
ሀዋሳ፡ የሲዳማ ክልል የቤተሰብ ብልጽግናን ለማረጋገጥ 7 ኢንሼቲቭና 67 ፓኬጆችን የያዘ 767 የተሰኘ ፓኬጅ ቀርጾ ወደ ትግበራ ሊገባ መሆኑን አስታውቋል።
በክልሉ የፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ ዳዊት ሀዬሶ(ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፣ 767 የተሰኘው ኢንሼቲቭና ፓኬጅ እርሻን፣ የእንስሳት ሀብት ልማት፣ ቱሪዝም፣ ትምህርት እና ስልጠና፣ ኢንዱስትሪ፣ ንፅህናን እንዲሁም የማህበረሰብና አካባቢ ደህንነትን ያካተተና በውስጡም 67 ፓኬጆችን አቅፎ የያዘ ነው።ኢንሼቲቭና ፓኬጁ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የሚተገበር ሲሆን፣ትግበራው በጥናት በተለየው መሰረት እንደ የአካባቢው ተፈጥሯዊ ባህርይ ሊለያይ ይችላል።
የክልሉ መንግሥት የሕዝቡን የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስና የጋራ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ላለፉት ሶስት ዓመታት የተለያዩ የልማት ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
የሲዳማ ክልል በክልልነት ከተደራጀ ጀምሮ የሕዝቡን ፍላጎት መነሻ ባደረገ መልኩ የጋራ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የተለያዩ ስራዎች ሲሰራ መቆየቱንም አውስተው፤በመንገድ፣ በግብርና ፣ በንጹህ መጠጥ ውሃ፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በመልካም አስተዳደር እና በተሻሻለ እንስሳት ዙሪያ ተጠቃሽ ሥራ መሠራቱንም ኃላፊው አንስተዋል። በዚህም በክልሉ 9 ነጥብ 8 በመቶ እድገት ማስመዝገብ መቻሉን አስታውቀዋል።
የጋራ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የተሄደበት ርቀት የሚበረታታ ቢሆንም፣ በጋራ ብልጽግና ብቻ የሚፈለገውን የቤተሰብ ብልጽግናን በተፈለገው ፍጥነት ማረጋገጥ አይቻልም ያሉት ዳዊት (ዶ/ር) ፤የቤተሰብ ብልጽግናን በተሻለ ደረጃ ማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎች በጥናት ተለይተው ወደ ትግበራ ሊገባ እንደሆነም አመልክተዋል።
ሆላንድ፣ ቻይና፣ አሜሪካ፣ ጀርመንና ጃፓን ልምድ የተወሰደባቸው ሀገራት እነዚህን ኢንሼቲቭና ፓኬጅ በመተግበር ድህነትን ታሪክ ያደረጉ መሆናቸውንም ኃላፊው በማሳያነት ጠቅሰዋል።
እንደ ዳዊት(ዶ/ር) ገለጻ፣ ኢንሼቲቭና ፓኬጆቹ በዚህ ደረጃ ተቀርጸው ከመቅረባቸው በፊት ብዙ እየተመከረበት ቆይቷል። በተያዘው ዓመት መጨረሻ ወደ ትግበራ የሚገቡ ይሆናል።
ኢንሼቲቭንና ፓኬጅን በአግባቡ ስራ ላይ ማዋል ከቻልን የምንፈልገውን የቤተሰብ ብልጽግና እውን የምናደርግበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም ያሉት የቢሮ ኃላፊው፤ ለስኬታማነቱም መንግሥትና ፓርቲው በቁርጠኝነት እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
የኢንሼቲቭና ፓኬጁ ፋይዳ አስመልክቶ ከክልል ማዕከል አንስቶ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ላሉ ለመንግሥት የስራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ መሠራቱንም ነው ዳዊት (ዶ/ር) የተናገሩት። በቀጣይም ለአርሶ አደሩና ለአርብቶ አደሩ ግንዛቤ የማስጨበጡ ስራ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።
የክልሉ መንግሥት ለዚህ ኢንሼቲቭና ፓኬጆች ተግባራዊነት አስፈላጊውን ሁሉ አቅርቦት ለማቅረብ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ሕዝቡም ኢንሼቲቭና ፓኬጁ መንግሥት የማህበረሰቡን ኑሮ እንዲለወጥ አስቦ ያዘጋጀው መሆኑን በመገንዘብ ለተግባራዊነቱ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
አዱሱ አዶላ
አዲስ ዘመን መጋቢት 26 ቀን 2016 ዓ.ም