ታሪክ እንደሚያስረዳው፣ ነብዩ መሐመድ የእስልምና እምነት በመካና አካባቢው በሚሰበክበት ዘመን በአንዳንድ ቀንደኛ ነጋዴዎች፣ ባለሥልጣናት እና መሰል አካላት ተቃውሞ ሲደርስበት እምነቱ በትክክል የገባቸው ተከታዮቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ በመላካቸው ምክንያት እስልምና ኢትዮጵያዊና የኢትዮጵያውያን እምነት ሆኗል። መልካም እሴቶቹ ሁሉ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን እሴቶች ናቸው ማለት ነው።
ባለፈው ዓመት ተሾመ ብርሃኑ ከማል የተባሉ ጸሐፊ እንዳሰፈሩት የእስልምና እምነት በዓለም የተሰራጨው በሦስት ዋና ዋና ወቅቶች ሲሆን፤ የመጀመሪያው ከ632-800 ባለው ዘመን ነው፡፡ በዚህ ዘመን እስልምና በኢትዮጵያ፣ በፋርስ፣ በሶሪያ፣ በሰሜንና በምሥራቅ አፍሪካ፣ በሰፓይንና በሲሲሊ ተቀባይነት አግኝቷል፡ ፡ ከዚህ የምንረዳው ከሌሎች ታሪካዊ ዳራዎች በተጨማሪ ኢትዮጵያ እስልምናን ከተቀበሉት አገራት አንዷ ብቻ ሳትሆን ቀዳሚዋም መሆኗን ነው።
ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ሁሉ ከብዙ ሺህ ዓመታት ጀምሮ በፖለቲካና በኢኮኖሚ ግንኙነት ብቻ ሳይሆን በጠበቀ ማኅበራዊ ግንኙነት የምትታወቀው ኢትዮጵያ፣ ለእስልምና ሃይማኖት ቅርብ እንድትሆን ካደረጉ ምክንያቶች መካከል መሰል መስተግባሮች ከዋነኞቹ ተርታ የሚዘረዘሩ ስለመሆናቸው የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።
ከላይ የጠቀስናቸው ጸሐፊም «ኢትዮጵያ በጥንታዊነታቸው ከሚታወቁ የንጉሠ ነገሥት ግዛቶች አንዷ ስትሆን ሥልጣኔዋ ከግብፅ ሥልጣኔ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ንጉሥ ሰለሞን የተባለ የሔብሩ ንጉሥና ንግሥተ ሳባ የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት ሁለቱን አገሮች አስተሳስረዋል የሚል ታሪክ አለ፡፡
በ3ኛው ክፍለ ዘመን የግሪኩ ቅኝ ገዥ ግብፅን በቅኝ ግዛትነት ይዞ በነበረበት ጊዜ ኪነጥበቡን ወደ ኢትዮጵያም አምጥቶ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በዚህ ጊዜ የአይሁዶች ሃይማኖት ለረዥም ምዕተ ዓመታት በኢትዮጵያ ተንሰራፍቶ የነበረ ቢሆንም እንኳን ከ330 ጀምሮ ክርስትና ገብቷል፡፡ ምንም እንኳን ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ይህን ያህል ዓመታት ቢወስድበትም በዓረቢያና በኢትዮጵያ መካከል በነበረው ጂኦ-ፖለቲካዊ ቀርቤታ እስልምና ወደ ኢትዮጵያ የገባው በራሱ በሳዑዲ ዓረቢያ እንደተጀመረ በራሳቸው በነቢዩ መሐመድ ዕድሜ ነው፡፡″ በማለት ያሰፈሩት ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነውና ወደ ዛሬው ረመዳን በዓል እንለፍ።
ከአምስቱ የእስልምና ማዕዘናት ውስጥ አንዱ የሆነውና ሃያ ዘጠኝ ወይም ሠላሳ ቀናትን የሚዘልቀው ረመዳን በሂጅራ አቆጣጠር ዘጠነኛው ወር ሲሆን፤ በሙስሊሞች ዘንድ የፆምና ጸሎት ወር ነው፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ረመዳን የሚጀምረው በየዓመቱ ከ10 እስከ 12 ቀናት ቀደም ብሎ ሲሆን፤ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ኢስላማዊው የዘመን አቆጣጠር በጨረቃ የሒጅራ አቆጣጠር ስለተመሠረተ ነው፡፡ ወሮቹ 29 እና 30 ቀናት የሚረዝሙ ናቸው።
ከእምነቱ አስተምሕሮ መረዳት እንደሚቻለው፣ ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከምትጠልቅ ድረስ መፆም ለአቅመ አዳም እና ሄዋን ለደረሱ ሙስሊሞች ፋርድ (ግዴታ) ነው። አልጋ ላይ የዋሉ በሽተኞች፣ መንገደኞች፣ አረጋውያን፣ ጡት አጥቢ እናቶች፣ የስኳር በሽተኞች፣ ወይም የወር አበባ ያላቸው እንስቶች ሲቀሩ ሁሉም ይፆማል።
