ለዓባይ የተዘረጉ ለጋስ እጆች

ዜና ሀተታ

ዓባይ ወንዝ በኢትዮጵያውን የቁጭት፣ የእንጉርጉሮና የወቀሳ ዜማ ሆኖ ኖሯል፡፡ ማደሪያ ቢስነቱም የሊቃውንትና ጠቢባን ርዕሰ ጉዳይ ነበር፡፡ የዓባይ ውሃ መጠጥ ሆኖ እንዲጠጣ፣ መና ሆኖ እንዲጎረስ፣ ሲሳይ ሆኖ እንዲቆረስ፣ ለጨለማ ብርሃን እንዲሆን የእልፍ ኢትዮጵያውያን ምኞት ነበር፡፡

በትችትና ምኞት የተነገረውን የዓባይ ወንዝ ግንድ ይዞ ዟሪነት ታሪክ ለመግታት፣ የልጅ ባዕድነቱን ለማክተም፣ የማደሪያ ቢስነት ትርክቱንም ለማስቆም፣ ለጨለማ ብርሃን እንዲሆንና የኢትዮጵያውያንን ህልም እውን ለማድረግ የዓባይ ግድብ ግንባታ በወርሀ መጋቢት 2003 ዓ.ም  በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በጉባ ወረዳ ሰማይ ስር የግንባታው የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ።

እነሆ በአሁኑ ወቅት ታዲያ የዓባይ ግድብ ግንባታ በልጆቹ ብርቱ ክንድ እየተገነባ 13 ዓመታትን ተሻግሯል። የኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ ሀሩር ከበረታባቸው የጉባ ተራሮች ግርጌ ታላቅ ጀብዱ ፈፅሟል። ዓባይ ግስጋሴውን ገታ አድርጎ ወደ ውስጥ በአትኩሮት እንዲያጤን ተደርጓል፤ በሀገር እጅ ለሀገር ልጅ እንዲሆንም ተደርጓል።

ጉዞው ከተገታና በቤቱ ማደር ከጀመረም ዓመታትን አስቆጠሯል፤ በኢትዮጵያውያን የድጋፍ ማዕበል ታጅቦ፣ በጠላት ዓይን እየተገለመጠ፣ በርካታ ተግዳሮቶችን በመሻገር የተስፋ ፍሬውን ለልጆቹ ማቅመስ ከጀመረም ሰነባብቷል።

ግድቡን ከዳር ለማድረስ እናቶች በመቀነታቸው ከቋጠሯት ገንዘብ ለግሰዋል። ከዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ እስከ ባለሀብት በገንዘብ፣ በእውቀት፣ በጉልበትና በቴክኒካል ጉዳዮች ድጋፍ አድርገዋል። ከልጅ እስከ አረጋውያን በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ለግድቡ ያለማቋረጥ አለኝታነታቸውን አረጋግጠዋል።

በርካታ ተቋማት ከተቋቋሙበት ተግባርና ኃላፊነት ጎን ለጎን ቦንድ በመግዛት፣ ቴክኒካል ድጋፍ በማድረግና ሰራተኞችን በማስተባበር አሻራቸውን እንዲያሳርፉ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት፣ የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ፣ መድን ሰጪ ኩባንያዎች እና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ድጋፍ ካደረጉ ተቋማት መካከል ናቸው። ተቋማቱም ለዝግጅት ክፍላችን ይህንን ብለዋል።

ደረሰ በላይነህ ይባላሉ። በኢትዮጵያ መድን ድርጅት የፕሮሞሽንና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ናቸው። የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ለዓባይ ግድብ ግንባታ የተለያዩ አስተዋጽኦዎችን አበርክቷል። በ2013 ዓ.ም የ50 ሚሊዮን ብር፣ በ2014 ዓ.ም የ100 ሚሊዮን ብር፣ በ2015 ዓ.ም የ155 ሚሊዮን 310 ሺህ ብር በ2016 ዓ.ም 173 ሚሊዮን 350 ሺህ ብር ቦንድ በመግዛት የድርሻውን ተወጥቷል።

በአጠቃላይ ድርጅቱ ለዓባይ ግድብ የ478 ሚሊዮን 660 ሺህ ብር ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ማድረጉን የሚናገሩት አቶ ደረሰ፤ ድርጅቱ መድን ሰጪ ተቋም እንደመሆኑ መጠን በዓባይ ግድቡ ምንም ዓይነት አደጋ ቢደርስበት መቋቋም እንዲችል የመድን ሽፋን ተሰጥቶታል ብለዋል። የተቋሙ ሰራተኞች ለግድቡ የራሳቸውን አሻራ እንዲያሳርፉ በሁለት ዙር ቦንድ እንዲገዙ የማስተባበር ስራም ተሰርቷል ብለዋል።

