ብዙ ነገር ያምረናል፣ ካማረን ውስጥ አንድ አስረኛውን እንኳን ርቆናል። ትላንትን ለብቻ ማለፍ፣ ዛሬን በራስ መሻገር..ነገን ለብቻ መጠበቅ አልድን እንዳለ የቆላ ቁስል የነፍስ ቁርጥማት ነው። ምን ሆነሃል ብሎ? እንደጠያቂ የነፍስ ወዳጅ የለም። ያጣንው ጠያቂ ነው..እንደገበያ ሕዝብ በከበቡን ወዳጆች መሐል ቆመን ጠያቂ ያጣን፣ ለማንም የማናሳየውን የብቻ ታሪካችንን ለመጋራት ከሺ አንድ ያጣን አጀበ ብዙ ነን።
በምን አለው የቀረቡን እንዲሸሹን የተቆራኙን ናቸው። ኪሳችንን ካልሆነ ምናችንንም ለማፍቀር አቅም የሌላቸው ጊዜያዊ ፍጡራን ናቸው። በምን ሆንክ የቀረቡን እነርሱ እንዳይርቁን የተጠጉን፣ በልባችን በኩል የተዋሓዱን፣ እኛነታችንን ካልሆነ ምናችንንም ለማየት ብርታት የሌላቸው ዘላለማዊ ጥላዎቻችን ናቸው። በዚህ የሕይወት ተሞክሮው ውስጥ ሳለ ነው ለምን እንደቀረበችው ካልተረዳት ትዝብት ጋር የተዋወቁት። መጀመሪያና መጨረሻ የሌላት..የት ጀምራ የት እንደምታበቃ ፌርማታ አልባ ሀሳብና ምኞት አላት። በመጨረሻውን በመጀመሪያዋ ሸሽጋ ወዳጇ አደረገችው። እየቆየ ሲመጣ የተደናበረባትን ያህል አደናበራት። አሁን ላይ እሱ እንጂ እሷ ስለሱ በምንም እርግጠኛ አይደለችም። ምንሽ ነው ላሏት ባሌ ከማለት በስተቀር በመተማመን የምትመሰክረው እውነታ የላትም።
አንድ ቀን በጀርባዋ ቆሞ የሚወደውን ማጅራቷ ላይ ያንቀላፋ ስስ ጸጉሯን በሌባ ጣቱ በቀስታ እየነካካ እንዲህ አላት..‹መጀመሪያ የሌላት ሴት ነሽ..
እስኪጨርስ ሳትጠብቀው ‹ምን ማለት ነው? ስትል ጠየቀችው።
‹እንዲህ እንደአሁኑ..!
ሳይገባት ዝም አለች። አንዳንድ ነገሩ አይደለም ለመረዳት ለጥያቄ የማይመችም ነው። እንዲህ እንደአሁኑ በሚል ሀሳብ ውስጥ ምን አይነት ጥያቄ መነሳት ይችላል? ወደኋላዋ ዞራ ምን ለማለት እንደፈለገ አጥብቃ ልትጠይቀው ፈልጋ ነበር ግን መልሱ በጥብቆ በመጠየቅ ውስጥ የሚገኝ እንዳልሆነ ሲገባት ተወችው። ማጅራቷን እየነካካ እና እሷም በሚገርም ስሜት ውስጥ ሆና ጥቂት ሰነበቱ።
ሌላ ጊዜ ደግሞ ‹ምንም የሚወደድ ነገር ከሌላት ሴት ጋር አብሮ መኖር ለወንድ ልጅ ምን ማለት እንደሆነ የገባሽን ንገሪኝ? ሲል ፊት ለፊቷ ተሰየመ። ለምን እንደጠየቃትና መልሱን ለምን እንደፈለገው አታውቅም። ከጥያቄው ኋላ ዳግመኛ ባሏ ላይሆን ቆርጦ ፊቷ የመጣ መሰላት። ጠይቋት መልሳለት አታውቅም..ብትመልስለት እንኳን መጨረሻዋ መደናገር ነው። እጇን ስቦ ከሌሎቹ ለይቶ የቃልኪዳን ቀለበቷ ያረፈበትን ጣቷን እየነካካ ‹በዚህ ጣት በኩል እኔና አንቺ ሌላውና ሌላው የተወራረስነው ውርስ አለ? እውነት ይሄ ጣትና ይሄ ቀለበት ሁለት ጥንድ ነፍሶችን የማስተሳሰር አቅም አለው? ነው ወይስ ከለመደብንና ከተለማመድነው የዘር ውርስ መውጣት አቅቶን ሳናምንበት የምናደርገው ነው? ፍቅር ስፍራው የት ነው? እምነት..እውነት ካለልብ በጣት ብቻ እውን መሆን ይችላሉ? እንዲህ ብሎ የቃልኪዳን ጣቷን ሳም አደረገው። የምትሽረው እንዲህ ባለው ሁኔታ ነው..
