አዋጁ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚኖሩ ዜጎች እፎይታን የሚሰጥ ነው

አዲስአበባ፡– የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅ መጽደቅ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚኖሩ ዜጎች እፎይታ የሚሰጥ መሆኑ ተገለጸ።

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ የአዋጁን አላማ አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ ማብራሪያ እንደተናገሩት፤ ከመኖሪያ ቤት ኪራይ ጋር የተያያዙ ችግሮች ዜጎችን ለከፋ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እየዳረጉ ሲሆን፤ ለኑሮ ውድነት መጨመርም አንዱ ምክንያት እየሆነ ነው።

እስካሁን ባለው አካሄድ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋና የመቀመጫ ጊዜ የሚወሰነው በደላላ እና በአከራይ ተጽእኖ ብቻ ነው

ያሉት ሚኒስትሯ፤ በዚህ ረገድ መንግሥትም ጣልቃ በመግባት ፍትሐዊ አሰራር ለመዘርጋት እድሉ አልነበረውም ብለዋል። ይህም በተለይ በከተሞች አካባቢ የመንግሥት ሠራተኛውና ዝቅተኛ ገቢ ያለው ማህበረሰብ በከፍተኛ ችግርና መሳቀቅ ውስጥ እንዲኖር አስገድዶታል ሲሉም አስረድተዋል።

ሚኒስትሯ እንደገለጹት፤ አዋጁ የተከራይና አከራይ ግንኙነትን በሕጋዊ መንገድ ለመምራት ብሎም ግልጽነት የሰፈነበት አሰራር በመዘርጋት ዜጎች ተሳቀው የማይኖሩበትን ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችል ነው። አዋጁም የበርካታ ሀገራት ተሞክሮን በመውሰድ ዋጋ የሚጨምረው ማነው፤ አንዴትስ መጨመር አለበት፤ የሚለውን ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ተዘጋጅቷል።

ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት አንድ ሰው ከአጠቃለይ ገቢው ከ25 እስከ 30 በመቶ የበለጠ ለቤት ኪራይ መክፈል የለበትም። በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ግን በትንሹ ከሰባ በመቶ በላይ እየተከፈለ ይገኛል። ይህም ጤናን ጨምሮ ሌሎች መሠረታዊ ፍላጎቶችን በማዛባት የተለያዩ ዜጎችን ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እየዳረገ ይገኛል። የአዋጁ መጽደቅ ይህንን ቀውስ የሚያስቀር ሲሆን፤ መንግሥትም ተገቢውን ግብር በመሰብሰብ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን እንዲያከናውን የሚያስችል ነው ብለዋል።

በዝግጅት ወቅት ከክልሎች ጋር በርካታ ውይይት መደረጉንና ግብዓትም መሰብሰቡን የገለጹት ወይዘሮ ጫልቱ፤ አዋጁ የተከራዮችን መብት ብቻ ሳይሆን የአከራዮችንም ጥቅም በሚያስጠብቅ መልክ የተዘጋጀ እንደሆነም አብራርተዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሥራውን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ የሚያስችል የመንግሥትና የግለሰብ መኖሪያ ቤቶች አያያዝ ሶፍት ዌር አዘጋጅቷል ሲሉም ጠቅሰዋል።

የፍትህ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ በበኩላቸው፤ አዋጁን ለመተግበር ምን ያህል ዝግጅት ተደርጓል በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ በአዋጁ በክልሎችና ሁለቱ የከተማ መስተዳድሮች የተቆጣጠሪ አካል እንደሚወሰን ጠቁመው፤ በክልል ከተሞች ያሉ የከተማና መሠረተ ልማት ተቋማት ወይንም ተመሳሳይ ኃላፊነት ያለባቸው ቢሮዎችን ለዚህ ተግባር ክልሎች ይወስናሉ ብለዋል።

እነዚህ አካላት ለተቆጣጣሪው አካል በተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት መሰረት አዋጁን ተግባራዊ የሚያስደርጉ እንደሆኑና በዚህ ሂደት የከተማ ልማት ሚኒስቴር አዋጁን የመከታተልና ክልሎችን የማስተባበር ብሎም የመደገፍ ሥራ እንደሚያከናውን ጠቁመዋል።

እነዚህ አካላት እስከ ሦስት ወር የሚደርስ የቤት ኪራዩን ዋጋ በአስተዳደራዊ ቅጣት የመወሰን መብት አላቸው። ነገር ግን ጥሰቱ እንደ ሰነድ ማጭበርበር፤ ገቢ ግብር መሰወር ያለ የወንጀል ድርጊቶች ከሆነ በወንጀል ሕጉ ተጠያቂ የሚደረጉ ይሆናል ብለዋል።

አዋጁ በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተሞች እንዲሁም በሁሉም የክልል ከተሞች እና ለክልሎች ተጠሪ በሆኑ ዋና ዋና ከተሞች የሚተገበር ይሆናል። በተጨማሪም ክልሎች ሌሎች ከተሞችንም ችግሩ ይመለከታቸዋል ብለው ካመኑ ማካተት እንደሚችሉ በአዋጁ ተመላክቷል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You