በተለምዶ የአንድ ሰው ጥፍር ስለ ስራው ብዙ ይናገራል ይባላል። ነገር ግን የጥፍር ቀለም ከስራም አልፎ ስለ አንድ ሰው ልምድ፣ የጭንቀት መጠን እና ጤንነቱ ጭምር እንደሚገልጽ ደግሞ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ነጭ እና ጥቁር ጥፍር
ጥፍር ነጭ ቀለም ይዞ ወደ ጫፍ በኩል ጠቆር ሲል (Terry’s nail) ይባላል። ይህ ምልክት የከፋ የጤና ጉዳት እንዳለ ባያመላክትም አልፎ አልፎ ግን የከባድ ጉበት ህመም ምልክት ሊሆን ይችላል።
ነጭ ጥፍር
ከመወለድ ጀምሮ የነበረ የጥፍር ንጣት አብዛኛውን ግዜ ምንም አይነት የጤና ችግር አያመላክትም። ቆይቶ የተከሰተ ከሆነ ግን ከባድ የሚባል የጉበት፣ የኩላሊትና የልብ ህመም እንዲሁም የደም ካንሰር ምልክት ሊሆን ይችላል።
ቢጫ ጥፍር
የቢጫ ጥፍር በሽታ ከባድ የሚባል የሳንባ ህመም ወይም «ሊምፊዴማ» ተብሎ የሚጠራ በሽታ ምልክት ሊሆን ይችላል።ይህ የጤና ችግር እጅ እና እግር ላይ እብጠት የሚያሳይ ምልክት ሊሆን ይችላል። በዚህ በሽታ ምክንያትም በታካሚዎቹ አጠቃላይ ጣቶች ላይ ጥፍር ወደ ቢጫነት የመቀየር ሁኔታ ይስተዋላል።
ሰማያዊ ጥፍር
ከጥፍር በታች የሚገኘው የሴል ክምችት ወደ ሰማያዊ ቀለም ሲለወጥ የህመም ምልክት መሆኑን ያመላክታል።። ይህ ሁኔታም በደም ውስጥ የሚገኝ የኦክስጅን እጥረት ስለመኖሩ የሚጠቁም ምልክት ነው።
በጥፍር ላይ የሚወጣ መስመር
አብዛኛውን ጊዜ በጥፍር ላይ የሚወጣ መስመር የጣት ቆዳ በሽታ ምልክት ነው።
የጥፍር መሰበር ወይም መሰንጠቅ
የጥፍር ጥንካሬ አለመኖር አብዛኛውን ግዜ እድሜያቸው በገፉ ሰዎች ላይ የሚታይና የተለመደ ምልክት ነው።
ጥፍር ከቆዳ የሚገናኝበት ቦታ ላይ የሚከሰት እብጠት
ቆዳ ላይ በጥፍር ዙሪያ የሚከሰት እብጠት በጉዳት ምክንያት የሚያጋጥም ሊሆን ይችላል። ከዚህ በዘለለም አንዳንድ በሽታዎች በዚህ የጣት ክፍል ላይ እብጠት እንዲከሰት የማድረግ አቅም ይኖራቸዋል።ይህ አጋጣሚ ሲከሰት ደግሞ ጣቶች በወደውስጥ እንዲሰረጎዱና እንዲጎዱ ጭምር ያደርጋሉ።
ከጥፍር ስር የሚፈጠር ጥቁር መስመር
ይህ ምልክት ከጥፍር ስር ጀምሮ እስከ ጫፍ የሚደርስ ጠቆር ያለ መስመር ሲሆን ከጥፍር ስር ከየት በኩል እንደሚጀምርም ለማወቅ ይቸግራል።መስመሩ የሚፈጠ ርበትን ምክንያትም በቅጡ ማወቅ ይከብዳል። ይህን ለማረጋገጥና የካንሰር ይዘት እንዳለው ለማጣራትም የህክምና ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል።
የተበላና በእጅጉ የተጎዳ ጥፍር
ይህ ሁኔታ በጥፍር መብላት የሚፈጠር ጉዳት ሲሆን ሁኔታውን ለመቀየር የልምድ ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል።
አብዛኛውን ግዜ ጥፍር ላይ የሚከሰቱ ለውጦች ለጤና የማያሰጉ ሊሆኑ ይችላሉ። አንዳንዴ ግን ስር የሰደደ በሽታ ምልክት የሚሆኑበት አጋጣሚ የሰፋ ነው።ይህ መሆኑ ከታወቀም በወቅቱ ምርመራ ማካሄድ ተገቢና የግድ ይሆናል። የጥፍር ለውጥን ለማስተካከል ረጅም ግዜና ሰፊ ትእግስት ይጠይቃል። ምንጭ:- ጤነኛ ዶት ኮም
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 8/2011