በአማራ ክልል በሰባት ወራት ለዓባይ ግድብ ከ 32 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል

አዲስ አበባ፡- በአማራ ክልል ለዓባይ ግድብ ግንባታ በሰባት ወር ውስጥ ከ32 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን የክልሉ የህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የጽህፈት ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ተናኘ አበበ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ እና ንግድ ባንክ በተገኘው መረጃ ከክልሉ ነዋሪዎች በሰባት ወር ውስጥ ከ32 ሚሊዮን 329ሺ ብር በላይ በቦንድ ግዢ ተሰብስቧል።

ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ በተያዘው በጀት ዓመት ከቀድሞ ዓመታት በተለየ መልኩ ዕቅዱን ከፍ በማድረግ 70 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ አቅዶ እንደነበር አስታውሰው፤ ሆኖም በክልሉ በነበረው ችግር የታሰበውን ያህል መስራት እንዳልተቻለ ተናግረዋል።

ግድቡ የተጀመረበትን 13ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግም 40 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ልዩ እቅድ ታቅዶ እንቅስቃሴ ተጀምሯል ያሉት አቶ ተናኜ፣ ከክልሉ ወጣቶች እና ሴቶች አደረጃጀቶች ጋር በጋራ በመሆን እቅዱን ለማሳካት ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም አመላክተዋል።

የክልሉ ነዋሪዎች ግድቡ ከተጀመረ ጀምሮ ተሳትፏቸው መቀጠሉን የተናገሩት ኃላፊው፤ ግድቡ ከተጀመረ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የቦንድ ግዢ ያላቋረጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸውን ተናግረዋል። የመንግሥት ሠራተኛ የሆነው በተከታታይ ያለማቋረጥ ቦንድ የሚገዙ እንዲሁም በጡረታ ላይ ሆነው ቦንድ መግዛታቸውን ያላቋረጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዳሉም አመላክተዋል።

የመንግሥት ሠራተኛው፣ ጡረተኛው፣ ነጋዴው፣ ተማሪው እንዲሁም ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ለግድቡ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረው፤ ድጋፉ ከገንዘብ በተጨማሪ በርካታ ሰዎች 8100 ላይ A ብለው በስልክ መልዕክት በመላክ አስተዋጿቸውን እያበረከቱ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

የዓባይ ግድብ ሲጀመርም ትልቅ የሕዝብ ድጋፍ ያለው በመሆኑ ፈተናዎች ቢያጋጥሙም ግድቡን “ሳንጨርሰው አናቆምም” የሚል ቁርጠኝነት ተይዞ እንደተጀመረ ያስታወሱት አቶ ተናኜ፤ አሁንም ሲጀመር የነበረው ስሜት እንዲቀጥልና ኅብረተሰቡ ግድቡ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ድጋፉን እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፈዋል።

ለዓባይ ግድብ ቦንድ የሚገዛ ሰው በግድቡ ላይ አሻራውን ከማሳረፉ ባሻገር ገንዘቡን ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ እንደፍላጎቱ ከነወለዱ ጭምር ማግኘት እንደሚችል ጠቁመው፤ ሁሉም ኅብረተሰብ የዓባይ ግድብን ቦንድ በመግዛት እንዲሁም ተንቀሳቃሽ ስልክ በመጠቀም 8100 ላይ A ብሎ በመላክ በግድቡ ላይ አሻራውን እንዲያሳርፍ ጠይቀዋል።

መዓዛ ማሞ

አዲስ ዘመን መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You