
-በቀን ሦስት ሚሊዮን ሊትር የሚጠጋ ነዳጅ ወደ ሀገር እየገባ ነው
አዲስ አበባ፡– በቅርቡ አጋጥሞ የነበረው የነዳጅ እጥረት በአሁኑ ጊዜ ሙሉ በሙሉ መቅረፍ ተችሏል ሲል የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት አስታወቀ፡፡ በቀን ሦስት ሚሊዮን ሊትር የሚጠጋ ነዳጅ ወደ ሀገር እየገባ መሆኑም ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ከፍተኛ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ዓለማየሁ ፀጋዬ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የነዳጅ እጥረቱ አጋጥሞ የነበረው በጅቡቲ ጥሎ በነበረው ከባድ ዝናብ ምክንያት መንገዶች በመዘጋጋታቸው ነው፡፡ በዚህ ሳቢያም ነዳጅ የሚጭኑ ከባድ ቦቴዎች ወደ ሀገር መግባትም ሆነ መውጣት አልቻሉም ፡፡
መንገዱ ከዚህ ቀደምም ችግር የነበረበት ነው ያሉት ባለሙያው፤ ከሹፌሮችም በተደጋጋሚ ስሞታ የሚቀርብበት ነው ሲሉ ተናግረዋል ፡፡
አቶ ዓለማየሁ፤ ድርጅቱ ያጋጠመውን የነዳጅ እጥረት ለመቅረፍ ነዳጅ የጫኑ ተሽከርካሪዎች በድሬዳዋ በኩል እንዲገቡ መደረጉን ገልጸው፤ በዚህም አጋጥሞ የነበረውን ችግር ሙሉ በሙሉ መቅረፍ መቻሉን አንስተዋል፡፡
ችግሩ ከማጋጠሙ በፊት በቀን በአማካኝ ከ250 እስከ 300 የሚሆኑ ነዳጅ የሚጭኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ ያሉት አቶ ዓለማየሁ፤ አሁን ላይ መንገዱ የተከፈተ በመሆኑ እነዚህ ነዳጅ የጫኑ ከባድ ተሸካርካሪዎች ወደ ሀገር መግባት ጀምረዋል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ እንደዚህ ቀደሙ በቀን እስከ ስምንት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሊትር ናፍጣ እንዲሁም እስከ ሁለት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ሊትር ቤንዚን የሚደርስ በየቀኑ ወደ ኢትዮጵያ እየገባ ይገኛል ሲሉም አብራርተዋል ፡፡
እንደ አቶ ዓለማየሁ ገለጻ፤ ችግሩ በተከሰተበት ወቅትም ቢሆን ከመጠባበቂያ የነዳጅ ማከማቻ ወጪ ተደርጎ ለነዳጅ ማደያዎች እንዲደርስ ተደርጓል፡፡ በዚህም አሳሳቢ የሚባል የነዳጅ እጥረት አላጋጠመም ነበር፡፡ ረጅም የነዳጅ ሰልፍ እንዲኖር ያደረገው ኅብረተሰቡ ላይ የነዳጅ እጥረት አለ የሚል ስጋት መሆኑን ጠቁመዋል ፡፡
በቀጣይ እንዲህ አይነት ችግሮች ሲያጋጥሙ ቶሎ ምላሽ ለመስጠት ድርጅቱ በቂ መጠባበቂያ ነዳጅ በመያዝ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ይሠራል ያሉት አቶ ዓለማየሁ፤ ወደፊት ከፍ ያለ በጀት በመመደብ ነዳጅ በባቡር የማጓጓዝ ሥራ ቢጀመር ለዚህ አይነት ችግር አይነተኛ መፍትሔ መሆኑን ጠቁመዋል ፡፡
ዳግማዊት አበበ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 28 ቀን 2016 ዓ.ም