ስንት ጥያቄዎችን አከታትሎ እንደጠየቃት ለማወቅ ብታስብ አልሆነላትም። መልስ ከሌለው ጥያቄ ጋር ሰው የሆነ የሚለው በትክክል እሱን የምትገልጽበት ነገሯ ነው። ካሰረላት የዳይመንድ ቀለበት ላይ ዓይኑንና ልቡን ሳያሸሽ ‹ይሄ ቀለበትና ይሄ ጣት ለእኔና ላንቺ ፍቅር ባይተዋሮች ናቸው ከማለቱ ‹ሳታምንበት ነበር ያሰርክልኝ? የሚል ጥያቄ መጣባት። ለመጠየቅ እስኪናገር መጠበቅ ለምን እንዳስፈለጋት አታውቅም..እንደእስከዛሬዋ ቢሆን እየተናገረ የምታወራ ነበረች ዛሬ ግን እስኪጨርስ ጠበቀችው። በትዕግስቷ በኩል የጥያቄዋን መልስ አገኘችው..‹የትኛውም ወንድ ወደየትኛዋም ሴት ሕይወት ሲገባ እጅ መንሻ ይዞ ነው። ያንን ባላደርግ አንቺም የእኔ አትሆኚ ቤተሰቦችሽም አይሰጡኝም ነበር ሆኖም በሆነውና ስለሚሆነው ልክ አይደለም የሚል ሀሳብ የለኝም። በአንዳንድ የዓለም ሀገራት ሴት ልጅ ወደትዳር ስትገባ በባሏ በኩል በሴትነቷ፣ በእናትነቷ፣ በሚስትነቷና የምትካስ ናት..በእርግጥ እናትም ሚስትም ለምትሆን ሴት ይሄ ያንሳል..ግን ለፍቅር ዋስትና አይሰጥም በሚለው አቋም ስር ነኝ› አለ።
ዛሬ ደግሞ ይሄን አላት ‹አንቺ ሰፊና ግዙፍ ዓለም ነሽ ከዚች እዚች አትሁኚ..
‹ከዚች እዚች ማለት?
‹ወደነገ የማይንጠራራ ሀሳብና እምነት ማለቴ ነው› ሲል አጉድላ ግማሽ ያደረገችውን የወይን ብርጭቆ ሞላላት። ወይኑን ወደብርጭቆው ሲያንቆረቁርና እንዳይፈስ የሚያደርገውን ጥንቃቄ በውስጧ እያደነቀች ምን አይነት ወንድ? ቢሆን ነው ሳልረዳው ባሌ ያደረኩት የሚል ግብዳ ሀሳብ ወደቀባት። ከሀሳብ የገላገላት በምን እንደፈገጋታ ያላወቀችውና ፊቱ ላይ ድንገት ያስተዋለችው ፈገግታው ነበር። ሳቁን ትወድለታለች..በጺም የተሸፈነ ፊቱ በነጫጭ ጥርሶች ሲታጀብ ቡራቡሬ ሰው ያስመስለዋል።
ልትናገር ስትል የወይን ብርጭቆውን አነሳ። ተጎንጭቶ ሲጨርስ ወሬ ለመጀመር ተሰናድታ ነበር ግን አልተሳካለትም። በአጠጣጡ ተማርካ ፈዘዘችበት። አጠጣጡን አለማድነቅ አልቻለችም..በአንድ ትንፋሽ ብርጭቆውን ርቃኑን አስቀርቶ የመጨረሻውን ጉንጩ ውስጥ አቁሮ ጠበቃት። በብርጭቆው ወደብርጭቆዋ እየጠቆመ ጠጪ እንጂ በሚመስል ሁናቴ በዓይኑ ምልክት ሰጣት። ብርጭቆዋን ስታነሳ ጠብቆ ጉንጩ ውስጥ ያቆረውን ወደሆዱ ዋጠ።
እንደሱ መሆን አትችልበትም። ሕይወቱ ከሕይወቷ በብርሃን ፍጥነት የቀደመ ነው። ዝግ ማለት አይችልበትም..ሲኖር በፍጥነት ነው። ሲራመድ፣ ሲያስብ፣ ሲወስን፣ ሲያወራ፣ ሲበላ፣ ፍቅር ሲሠራ፣ ሲያፈቅር፣ ሲጠላ በችኮላ ነው..ግን ተደነቃቅፎ አያውቅም። የእሱ ፍጥነት ይሁን የእሷ ትግታ ማንኛው ልክ እንደሆነ አታውቅም። በራቀ ልዩነት ውስጥ ተግባብተው መኖራቸው የሁልጊዜም ትካዜዋ ነው። አይገባም..አትረዳውም።
