እስልምና በአምስት መሠረቶች ላይ የቆመ ነው:: ፈጣሪን በብቸኝነት ማምለክ፤ ሶላትን መስገድ፤ ዘካ (ምፅዋት) ማውጣት፤ እና ሐጅ (ኃይማኖታዊ ጉዞ )መፈጸም የሚሉት ናቸው:: ሙስሊሞች ከእነዚህ አምስት የእስልምና መሠረቶች ውስጥ አንዱ የሆነውን የሮመዳን ፆምን ፆመው ጨርሰዋል:: የርኅራሔ፤ የደግነት፤ የመረዳዳት እና የፍቅር ወር የሆነውን የሮመዳንን የፆም ጊዜ ሲጨርሱ የኢድ በዓል ቦታውን ይረከባል:: ኢድ የሮመዳን ፆም የፍቺ በዓል ነው::፡
ኢድ የደስታ በዓል ነው:: ኢድ አልፈጥር የቅዱሱ ረመዳን ወር ፆም መፍቻ በዓል በመሆኑ በፆም ውስጥ ከምግብና ከመጠጥ እንዲሁም ከአላስፈላጊ ተግባራት ተቆጥቦ የቆየ ሰውነት ወደ ተለመደው የአመጋገብ ሥርዓት የሚመለስበትና ይህንኑም ከወዳጅ ዘመድ ጋር ማዕድ አብሮ በመቋደስ በደስታ የሚዋልበት ቀን ነው::
ሙስሊሞች ለአንድ ወር ያህል በትጋት ሲያከናውኑት የነበረውን የፆም ጊዜ ጨርሰው በዓላቸውን የሚያከብሩበት የደስታ ወቅት ነው:: በዚህ የደስታ በዓል ላይ ወዳጅ ከወዳጁ ይጠያየቃል፤ የተራቡና የታረዙ ወገኖች ይጎበኛሉ፤ ሁሉም ያለውን ያካፍላል፤ ደስታ በሁሉም ቤት ይገባል:: ዛሬ የሚከበረውም 1445ኛውን የኢድ በዓል እነዚህን እሴቶች ተላብሶ የሚከበር ነው::
በኢትዮጵያ ያለው የኢድ አከባበር ለየት የሚልባቸው እሴቶች አሉት:: ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የተለያዩ እምነቶችን በፀጋ የተቀበለችና የተለያዩ እምነት ተከታዮችም ተከባብረው የሚኖሩባት የተለየች ሀገር ነች:: ኢድን በመሳሰሉ የበዓል ወቅት በክርስትና በዓላት ጎረቤቶችን በመጥራት በዓሉን በጋራ ማሳለፍ የተለመደ ነው::
ይህ አንዱ ኢትዮጵያዊ እሴት ሲሆን ለዘመናትም ሲወርድ ሲዋረድ ዛሬ ላይ የደረሰ ድንቅ ኢትዮጵያዊ መገለጫችን ነው:: ይኸው ልዩ ኢትዮጵያዊ ዕሴቶች በዘንድሮው 1445ኛው የኢድ በዓል ላይ ተጠናክረው የሚታዩ ይሆናል::
ኢድ የስጦታ እና የመረዳዳት በዓል ነው:: የኢድ በዓል ሲከበር ሰዎች ስጦታ በመለዋወጥ ፍቅርና አክብሮታቸውን ይገልጻሉ:: እንኳን አደረሳችሁ ይባባላሉ:: ከዚሁ ጎን ለጎንም ያጡና የተቸገሩ ወገኖችን መርዳት አንዱ የበዓሉ ዕሴት ነው:: የእስልምና እምነት በኢድ ወቅት ድሆችን ከሚያስብበትና በዓሉንም በደስታ እንዲያሳልፉ በአማኞች ላይ ግዴታ ከጣለባቸው ትዕዛዞች አንዱ ላጡና ለተቸገሩ ወጎኖች የሚደረግ ድጋፍ ዘካተል ፊጥር ይባላል::
የእምነቱ ተከታዮች በጋራ የሰላት ሥነሥርዓት ወደ ሚያካሂዱበት ቦታ ከመሄዳቸው በፊት ለተቸገሩ ወገኖች የዘካተል ፊጥር እርዳታ ማድረግ ግዴታቸው ነው:: ይህ መሆኑ ደግሞ በችግር ላይ ያሉ ወገኖች የኢድን በዓል እንደሌሎች ወገኖቻቸው ሁሉ በደስታ እንዲያሳልፉ የሚያደርጋቸው ነው::
የኢድ እሴቶች ከሆኑት ውስጥ ሁሉም አማኝ በእኩል ስሜት በደስታ በዓሉን እንዲያሳልፍ ማስቻል ነው:: ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ይኸው የመረዳዳትና የመደጋገፍ ሁኔታ ከጥንት ጀምሮ የመጣ ሲሆን በዛሬው የኢድ በዓልም ይኸው ተጠናክሮ ይቀጥላል:: አሁን ባለው ሁኔታም ይህ የመረዳዳት ባሕል እየተጠናከረ መጥቷል::
ኢድ ከሃይማኖቱ ተከታዮች ባሻገርም እንደ ሀገርም ትልቅ ፋይዳ ያለው በዓል ነው:: መረዳዳትና መተዛዘን የሚጎላበትና ያለው ለሌለው የሚያካፍልበት በዓል በመሆኑ እንደሀገር ትልቅ ፋይዳ ያለው በዓል ነው:: በተለይም በአሁኑ ወቅት በፀጥታ ችግር ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉና የተሰደዱ በርካታ ወገኖች አሉ::
አሁን ያለንበት ወቅት በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ምክንያት የሰው እርዳታ የሚጠብቁና የኢትዮጵያውንን ድጋፍ የሚሹ በርካታ ዜጎች በየአካባቢው አሉ:: ለእነዚህ ወገኖች ቀድመን መድረስ ያለብን ደግሞ እኛው ነን:: ስለዚህም ኢድን በመሳሰሉ መረዳዳትና መደጋገፍ ጎልቶ በሚታይባቸው ቀናት እነዚህን ወገኖች ልናስባቸው ይገባል::
የኢድ በዓል አንዱ መገለጫ ሃብት ካላቸው ሰዎች የሚሰበሰብ ዘካ (ምፅዋት) ለድሆች የሚከፋፈልበት ወቅት ስለሆነ ይህንን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም እንደ ሀገር በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችን ጫና ማቃለል ይገባል:: በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ቤት ንብረታቸውን ትተው የተሰደዱና የተፈናቀሉ ወገኖችን እንዲሁም በድርቅ የተጎዱ ወገኖቹን በማገዝ ሃይማኖታዊ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2 ቀን 2016 ዓ.ም