* መሰረተ ልማትን በፍትሐዊነት በማከፋፈል ረገድ ችግር ነበረባቸው
* የፍትሐዊነት ቁጥጥር መስፈርት አውጥተው እንዲሰሩም አቅጣጫ ተቀምጧል
አዲስ አበባ፤ ኢትዮ ቴሌኮምን ጨምሮ ስምንት የፌዴራል ተቋማት በተደረገባቸው ግምገማ እስከአሁን መሰረተልማትን ለክልሎች በፍትሐዊነት በማከፋፈል ረገድ የጎላ ችግር ስለነበረባቸው ግልጽ መስፈርት እያዘጋጁ እንዲሰሩ እንደሚደረግ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ገለጸ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም ትናንትና በሰጡት መግለጫ ፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ መንገዶች ባለስልጣን እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመሰረተ ልማት ግንባታ የክልሎች ፍትሐዊ ክፍፍል ላይ ችግር መኖሩ ታይቷል ብለዋል። በተጨማሪ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን፣ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር እንዲሁም የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ከአየር ማረፊያዎች ግንባታ አንጻር የመሰረተ ልማት ፍትሐዊነታቸው ግምገማ እንደተደረገባቸው አመልክተዋል።
እንደ ወይዘሮ ኬሪያ ገለጻ፣ አንዳንዶቹ የእራሳቸው የፍትሐዊነት ክፍፍል መስፈርት ያወጡ ሲሆን፣ ምንም አይነት መስፈርት ሳይኖራቸው ሲሰሩ የነበሩም እንደነበሩ ተረጋግጧል። በአጠቃላይ ግን ሁሉም ተቋማት መሰረተ ልማቶችን ወደክልሎች የሚያሰራጩበት መንገድ እስከዛሬ ችግር የነበረበት መሆኑ ታውቋል። በመሆኑም በፌዴራል ደረጃ የፍትሐዊነት ቁጥጥር መስፈርት አውጥተው እንዲሰሩ እና ክትትል እንዲደረግበት ፌዴሬሽኑ አቅጣጫ አስቀምጧል።
በቀጣይ ጊዜያት በየፌዴራል ተቋማቱ የሚገነቡ መሰረተ ልማቶች የሁሉንም ክልሎች ዕድገት የተመጣጠነ ከማድረግ አንጻር ቁጥጥር እንደሚደረግበት የገለጹት ወይዘሮ ኬሪያ፣ እስከአሁን ስለተሰሩት ሳይሆን በቀጣይ ስለሚገነቡት የመሰረተ ልማት ክፍፍሎች በቂ መስማማትና ውይይት መደረግ እንዳለበት መወሰኑን ተናግረዋል።
እንደ ወይዘሮ ኬሪያ ከሆነ፤ ከዚህ በኋላ ማን ምን አይነት ችግር አለበት? ተብሎ እና የትኛው ክልል ምን አይነት መሰረተ ልማት ያስፈልገዋል? የሚለው በፍትሐዊነት ማረጋገጫ መስፈርት መሰረት እየተጠና እንዲሰራ ይደረጋል። በክፍፍሉ ላይ ለክልሎች የመሰረተ ልማት ስርጭቱ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት በቂ መስማማት እና ውይይት በሚመለከታቸው አካላት እንዲደረግበት አቅጣጫ ተቀምጧል።
የፌዴራል መንግሥትም የክልሎች የተመጣጠነ ዕድገት እንዲኖራቸው የልማት ስርጭቱ ፍትሐዊነት ላይ ክትትል የሚያደርግበት አሰራር እንዲኖረው ምክር ቤቱ ተወያይቶበታል።
ከዚህ በተጨማሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤቱ አዲስ ቀመር ማዘጋጀቱን የገለጹት ወይዘሮ ኬሪያ፣ አዲሱ ቀመር በተሻለ ሁኔታ የክልሎች ካቢኔ እና የሚመለከታቸው አካላት ውይይት እንዳደረጉበት አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 8/2011
ጌትነት ተስፋማርያም