‹‹የአራዳ›› ከያኒዋ ድምጻዊት

የሁለት ሎጋ ጥንዶች ጥምረት የፈጠራት ናትና እሷም ቁመተ ሎጋ ናት፤ ድምጻዊት ዓለም ከበደ። ትውልዷ ከወደ ሰሜን ሸዋ፣ ሸኖ ነው። ቤተሰቦቿ መኖሪያቸውን ወደ አዲስ አበባ መቀየራቸውን ተከትሎ አብዛኛው የልጅነት ትዝታዋ ከዛ ይቀዳል። አዲስ አበባ፣ አማኑኤል፣ ቶታል አካባቢ የልጅነት ትውስታዋ የሙዚቃ ጅማሮዋ ነዋ። ሙዚቃ መስማት ትወዳለች፤ ያም ቢሆን በትምህርት ቤት ቆይታዋ ከሙዚቃ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላት አልነበረችም። ለሁሉም ነገር መጀመሪያ አለውና እሷም በሙዚቃ ሕይወቷ አንድ ብላ ልትጀምር ሠፈሯ የሚገኙትን የቀበሌ ኪነት አባላት ለመቀላቀል ወሰነች።

ወስናም አልቀረች፤ ሠፈሯ ወደሚገኘው የቀበሌ ኪነት ቡድን በማምራት የ“ልቀላቀላችሁ” ጥያቄ አቀረበች። በሚያሰሙት ሙዚቃ ተማርካ የቀበሌ ኪነት ቡድኑን ለመቀላቀል ብታመራም በአቅራቢያዋ የሚገኘው የቀበሌ ኪነት ኃላፊ ልጅነቷን አይተው “በዚህ እድሜሽ አንቺ መሄድ ያለብሽ ወደ ትምህርት ቤት ነው” በማለት ጥያቄዋን ሳይቀበሉ ቀሩ። ቀበሌ እምቢ ስትባል መድረሻዋን ወደ ከፍተኛ ለወጠች። በሠፈሯ ይገኝ ወደነበረው ከፍተኛ ስድስት በማምራት የኪነት ቡድኑን ለመቀላቀል ጥያቄዋን ሠነዘረች። መልሱ የከፋ ሆነ፤ እዚህ የሚገኙት የኪነት አስተባባሪዎች ወላጆቿን በቅርበት ያውቁ ኖሮ ሁለተኛ ትምህርት ትቼ እዚህ አልመጣም እንድትል ከክልከላውም ተጨማሪ ቅጣት ቀጥተው ሸኟት። ለዚህ ምክንያታቸውም “ሕፃን ነሽ፤ ትምህርትሽን ተከታተይ፤ ዘፈኑ የትም አይሄድብሽም፤ ትደርሽበታለሽ።” የሚል ነበር።

በአቅራቢያዋ የሚገኙ የቀበሌም ሆነ የከፍተኛ ኪነቶችን የመቀላቀል ጥረቷ ባይሳካም በሙዚቃ ተስፋ አልቆረጠችም። የሷ ከፍተኛ የተከለከለችውን የሙዚቃ እድል ለማግኘት ወደ ጎረቤት አካባቢዎች አማተረች። በዚህም “ከፍተኛ አምስት″ ወደ ተባለ ኪነት ቡድን አቀናች። የምትወዳት የአስቴር አወቀ “ወፌ ላላ” ዘፈን የወጣበት አካባቢ ነውና እሱን ዘፈን ዘፍና የኪነት ቡድኑን ተቀላቀለች። በቡድኑ ከሷ ቀደም ዋና የሴት ድምፃዊያን የነበሩ ቢሆንም፣ እሱን ቦታ ለመውሰድ ጊዜ አልፈጀባትም።