ታላቁ ህዳሴ ግድብ ለፍጻሜ ደርሶ ኢትዮጵያ በስራ እድል ፈጠራ፣ በኃይል አቅርቦት፣ በመስኖ ልማትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ተጠቃሚ እንድትሆን ድርጅቱና ሰራተኞቹ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም ለዓባይ ግድቡ እጃቸውን ከዘረጉ ተቋማት አንዱ ነው። በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር ከ2013 ጀምሮ 389 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን የሚናገሩት የኢትዮ ቴሌኮም ኮሚኒኬሽን ኦፊሰር አቶ መሳይ ውብሸት ናቸው። ድጋፉ የተደረገው በ8100፣ በቴሌ ብር፣ በቦንድ ግዢ፣ በኤስኤምኤስ እና በሌሎች አማራጮች መሆኑን ይናገራሉ።

የበላነህ ክንዴ ግሩፕ የዓባይ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ጀምሮ በዓይነትም በገንዘብም አስተዋጽኦ አበርክቷል የሚሉት የድርጅቱ ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰጠኝ እንግዳ ናቸው። ድርጅቱ ቦንድ በመግዛትና ግንባታውን የሚያከናውኑ ሰራተኞችን ለማበረታታት የቁም እንስሳትን ጭምር በስጦታ አበርክቷል።

ድርጅቱ በዓይነትና ቦንድ በመግዛት ያደረገው ድጋፍ 36 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር ነው። 33 ሚሊየን ብሩ ለቦንድ ግዢ ቀሪው ድግሞ ግድቡን ለሚያከናውኑ ሰራተኞች የዓይነት ድጋፍ እንደሆነም ጠቁመዋል።

የዓባይ ግድቡ እውን መሆን ለድርጅቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል የሚሉት አቶ ሰጠኝ፤ በአምራች ዘርፍ የተሰማራ ድርጅት እንደመሆኑ መጠን የኃይል አቅርቦት መቆራረጥን ችግር በዘላቂነት ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸውም አብራርተዋል።

“ድርጅቱ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ለዓባይ ግድብ ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪም በሀገር ደረጃ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች ሲያጋጥሙ ድጋፍ የማድረግ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማትን የመገንባት ስራ ያከናውናል። በቀጣይም ለህዳሴ ግድቡ ድጋፍ በሚያስፈልግበት ጊዜ ሁሉ ድጋፉን ያደርጋል” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ዋቄ በበኩላቸው፤ ባንኩ ከመጀመሪያው ጀምሮ ታሪካዊ የሆነ ታላቅ ኃላፊነት ተሰጥቶት ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመው፤ በተለይ በፋይናንስ በኩል ቦንድ ከህትመት ጀምሮ እስከ ስርጭት ያለውን ስራ እንዲሰራ የተሰጠውን ኃላፊነት ሲወጣ የቆየ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለግድቡ ግንባታ ፕሮጀክት የተለያዩ እገዛዎችን ከማድረጉም ባለፈ ለዓባይ ግድብ ተግባር ማስፈፀሚያ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ያግዝ ዘንድ ሁለት ተሽከርካሪዎችን በስጦታ አበርክቷል። ቦንዶችን ከ25 ብር ጀምሮ በማሳተም ለህብረተሰቡ የማሰራጨት ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ መድን ሰጪዎች ማህበር አባል የሆኑ 18 መድን ሰጪ ኩባንያዎችም ለዓባይ ግድብ አስተዋጿቸውን አበርክተዋል። ግድቡ ከተጀመረ ጀምሮ አንድ ቢሊዮን 563 ሚሊዮን 893 ሺህ ብር ቦንድ በመግዛትና በጥሬ ገንዘብ በመስጠት የድርሻቸውን መወጣታቸውን ማህበሩ አስታውቋል።

የዓባይ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት መጋቢት 2003 ዓ.ም ጀምሮ እስከ የካቲት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ከሀገር ውስጥ ቦንድ ግዢና ስጦታ፣ ከዲያስፖራ ቦንድ ግዢና ስጦታ፣ ከ8100 A፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ገቢ እና ከደረት ፒን ሽያጭ በአጠቃላይ ከ19 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡንም ከማስተባበሪያው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You