ከሱቢህ (ፈጅር) አዛን ቀደም ብሎ በሌሊት (ንጋት) ላይ የሚበላው ምግብ (የቅድመ-ጎህ ምግብ) ሱሁር እና ምሽት ከመግሪብ አዛን በኋላ የሚፈታበት (የሚፈጠርበት) ምግብ (ፀሐይ ስትጠልቅ ፆም የሚፈታበት ምግብ) ኢፍጣር ይባላል። ይህ እንግዲህ ላለፈው አንድ ወር የዘለቀና በዛሬው እለት የተፈታ ፆም ነው።
ከእምነቱ ተከታይ ወገኖቻችን መረዳት እንደቻልነው፣ የፆም መንፈሳዊ ሽልማቶች (ሰዋብ) በረመዳን ውስጥ እንደሚባዙ ይታመናል። በዚህ መሠረት፣ ሙስሊሞች ከምግብ እና መጠጥ ብቻ ሳይሆን፣ ከትምባሆ ምርቶች፣ ከባለቤታቸው ጋር ፆታዊ ግንኙነት፣ እንዲሁም ከአጠቃላይ መጥፎ ባሕሪያት በመቆጠብ፤ ሰላት እና ቁርዓን መቅራትን በማዝወተር ከንጋት እስከ ፀሐይ መጥለቅ የሚዘልቀውን የፆም ወር ያሳልፋሉ። ይህንን እዚህ መጥቀስ ያስፈለገበት ምክንያት የፆም ወሩ በዚህ መልክ ማለፉን በጨረፍታ ለመጠቆም ሲሆን፤ ቀጥለን የእስልምና እሴቶችን እንመልከት።
ብዙውን ጊዜ ሙስሊሞች በጸሎት፣ በሰላት እና በሰደቃ (ምጽዋት) እንዲሁም ሥነ ምግባራቸውን ለማሻሻል በመጣር ፆሙን ያሳልፋሉ። ይህም በሃዲስ “ረመዳን ሲደርስ የገነት በሮች ይከፈታሉ፤ የሲኦል (ገሃነም) በሮች ይዘጋሉ እና ሰይጣናት ይታሰራሉ።” የሚለውን መሠረት ያደረገ ስለመሆኑ በሃይማኖቱ ታሪክ ጸሐፍት በተደጋጋሚ ሲጠቀስ ይታያል። እንደ ኢትዮጵያ ባሉና እስልምናና ክርስትና ብዙም ተለያይተው በማይታዩበት ሀገርም ይህ የእለት ተእለት የእምነቱ ተከታዮች ተግባር መሆኑ ይታወቃል። እስላማዊ እሴቶችን በተመለከተም እንደዛው።
የመቻቻል፤ የመረዳዳት፣ አብሮነትና የመከባበር ባሕል የእስልምና ሃይማኖት እሴቶች መሆናቸው ተደጋግሞ የተነገረ ነው። መረዳዳት፣ መከባበርና የታመመን መጠየቅ በእስልምና ኃይማኖት ሕግ የውዴታ ግዴታ ነው። አልፎ አልፎ በሚታዩ የአክራሪነት አስተሳሰቦች በሚፈጠሩ ግጭቶች አንዱ የሌላውን መመኘትና መቀማት በቅዱስ ቁርዓን ፍፁም የተከለከለና የሚወገዝ ነው፡፡
በባለፈው ዓመት የበዓሉ አከባበር ሥነሥርዓት ላይ የጉጂ ዞን ሸሪያ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሼክ ከድር አብዱረህማን “አክራሪነትና ጽንፈኝነት የኃይማኖቱን አስተምሮ የሚጥስ ተገቢ ያልሆነ ተግባር ነው” ማለታቸው የሚታወስ ነው። “በሃይማኖቱ የተፈቀደና የታዘዘው መቻቻል፣ መረዳዳት፣ አቅመ ደካሞችን መርዳትና አብሮነት ጥንትም የነበረ አሁንም ያለ ወደፊትም የሚኖር የተከበረና የተመረጠ ባሕል“ መሆኑንም ነው የገለፁት።
ይህ በሚመለከታቸው በቀጥታ ይገለፅ ከሚል ነው እንጂ ሁላችንም የምናውቀው ከመሆኑ አኳያ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን ከመግለፅ ያለፈ እዚህ የምንጨምረው ነገር አይኖርም። በትናንትናው እለት፣ እስልምና የሰላም፣ የፍቅርና የወዳጅነት እምነት እንደመሆኑ ምእመኑ በያሉበት በእነዚሁ እሴቶቻቸው ላይ ተመሥርተው ረመዳንን ያከበሩ ስለመሆናቸው በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።
ሁለቱ ታላላቅ ሃይማኖቶች፣ ክርስትና እና እስልምና የተቀደሱና የተባረኩ ወሮች የሚሏቸውን የፆም ወሮቻቸውን (‹‹ዓቢይ ፆም›› እና ‹‹ረመዳን››) በተመሳሳይ ጊዜ በፀሐይ ከመጋቢት 2 ቀን 2016 ዓ.ም (የጨረቃ መጋቢት 1 ቀን 2024/ ዓመተ 2024 የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የፀሐይና የጨረቃ ጥምር ቀመር ሲሆን፤ ከአውሮጳው ጋር አይገናኝም) እና በጨረቃ ከረመዳን 1 ቀን 1445 ዓመተ ሒጅራ ጀምሮ መያዛቸው ይታወቃል። ይህም በወቅቱ በብዙዎች አግራሞትን የጫረ ሲሆን፤ ለበርካታ የሁለቱም ሃይማኖቶች ምእመናን ውስጣዊ ደስታን የፈጠረ፤ ወንድማማችነትን፤ እንዲሁም የሺዎች ዘመናትን አብሮነትን ያንፀባረቀ ሆኖ ማለፉ ይታወቃል።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2016 ዓ.ም