ምክር ቤቱ እንደ ዓባይ ሁሉ ለሀገራዊ አጀንዳዎች ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ

አዲስ አበባ፡– እንደ ዓባይ ፕሮጀክት ሁሉ ለትላልቅ ሀገራዊ አጀንዳዎች ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ።

የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ደስታ ዲንቃ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የዓባይ ግድብ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የተሳተፉበት የጋራ ፕሮጀክት ነው። ግድቡ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ ብዙ ችግሮችን ሊቀርፍ የሚችል በመሆኑ እስከዛሬ ድረስ ሁሉም ዜጎች በመረባረብ አሻራቸውን እያሳረፉበት ይገኛሉ ብለዋል።

የጋራ ምክር ቤቱም ከግድቡ ግንባታ ጀምሮ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው፤ እንደ ዓባይ ያሉ ዘመን ተሻጋሪ የልማት ሥራዎች ላይ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል።

ግድቡ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚታይ የልማት ጉዳይ በመሆኑ፤ ከፖለቲካ ውጪ በሆነ እይታ ውስጥ ያለና የሀገር ሀብት ነው ብለዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የግድቡን ግንባታ እየደገፈ ያለውም የጋራ ሀብታችን መሆኑን በመገንዘብ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ፍላጎታችን በኢትዮጵያ ውስጥ ልማት መጥቶ መላው ኢትዮጵያዊያን የልማቱ ተጋሪ እንዲሆኑ ነው ያሉት ሰብሳቢው፤ ልማት በማምጣት ሂደት ውስጥም በጋራ መረባረብና የልማቱ ተጠቃሚ ለመሆን ከፍተኛ ፍላጎትና ጥረት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በአብዛኛው 99 በመቶ በሚባል ደረጃ የግድቡን ፕሮጀክት እንደሚደግፉ አመላክተዋል።

በተፎካካሪ ጎራ ያሉት ቡድኖች ትላልቅ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የመቻልና የመታገስ አዝማሚያ እንደሚያሳዩ ጠቁመው፤ ይህም በተለይ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ከተጀመረበት ወዲህ በስፋት እየተንጸባረቀ መሆኑን አንስተዋል።

እንደ ሰብሳቢው ገለጻ፤ ሀገራዊ በሆኑ የልማትና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ብዙ ተቃውሞ አይታይም።

በጋራ ምክር ቤቱ በኩል ሲሰባሰቡም የሚያበረታታ ሁኔታ አለው ብለዋል።

ምክር ቤቱ በዓባይ ግድብና በወደብ ጉዳይ ድጋፉን እየሰጠ መሆኑን ጠቁመው፤ ትልልቅ የሚባሉና ለትውልድ ተሻጋሪ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በዘለቄታዊነት ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።

የፖለቲካ ምህዳሩ ሰፍቶ የፖለቲካ ኃይሎች ተመሳሳይና እኩል የመወዳደሪያ ሜዳ የሚያገኙበትን ዕድል በማስፋት በማህበራዊም ሆነ በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች የበለጠ ውጤታማ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።

ሰብሳቢው አክለውም፤ የጋራ ምክር ቤቱ የልዑካን ቡድን በግድቡ ባደረገው ምልከታ ሕይወታቸውን የሚገብሩና ሌት ከቀን የሚሰሩ ሰራተኞች መኖራቸውን ያረጋገጠ መሆኑን አስረድተዋል። ይህ የሚደነቅና በኢትዮጵያ አዲስ የሥራ ባህልን የፈጠረ ነው ብለዋል።

በዚህም ዜጎች የግል ኑሯቸውን ለማሸነፍ ከሚያሳዩት ጥረት ባሻገር በሀገር ደረጃ ለሚሰሩ ሥራዎች በርካታ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ዓባይ የሀገር ንብረትና ልማት እንዲሁም ከትውልድ ትውልድ ተሻጋሪ በመሆኑ የጋራ ምክር ቤቱ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለመተባበር ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል። ኢትዮጵያዊያን የጀመሩትን ለመጨረስ እስከመጨረሻው ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን መጋቢት 25ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You