አዲስ አበባ የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎች፤ ቆንስላዎችና ዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ መቀመጫ ናት፡፡ ታዲያ ይህን ሚና የያዘች ከተማ ብትሆንም እንደእድሜዋ ያልዘመነች፤ ለነዋሪዎች ምቹ ያልሆች ከተማ እየተባለች ትተቻለች፡፡ በቅርቡ ከተማዋን ለማዘመን፤ ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የከተማ አስተዳደሩ የኮሪደር ልማት በሚል ፕሮጀክት ነድፎ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡
የአዲስ አበባን ገጽታ አጉድፈው ከሚያሳዩ ስፍራዎች መካከል እንደ ‹‹ዶሮ ማነቂያ እሪ በከንቱ፤ ፒያሳና ሌሎች ወንዝ ዳርና የመንገድ ኮሪደሮች›› ይገኙበታል፡፡ ለመልሶ ግንባታና የኮሪደር ልማት ተነሺዎች ተመጣጣኝ የገንዘብና የመሬት ካሣ አቅርቦት ተዘጋጅቶ የማስተናገድ ሥራ እየተሠራ ነው ፡፡
ልማቱ መንግሥት አዲስ አበባን እንደስሟ ውብ አበባ ለማድረግ ቀደም ሲል የገባውን ቃል መሠረት አድርጎ የሚከናወን፤ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ግዙፍና ሰው ተኮር የልማት ሥራዎችን የሚያካትት ነው።
እስካሁን ከተሠሩት የልማት ሥራዎች መካከል ማዘጋጃ ቤት፣ መስቀል አደባባይ፣ ወንድማማችነትና አንድነት ፓርክ፣ ሳይንስ ሙዚየም አብርሆት ቤተ መጽሐፍት፣ ፑሽኪን አደባባይ፣ ጎተራ አቃቂ ቦሌ መንገድ ግንባታ የመሰሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
እነዚህ ግንባታዎች ለከተማዋ ልዩ ገጽታ ከማጎናጸፋቸው በተጨማሪ ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍ ያለ አስተዋጽዖ እያበረከቱ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ ያለው አዲስ አበባን ለቱሪዝም ምቹ እና ውብ የማድረግ የኮሪደር ልማትም የዚሁ ልማት ቀጣይ ምዕራፍ ነው፡፡
በመጀመሪያ ዙርም በዓድዋ ድል መታሰቢያ ፒያሳ- አራት ኪሎ-ቀበና-መገናኛ፤ አራት ኪሎ-ቦሌ አየር ማረፊያ-ቦሌ ድልድይ-መገናኛ፤ ከመገናኛ-አዲስ አፍሪካ ኮንቬንሽን ማዕከል ሲኤምሲ እንዲሁም ከሜክሲኮ- አፍሪካ ኅብረት-ሳር ቤት ወሎ ሰፈር 40 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኮሪደር ልማት ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡
የኮሪደር ልማቱ በከተማዋ ለነዋሪዎች ምቹ ያልሆኑ፣ ለአደጋና ለበሽታ የሚያጋልጡ አካባቢዎችን እንዲታደሱ የማድረግ የልማት ሥራን ማዕከል ያደረገ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ይደመጣል፡፡
ምንም እንኳ የልማቱን አስፈላጊነት ለኅብረተሰቡ በተገቢው መንገድ የማስገንዘብ ሥራ ውስንነት ቢኖረውም የልማት ተነሽ የኅብረተሰብ ክፍሎች መነሳታቸው የተሻለ መኖሪያ አካባቢ እንዳገኙ ይገልጻሉ፡፡
የተለያዩ ዘገባዎች እንደሚያመላክቱት፤ በኮሪደር ልማት ሥራው ለሁሉም ማኅበረሰብ ምቹ የጋራ መጠቀሚያ ከመፍጠር ያለፈ የሚቀየር የመዲናዋ የአካባቢ ስያሜ የለም። በኮሪደር ልማት ሥራውም ቅርሶችና መሠረተ ልማቶችን የመንከባከብ፣ የመጠበቅና የማደስ ሥራ በማከናወን በነበሩበት እንዲቀጥሉ ይደረጋል። ይህም ከዓለም አቀፍ ከተማ ጋር ተወዳዳሪ እንድትሆን ያደርጋታል፡፡