‹ፍቅር ልክ የሚሆነው እንዴትና መቼ እንደሆነ ሳናውቅ የምናፈቅር ነን። ወይንን ከፍቅር ጋር አስተሳስረው የሚጽፉ ጸሐፊዎች፣ ጨረቃና ፀሐይን የፍቅር በኩር አድርገው በሚገጥሙ ገጣሚያን መሐል የፍቅርን ቦታ ለይቶ ማወቅ ፓስፊክን በማንኪያ የማጉደል ያህል አስቸጋሪ ነው። የሁሉም ሰው የፍቅር ታሪክ ከወይን ጋር የተነካካ ነው..ፀሐይና ጨረቃ፣ አድማስና ጠረፍ፣ ከዋክብትና ሰማይ ያልገቡበት የፍቅር ታሪክ የለንም። ፍቅርን እዛ ማን ሰቀለው? ፍቅርን ከነዛ ጋር ማን ደባለቀው?..ፍቅር ዝምታ ነው..መናገር አለመቻል። ማስረዳት..መግለጽ አመቻል። ፀሐይና ደመና በፍቅራችን መሐል ከገቡ አፍቃሪ ሳንሆን አክቲቪስት ነን፣ ምክንያት ካልሽ ፍቅር መናገር የማይችል፣ ስሜቱን በወጉ መግለጽ የማይችል ዱዳ ስለሆነ።
‹አንተ ሰው መቼ ይሆን የሚገባኝን የምትነግረኝ? ሳትገባኝ ባንተ መረዳት ብቻ ለሁለት ዓመት ፍቅረኛዬ አደረኩህ። አሁን ግን እንድትገባኝ እፈልጋለሁ..
ሾው ላይ ብትቀርብ ታሪካዊ ከምትሆን ደማቅ ሳቅ ጋር ‹ያልገባሽ ምኔ ነው? ሲል ሁልጊዜ ላድርገው ቢል በማይችለውና ድንገት ችሎት በሚያደርገው የሆነ እይታ ቃኛት። በዚህ እይታው እሷም እሱም ሰው መሆን አይችሉም። ወደሆነ ጥልቅ የፍቅር የስሜት ይረመረማሉ።
‹ምንህ የገባኝ አለ? ለሁለት ዓመታት ታሪኬ አድርጌህ ምንህም አልገባኝም። ግን እኔና ፍቅር ለአንተ ምንድነን?
‹አንቺ ማለት ፍቅርን፣ ፍቅር ማለት አንቺን ሆናችሁ በመንገዴ ላይ ተቀምጣችኋል። የትም ያላገኘሁትን የፍቅር ትርጉም በላቀ ዋጋ ባንቺ ውስጥ አግኝቼዋለሁ። ከአንቺ ጋር ካልሆነ ከማንም ጋር ፍቅር አያምርበትም። ያልገባሁሽ ገዝፌብሽ ሳይሆን የኔን መረዳት የሚቋቋም አቻ ሴትነት እየፈለግሽ እንጂ። አንቺ በሕይወቴ ውስጥ እንዲህ የምገልጻት የማትደገሚ ዕጣ ክፍሌ ነሽ።
‹ለእኔ ግን እንደዛ አይደለህም!
‹እንዴት ነኝ?
‹ሳይገባት ሁሉ ነገሯን የሰጠችው ምድር ላይ በምንም የማትለውጠው ታሪኳና ሕልሟን ነህ።
‹ይሄን ነበር ፍቅር የምለው..
‹የቱን..?
‹አሁን ያልሽውን..ፍቅር ከገባት ሴት ካልሆነ ከማንኛዋም ሴት የማይፈልቀውን የሕይወት ውሃ። ያልገባሁሽ ገዝፌብሽ እንዳልሆነ አሁን በደንብ የገባሽ ይመስለኛል› ሲል ከተቀመጠበት ተነሳ። አንዳንዴ በሚያያት እይታው ነፍሷ ውስጥ ሕይወት ጥሎ አጠገቧ አረፍ አለ።
በመቀጠልም ‹ትላንትና ነፍሴ ስትናገር እኔ ሳደምጥ ነበር..ምን እንዳለችኝ ታውቂያለሽ? እሷን ትረሳና፣ እሷን ታስከፋና፣ እሷን ትገፋና፣ እሷን ትተውና፣ እሷን ታብልና ከሕይወት ገጽ ላይ ትፋቃለህ..የማትጠቅም..የማትረባ ትሆናለህ› አለችኝ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 4 ቀን 2016 ዓ.ም