በኪነት ቡድኑ ከዓመት አለፍ ያለ ጊዜ ካገለገለች በኋላ በውድድር አልፋ ማዘጋጃ ቤትን የመቀላቀል እድል አገኘች። አስቴር አወቀ የምወዳት፣ በጣም የምሰማትና ዘፈን ስታወጣ ለመያዝ ጊዜ የማይፈጅብኝ ድምጻዊ ናት በማለት ትገልጻታለች። ማዘጋጃ ቤትን ብትቀላቀልም በመድረክ ሥራዋ አሁንም “ወፌ ላላ”ንና የተወሰኑ የአስቴር ሙዚቃዎችን በመጫወት እንደተገደበች ነው። ምንም እንኳን የምትጫወታቸው ዘፈኖች ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም ባህር አቋርጦ ሥራዋን ከማቅረብ አላገዳትም።

በመጀመሪያ የባህር ማዶ ጉዞዋ እስራኤል ሆነ። የማርታ “ዝማሙ፡”፣ የአስቴር አወቀ “ወፌላላ” እና አንድ ሌላ ሙዚቃን ይዛ ባህር ማዶ ተሻገረች። በወቅቱ ድምጻዊ ንዋይ ደበበ በሚያስተባብረው ስብስብ በመካተት እስራኤል ሀገር በሚዘጋጁ የሙዚቃ ኮንሰርቶች ሥራቸውን እንዲያቀርቡ ከታጩ ድምጻዊያን መሃል ሆነች። በስብስቡ ውስጥ አስተባባሪው ንዋይ ደበበን ጨምሮ፤ እውቁ የትግርኛ ቋንቋ ድምጻዊ ኪሮስ ዓለማየሁ፣ ድምጻዊ አረጋኸኝ ወራሽ፣ ድምጻዊ ሰማኸኝ በለው እና ድምጻዊት ቀኑብሽ አበበ ጋር በመሆን ወደ እስራኤል አቀናች።

አብረዋት የተጓዙት አብዛኞቹ የራሳቸው ዘፈን ያላቸው እውቅ ድምጻዊያን ነበሩና በመድረክ ላይ በርካታ ሙዚቃ ከማቅረባቸው ባሻገር ከሕዝቡ የሚያገኙት ፍቅር እኔስ እስከ መቼ በሰው ዘፈን የሚል ስሜት ፈጠረባት። የውጭውን እድል ስታገኝ ከማዘጋጃ ፈቃድ ሳታገኝ ወደ እስራኤል ማምራቷን ተከትሎ ከጉዞዋ ስትመለስ በምሽት ክበቦች ሙዚቃን መሥራት ጀመረች። ሆኖም በሙሉ ባንዶች ታጅቦ መዝፈን የለመደ ልቧ ሊረካ አልቻለም። በዚህ የተነሳ ራስ ቲያትር ባለሙያ ፈልጎ ማስታወቂያ ማውጣቱን ተከትሎ ትያትር ቤቱን ተቀላቀለች።

ራስ ትያትርን መቀላቀሏን ተከትሎ የባህልም ሆነ ዘመናዊ ዘፈኖችን የመጫወት እድል አገኘች። ከዚህ በተጫማሪ በየሳምንቱ በትያትር ቤቱ ይቀርብ በነበረው “ትእይንተ ጥበባት” በተሰኘው መሰናዶ አዳዲስ ሙዚቃዎችን ማቅረብ ጀመረች። በዚህ መድረክ ላይ የባህሉንም ሆነ ዘመናዊ ዘፈኑን በብቃት ማቅረብ በመቻሏ ዓለም የምትሰኝ ድምጻዊ መኖሯን ለማሳወቅ ምክንያት ሆናት። በዚህ የተነሳ “ማህሌት” የተሰኘ ሙዚቃ ቤት የድሮ ዘፈኖችን ሰብስቦ በኮሌክሽን ለማውጣት ሲያስብ ከታጩት መሃል አንዷ ሆነች። እንደልቤ ማንደፍሮ፣ ባህሩ ቃኘው፣ ከተማ መኮንንና እሷ በጋራ ሆነው የሰሩት አልበም ወጣ። አልበሙ ምንም እንኳን ቆየት ያሉ ዘፈኖችን የያዘ ቢሆንም ዓለምን ከአድማጭ ጋር በማስተዋወቅ ረገድ ድርሻው የጎላ ነበር።