በቅርስነት የተለዩ እንደሲኒማ ኢትዮጵያ፣ ሀገር ፍቅር፣ ሸዋ ሆቴል፣ ሲቲ ኮንቬንሽን፣ የሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ ቤት፣ የቀድሞዎቹ ማዘጋጃና ፖስታ ቤት ታድሰው ባሉበት ይቀጥላሉ ተብሏል። ይህም አልፎ አልፎ በአንዳንድ ‹‹አክቲቪስቶች›› ዘንድ የሚነዛውን የሐሰተኛ መረጃ ያከሸፈ ነው፡፡
የልማት ተነሽዎች ባሉበት አካባቢ ባሉ ክፍለ ከተሞች የኮሪደር ልማት ክትትል ግብረ ኃይል እንዳለና በከተማ አስተዳደር ደረጃ ለአምስቱም የኮሪደር የልማት ተነሺዎች ቅሬታ ምላሽ የሚሰጥ ጽሕፈት ቤት መኖሩ ለሚነሱ ቅሬታዎች መልስ የሚሰጥ ነው፡፡
የነዋሪዎችን ማኅበራዊ ትስስር ለማስቀጠልም በድጎማ የሚቀርቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በማቅረብ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ዕድል መኖሩም አብሮነታቸውንን ለማስቀጠል ምቹ አጋጣሚ ነው፡፡ ይህም ልማቱ የማኅበረሰቡ ማኅበራዊ መስተጋብር እንዲቀጥልና በልማቱ ላይ የባለቤትነት ስሜት እንዲፈጥርባቸው የሚያደርግ ነው፡፡
የኮሪደር ልማቱ ካለው ስፋት አንፃር በፒያሳ፣ አራት ኪሎና ቦሌ መስመር የመንገድና የአረንጓዴ ልማት ሥራውን እስከ ግንቦት መጨረሻ ለማጠናቀቅ በትኩረት በመሠራት ላይ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና ድንገተኛ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን መረጃ እንደሚያመላክተው፤ የመዲናዋ የኮሪደር ልማት ከከተማ ልማትም ባለፈ ለእሳትና ድንገተኛ አደጋ ተጋላጭ የነበሩ ዜጎችን ሊታደግ የሚችል ነው፡፡
ከቤቶች ግንባታ ጥግግት፣ ከመንገዶች ጥበት፣ ከኤሌክትሪክ ማስተለለፊያ ገመዶች መደራረብ እና ከፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች መደፈን ጋር የሚከሰቱ አደጋዎችንም ለመከላከል እየተከናወነ ያለው የመንገድ ኮሪደር ልማት የሚኖረው አስተዋፅዖ ከፍ ያለ ነው።
የኮሪደር ልማቱ ቤቶች በፕላን እንዲገነቡ፣ መንገዶች እንዲሰፉ፣ ዘመናዊ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታና የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች በጥራት እንዲሠሩ የሚያደርግ ነው። በርካታ አካባቢዎችን ከእሳት ቃጠሎ፣ ከጎርፍ መጥለቅለቅ፣ ከትራፊክ መጨናነቅና ሌሎችም አደጋዎች የታደገ ሁነኛ መፍትሔ ይሆናል ተብሎም ይታመናል፡፡
የኮሪደር ልማቱ የአዲስ አበባ ከተማን ታላቅነትና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪ ከተማ ለማድረግ፣ ስሟን የሚመጥን ለማድረግ እና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የተጀመረ የመልሶ ግንባታ ሥራ ስኬታማ እንዲሆን የሁሉም አዎንታዊ ትብብር ወሳኝ ነው።
ግርማ ሞገስ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም