ግብጽ የዓባይ ግድብ መጠናቀቅ ለተፋሰሱ ሀገራት ታሪክ የሚቀይር ይሆናል የሚል ፍርሃት አላት

አዲስ አበባ፡– ግብጽ የዓባይ ግድብ መጠናቀቅ ለተፋሰሱ ሀገራት ታሪክ የሚቀይር ይሆናል የሚል ፍርሃት አላት ሲሉ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ሀብት ምህንድስና ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር መኮንን አያና አስታወቁ።

በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ሀብት ምህንድስና ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር መኮንን አያና ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ግብጾች የሚያስፈራቸው ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የግድብ ግንባታ ካጠናቀቀች ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የኢትዮጵያን መንገድ ይከተላሉ፤ የግብጽ የበላይነትም አይኖርም የሚል ነው። በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያ በዓድዋ ላይ የነበረው ስኬት በዓባይ ግድብ ከተደገመ ለናይል ተፋሰስ ሀገራት ታሪክ የሚቀይር ይሆናል የሚል ትልቅ ፍርሃት አለባቸው።

የዓባይ ግድብ የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠ 13 ዓመት ሆኖታል ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ ግድቡ ብዙ ፈተናዎችን አልፏል። ይሁን እንጂ ባለፉት 13 ዓመታት ውስጥ የመጣበት ሂደት ውጤታማና በስኬት የተሞላ ነው። ካሉ ፈተናዎች አንጻር ለመጠናቀቅ መቃረቡ አስደሳች ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በዓድዋ ድል አፍሪካን አንድ እንዳደረገችና ከጭቆና ነጻ እንዳወጣች ሁሉ በግድብ ግንባታ ውጤታማ በመሆን ለአፍሪካ ሀገራት አርዓያ ትሆናለች የሚል ፍርሃት በመኖሩ ለማስተጓጎል ሙከራ መኖሩን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከዓባይ ግድብ ግንባታ ጋር በተገናኘ ስለ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ያገኘችው ትምህርት ብዙ ነው ያሉት ፕሮፌሰር መኮንን፤ ወደፊት በዓባይ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች በሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ መነሳታቸው አይቀርም ነው ያሉት ።

ኢትዮጵያም ባለፉት 13 ዓመታት በዓባይ ግድብ የዲፕሎማሲ የበላይነት ያረጋገጠችበት በመሆኑ ስኬታማ ጉዞ መሆኑን ገልጸዋል።

የዓባይ ግድብ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለ ጊዜ አንስቶ በኢትዮጵያ ላይ በርካታ ፈተናዎች ነበሩ የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ ግድቡ ሲጀመር ደሃ ናቸው፤ አይሰሩትም የሚል እምነት ነበር። ነገር ግን ግንባታው እውን ሲሆን ብዙ ጫናዎች መደረጋቸውን አውስተዋል።

ግድቡ በአሁኑ ጊዜ በተሻለ ፍጥነትና ጥራት ወደፊት እየሄደ ነው። ባለፈው ዓመት አራተኛ ዙር ሙሌት ተሞልቷል፤ ከሁለት ወር በኋላ አምስተኛ ዙር እንደሚሞላ የገለጹት ምሁሩ፤ በዚህም ከ50 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በላይ ውሃ የሚይዝ ይሆናል። የመጨረሻውን 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ለመያዝ የሚቀረው አንድ ዙር ሙሌት ብቻ ነው። ከሰባት ወር በኋላ የሲቪል ስራው እንደሚጠናቀቅም ገልጸዋል።

በቀጣይ ተርባይኖችን ወደ ሥራ በማስገባትና ኃይል በማመንጨት ለውጭ ገበያ የማቅረብ ሥራ በስፋት እንደሚሰራ ጠቁመው፤ ይህም የኢትዮጵያን እድገት የሚያፋጥን እንደሚሆን ተመራማሪው ገልጸዋል።

እንደ ተመራማሪው ገለጻ፤ ግብጽ የዓባይ ግድብ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ዓመት ጀምሮ በየዓመቱ የማስፈራሪያ መግለጫ ማውጣቷ የተለመደ ነው። መሰል መግለጫዎች ከጥንት ጀምሮና የተለመዱ ናቸው።

‹‹የዓባይ ወንዝ ከሌለ ግብጽ የለችም። የቀድሞ መሪዎቻቸው ጭምር ዓባይን የተቆጣጠረ ግብጽን ተቆጣጠረ የሚል አስተሳሰብ አላቸው፤ በመሆኑም ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝን መጠቀም ከጀመረች ግብጽን መቆጣጠር ነው›› ብለው የሚያምኑና በሕዝባቸው ላይ ይህን አስተሳሰብ ማስረጻቸውን አስታውቀዋል።

በሕገ መንግሥታቸው ውስጥ ለመሪዎች ሰላም የማይሰጥ አንቀጽ ተቀምጧል ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ እ.ኤ.አ በ2014 በሕገ መንግሥታቸው ላይ የዓባይን ወንዝ መጠበቅ ኃላፊነት የመንግሥት ነው ይላል።

የግድቡ ግንባታ ወደ ኋላ የማይመለስ መሆኑን የግብጽ መንግሥት ቢያውቅም በየጊዜው መግለጫዎችን ያወጣል። ያሉት ምሁሩ፤ ይህም ለግብጽ ሕዝብ ዝም እንዳላለ ለማሳየት ካልሆነ በስተቀር ኢትዮጵያን በማስፈራራት የሚስተጓጎል የግንባታ ሥራ እንደማይኖር ገልጸዋል።

ሞገስ ጸጋዬ

አዲስ ዘመን መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You