እሷ ከመስፍን ጋር “ሸሞንሟናዬ”ን አንድ የሜሪ አርምዴን “ሞላ ሀገሩ ሰማ” የተሰኘ ሙዚቃ በሷ በድጋሚ ከተዜሙና በአልበሙ ከተካተቱ ሥራዎች መሃል ይገኙበታል። በመቀጠል “አተረማመሰው” ስትል የሰየመችውን አልበም አወጣች። ከዚህ አልበም ውስጥ አተረማመሰው የተሰኘው ዘፈን በምሽት ቤቶች ከፍተኛ ተቀባይነትን ሲያገኝ፣ “በለው በለው” በሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን በብዛት የተሰማ ሥራዋ ነው።

የራሷን ሥራ ማውጣቷን ተከትሎ በየመድረኩ ፈላጊዋ በዛ፤ ሥራዋን ባቀረበችበት መድረክ ሁሉ እሷን የሚሉ አድናቂዎቿ ቁጥር እያሸቀበ ሄደ። ይህን ተከትሎ ከሀገር ውጭም አብረሽን ሥሪ የሚሉ ጥሪዎች በረከቱ። እሷም ለነዚህ ጥያቄዎች ቀና መልስ በመስጠት በመጀመሪያ ጅቡቲ፤ ከጅቡቲ መልስ ወደ ኬንያ በማቅናት የሙዚቃ ሥራዋን አቅርባ ተመለሰች።ወደ ካናዳም ተመሳሳይ የአብረሽን ሥሪ ጥያቄ መምጣቱን ተከትሎ ቀጣዩ መዳረሻዋ ካናዳ ሆነች።

የካናዳ ሥራዋ ሲጠናቀቅ ወደ ጎረቤት አሜሪካ አቅንታ ሥራዋን የምታቀርብበት እድል ተመቻቸ። ከካናዳ ወደ አሜሪካ ስታቀና ሥራዋን አቅርባ ለመመለስ ቢሆንም ለሥራ ያቀናችባት አሜሪካም እስካሁን መኖሪያዋ ሆና ቀርታለች።

መኖሪያዋን አሜሪካ ካደረገች በኋላ “አራዳ” ስትል የሰየመችውን ሦስተኛ አልበም ለአድማጭ አድርሳለች። አልበሙ ላይ የሚገኘው “አራዳ” የተሰኘ ዘፈን በወቅቱ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥንና በአልበሙ አከፋፋይ አማካኝነት እሷ ወደ ሀገር ቤት ባትመጣም የቀድሞ ቪዲዮቿን ከሀገር ውስጥ የቪዲዮ ምስሎች ጋር በመቀላቀል የቪዲዮ ክሊፕ ተሰርቶላታል።

ይህ ዘፈኗ ለአዲስ አበባ ማስታወሻ ይሆን ዘንድ በከተማው የሚገኙ በርካታ ሠፈሮች የተጠቀሱበት ተወዳጅ ሥራዋ ነው። ሆኖም እሷ ከተጫወተችው በኋላ ድምጻዊ ጎሳዬ ተስፋዬ ዘፈኑን ደግሞ የተጫወተው በመሆኑ የተወሰኑ አካላት የእሱ ሥራ ቢመስላቸውም እውነታው ግን ሙዚቃውን ዓለም ከበደ ቀድማ የሠራችው መሆኑ ነው። የዘፈኑን ሃሳብ ተመስገን ተካ ሲያመጣው ዓለምፀሐይ ወዳጆ ገጣሚነት፤ በታመነ መኮንን የዜማ ደራሲነትና በዓለም ድምጽ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአድማጭ ጆሮ የደረሰ ተወዳጅ ሥራ ነው።

አራዳ

እስኪ ላወድሰው

እኔው ላሞጋግሰው

እየደጋገመኝ

ናፈቀኝ አንድ ሰው

ሳሳሁ ኧረ ሳሳሁልህ

እኔስ ገባሁ እዳ

በቆንጆ ልጅ ፍቅር

ሸግዬ የአራዳ (2)

ዛሬም ና ነገም ና

ቢያሻህ ከነገ ወዲያ

እርም ነው ማፍቀሩ

ገላ ከኛ ወዲያ (2)

