሚያዛቸውን ተግባር በቅንነት የሚያከናውኑበት ሆኖ ጾሙ በተጀመረበት ወቅት ‹‹ ረመዳን ከሪም ›› መልካም የጾም ወቅት እንደተባለው ሁሉ ጾሙ ሲጠናቀቅም እንዲሁ ‹‹ ኢድ ሙባረክ ›› በማለት መልካም ምኞታቸውን የሚገልጹበት ነው።
ጾሙ ሲጠናቀቅም የእምነቱ ተከታዮች ወደ መስጂድ በመሄድ የተለያዩ ሀይማኖታዊ ስነ -ስርዓቶችን በማከናወን በአሉን ያሳልፋሉ፤ ይህ ክብረ በዓልም በአዲስ አበባ እና በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በደማቅ ስነስርአት ተከብሯል። በበአሉ ላይ ዑላማዎች፣ ሼኾች፣ ኢማሞች እና መላ የእምነቱ ተከታዮች ላይ ተሳትፈዋል።
በዕለቱም ምዕመናኑ በዓሉን አቅመ ደካሞችን፣ ወላጅ አልባ ህጻናትና፣ ረዳት የሌላቸው ደካሞችን በመርዳት እና በመንከባከብ እንዲያከብሩ የእምነቱ መሪዎች ያሳስባሉ፤ የእምነቱ ተከታዮች በዚሁ መሰረት በአሉን ያከብራሉ። የረመዳን ወር አብቅቶ በኢድ ቀን ምዕመናኑ እንግዶችን በቤታቸው የሚያስተናግዱ ሲሆን እነሱም ወዳጆቻቸውንም ሆኑ የተቸገሩ ሰዎችን ጣፋጭ እና ሌሎች ስጦታዎችን በመያዝ ይዘይራሉ አልያም ይጎበኛሉ።
በረመዳን የጾም ወቅት ላይ ወጣቶችም ሆኑ የእምነቱ ተከታዮች እምነቱ የሚያዘውን ተግባር በማድረግ ጊዜቸውን የሚያሳልፉ ሲሆን ይህ ተግባር የረመዳን ወር ካለቀ በኋላ በሚኖረው ጊዜም ጭምር ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚገባም ሁሌም ይመከራል።
በዚህ የጾም ወር ሕዝበ ሙስሊሙ እና ክርስቲያኑ በጋራ ያሳለፉት የጾም ወቅት በመሆኑ የእምነቱ ተከታዮች አንድነታቸውን እና አብሮነታቸውን በሚያጎለብት መልኩ አንዳቸው ለአንዳቸው ያላቸውን መልካም ተሳትፎ እና ሕብረት ያሳዩበት ወቅት መሆን መቻሉ በአምነቱ መሪዎችና በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ/ዶ/ር/ ተገልጧል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ 1445ኛው የኢድ አልፈጥር በአልን አስመልክተው ባስተላለፉት መልእክት በአሉ የሰላም የደስታና የአብሮነት ማሳያ መሆኑን አስታውቀዋል። በረመዳን ወር የታየውን መረዳዳትና መልካም ስነ ምግባር ተጠናከረው መቀጠል እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼኅ ሱልጣን አማን ኤባ በረመዳን ጾም ወቅት የዳበሩት የመረዳዳት ተግባሮች ሊቀጥሉና የማህበራዊ መስተጋብሩ አካል ሊሆኑ አንደሚገባ ነው ያስታወቁት።
ጠቅላይ ሚኒስትር/ ዐቢይ አሕመድ /ዶ/ር/ የኢድ አልፈጥር በአልን አስመልክተው ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክታቸው ያሳለፍነው የረመዳን ወር አያሌ ችግረኞችን ያገዝንበት፣ እርስ በርስ የተደጋገፍንበትና ኢትዮጵያውያን ሕብረ ብሄራዊ አንድነታቸውን በጽናት ያሳዩበት ወር መሆኑን አስታውቀዋል። እነዚህ ሁሉ ለመንገዳችን የመብራት ምልክቶች ናቸው፤ የሚገጥሙንን ተግዳሮቶች በአንድነት ሆነን ልናልፋቸው እንደምንችል ያስገነዝቡናል ሲሉም በጾሙ ወቅት የታየውን የመረዳዳት እሴት አስታውቀዋል።
‹‹ ብልህ ሰው ረመዳንን እስከ ረመዳን ያቆየዋል፤ የሚል አባባል አለ፤ በረመዳን ጾም ጊዜ ያገኘውን በረከት፣ መንፈሳዊ ኃይልና ጠላትን ድል የማድረግ አቅም እስከሚቀጥለው ረመዳን ድረስ ይጠቀምበታል፤ ወደ ሁዋላ አይመለስም አንደማለት ነው››› ሲሉም አስገንዝበዋል።
እኛም በመጋቢት ለውጥ ያገኘናቸውን እሴቶች ብልጽግናችንን እስከምናረጋግጥ ቀጣይ ምእራፍ ድረስ ይዘናቸው ልንዘልቅ ይገባል፤ ሰላም ይቅርታ እና ፍቅር እሴቶቻችንን ናቸው፤ በፍቅር መደመርና በይቅርታ መሻገር ዋናው መርሃችን ነው ሲሉም አያይዘው አስታውቀዋል።
የእምነቱ መሪዎችና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ/ዶ/ር/ እንዳሉት፤ እነዚህ በረመዳን ወቅት እና በኢድ አልፈጥር በአል ላይ በእምነቱ ተከታዮች አልፎም ተርፎ በሌሎች እምነት ተከታዮች ዘንድ የተተገበሩ የመረዳዳት፣ የመተሳሰብ እሴቶች በእርግጥም በርካቶችን ታድገዋል፤ ይህ እንዲሆኑ ያደረጉት እነዚህ አካላት ሊደነቁ ይገባቸዋል። በቀጣይም እነዚህን እሴቶች በመጠቀም ችግረኞችን ይበልጥ መታደግ እንዲቻል፣ እነዚህን ውብ እሴቶች በመጠቀም ሀገርንም ለማሻገር ሁሉም ወገን አጥብቆ መስራት ይኖርበታል።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 4 ቀን 2016 ዓ.ም