ብጠራህ አትሰማኝ

ሀገርህ አቀናህ (2)

ፈጥነህ በባቡሩ

በሰጋሩ ናና

ቶሎ ናና ናና

አራዳ ስሙ ሲነሳ

አብረን ፒያሳ ፒያሳ

እንዳያድር ለፊያቱ

ደውልልኝ ከመርካቶ…

ቦሌ ነህ ወይ ሳሪስ ቄራ

ልምጣ በአየር

እንደ አሞራ…

በቅሎ ቤት ነህ

ጌጃ ጎፋ

ምነው ባይህ

ልቤ ጠፋ

ሽሮ ሜዳ

ወይ እንጦጦ

መቼ ቀረ

ልቤ ቆርጦ

የሁለት ወንድ ልጆች እናት የሆነችው ድምጻዊቷ በምትኖርበት አሜሪካ፣ ቨርጂኒያ በሚገኙ የሀበሻ ምሽት ክበቦች ሙዚቃን ብታቀርብም በርካታ የሀገራችን የሙዚቃ አድማጮች የሚገኙት በኢትዮጵያ ነውና ከበርካታ አድማጮቿ ተራርቃ ቆይታለች። ይሄንንም ለመካስ ይመስላል ከበርካታ ዓመታት በኋላና 11 ዓመታትን እንደፈጀ የተገለጸው አራተኛ አልበሟን “አቀላለጠው” በሚል ርእስ ለአድማጭ አድርሳለች። አልበሙ በምትኖርበት አሜሪካ በርካታ የሙያ ባልደረቦቿና አድናቂዎቿ በተገኙበት የ“አልበም ሪሊዝ” ፓርቲ የተደረገለት ሲሆን፣ በአድማጮች ዘንድም ጥሩ ተቀባይነትን አግኝቷል። በሀገር ውስጥ ግን ለረዥም ጊዜ ከአድማጭ ተራርቃ በመቆየቷ ሊሆን ይችላል የተለፋበትን ያህል አልተሰማም።

አቀላለጠው

የማምንህ (3)

ወዴት ነህ

ከእንግዲህ ሸብ አድርገው

ድጉን ከወገብህ

ከእንግዲህ አይክፋህ

ዝናር ካጠገብህ

ሸማ ጣል ይሉሃል

ሸማ ጥለህ ውሰድ

አለሁ አትልም ወይ

ጊዜን የመውደድ

ደሞ ደሞ ደሞ ደሞ

ያሸንፋል

ገላህ ቀድሞ

ሸበላ አካልህ

የተመረጠው

ደሞ አንጀቴን አቀላለጠው

አቀላለጠው…

ካንተ አይለየኝ ብዬ

ምያለሁ ከገዳም

አንድም እንደወንድም

አንድም እንደወዳጅ

አምንሃለሁ እንጂ

ምነው አላምንህ

ትረታ የለም ወይ

ስለኔ ሆነህ

የድምጻዊቷ የመጨረሻ ሁለት አልበሞች መኖሪያዋን በሀገረ አሜሪካ ካደረገች በኋላ የተሰሩ ናቸው። የመጨረሻ አልበሟ “አተረማመሰው” 13 ዘፈኖችን የያዘ ሲሆን፤ አልበሙ ከሙዚቃ ሪትም፣ እንዲሁም የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን እንዲያነሱ በማሰብ ጊዜ ሰጥታ መሥራቷን በአንድ ወቅት ከአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ጋር በነበራት ቆይታ ገልጻለች። ዓለም ከድምጻዊያን ለአስቴር አወቀ የተለየ ቦታ ያላት ሲሆን፤ ከአስቴር በተጨማሪ ብዙነሽ በቀለ፣ ሐመልማል አባተ፣ ሕብስት ጥሩነህ የምትወዳቸው ድምጻዊያን እንደሆኑ ትናገራለች። ያም ቢሆን የወጣ ካሴት እንደማያልፋትና ሙዚቃ አዳማጭና የበርካታ ድምጻዊያን አድናቂ መሆኗን አትሸሽግም።

ቤዛ እሸቱ

አዲስ ዘመን  መጋቢት 29 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You